1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፓሪሱ የአፍሪቃ የሳይንስ ተሰጥኦ ሳምንት ተሳታፊ ወጣቶችና ምርምሮቻቸው

ረቡዕ፣ ኅዳር 1 2014

በፈረንሳይ ፓሪስ በየዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪቃ የወጣቶች የሳይንስ ተሰጥኦ ሳምንት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉበት ነው። በዘንድሮው መርሀ ግብርም ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣት ሳይንቲስቶችም ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/42pWV
Selamawit Getachew - Wissenschaftlerin
ምስል Privat


በፈረንሳይ ፓሪስ በየ ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪቃ የወጣቶች የሳይንስ ተሰጥኦ ሳምንት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ  ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉበት ነው። 
ከጎርጎሪያኑ  ጥቅምት  18  ቀን  2021 ዓ/ም ጀምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው  የወጣት አፍሪቃውያን የሳይንሳ ተሰጥዖ ሳምንት የበርካታ ሃገራት ወጣት ሳይንቲስቶች የታደሙበት ሲሆን ሰላማዊት ጌታቸው እና እስከዳር ገበየሁ የተባሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣት ሳይንቲስቶችም ተሳትፈዋል። በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ  ለሀገራቸው ጥሩ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በሚሳተፉበት በዚህ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያኑ ወጣቶቹ ለተሳትፎው የተመረጡት ወጣት ሰላማዊት እንደምትለው በሙያቸው ባደረጓቸው ሳይንሳዊ ጥናቶች ነው። 

Selamawit Getachew - Wissenschaftlerin
ምስል Privat

ወጣት ሰላማዊት ጌታቸው የቁስ ሳይንስ ባለሙያ ስትሆን የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቁስ ሳይንስ እና በምህንድስና፤ ሁለተኛ ዲግሪዋንም በተመሳሳይ ዘርፍ ፈረንሳይ ከሚገኘው ሞንፖሌ የሳይንስና ቴክኖሎጅ  ዩንቨርሲቲ  አግኝታለች። የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ፅሁፏንም በፈረንሳይ እንዲሁም ጀርመን ከሚገኘው የውሃ ማጣሪያ ኬሚካሎችን እና መገልገያዎችን ከሚያቀርበው ኩሪታ ከተባለ ኩባንያ ጋር በኃይል ማመንጫዎች ውስጥ ከውሃ ማከሚያ ኬሚካሎቻቸው ውስጥ አንዱን በመጠቀም ዝገትን መከላከል በሚቻልበት ዘዴ ላይ ምርምር አድርጋለች።
ይህንን የምርምር ውጤቷን በተለያዩ መድረኮች ስታቀርብ የቆየችው ሰላማዊት፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በለንደን ብሩኔል  ዩንቨርሲቲ በሜካኒካል የአየር እና የጠፈር ምህንድስና ቴክኖሎጅ የዶክትሬት ዲግሪዋን በመከታተል ላይ ትገኛለች።ለሰሞኑ የፓሪስ  ተሳትፎ ያበቃት ሌላው ሳይንሳዊ ምርምርም  መግነጢሳዊ-ተኮር በሆነ አቀራረብ  አጠቃላይ በፈሳሽ ማስተላለፊያ በቧንቧዎች ውስጥ የሚከሰት ዝገትን መከላከል የሚቻልበትን ስልት በሚያመላክተው ጥናቷ ነው።

Selamawit Getachew - Wissenschaftlerin
ምስል Privat

ሰላማዊት እንደገለጸችው በጥናቷ ዝገትን ለመጠቆም የምትጠቀመው መሳሪያ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር የተገናኘ ሲሆን ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ነው። ይህ ሳይንሳዊ ጥናቷም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድታለች።
ሌላኛዋ ተሳታፊ በኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም በረዳት ተመምርምሪነት ከአራት ዓመታት በላይ የሰራችው እስከዳር ገበየሁ ነች። እስከዳር የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያያዘችው ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በኤለክትሪክና በኮምፒዩተር ምህንድስና  ሲሆን በ2012 ዓ/ም ኢትዮጵያ  ባደረገችው ሳተላይት የማምጠቅ ስራም  ተሳታፊ ነበረች ።በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቼክ ቴክኒካል ዩንቨርሲቲ በኮምፒዩተር እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሁለተኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ ትገኛለች። በፓሪሱ በመርሃ ግብር ተሳታፊ እንድትሆን የተመረጠችውም ዝቅተኛ ዋጋ ባላቸው አነስተኛ ሳተላይቶች ላይ ባደረገችው ምርምር ነው።

Eskedar Gebeyehu - Wissenschaftlerin
ምስል Privat

በፈረንሳይ ፓሪስ በየ ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪቃ የወጣቶች ሳይንሳዊ ተሰጦዎች ሳምንት በየሀገሩ በሚገኙ የፈረንሳይ ኢምባሲዎችና ዩንቨርሳይንስ በተሰኘው የፈረንሳይ የህዝብ ተቋም አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን፤በዘንድሮው መርሀ ግብርም ከ35 ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ እና ከ27 የአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ 49 ሳይንቲስቶች ተጋብዘዋል። ከነዚህም ውስጥ ሁለቱን ወጣት ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች ጨምሮ 26ቱ ሴቶች ሲሆኑ  23ቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው።ወጣት እስከዳር ገበየሁ ምንም እንኳ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተሳተፈችው ካለችበት ቼከ ሪፐብሊክ   በበይነመረብ ቢሆንም ፤ በዚህ መርሃ ግብር  «አፍሪቃውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት እንደምንችል ተመልክቻለሁ።» ትላለች ።
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው የምትለው ወጣት እስከዳር ለወደፊቱ በሳይንሱ ዘርፍ ሴቶችን የማገዝ ተገቢ መሆኑን ገልፃለች።ሰላማዊትም ይህንን ሀሳብ እንምታጋራ ገልጻ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ሀገሯ ስትመለስ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ የግንዛቤ ማስጨብጫ መድረኮችንና ስልጠናዎችን ለማዘጋጄት ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች።

Selamawit Getachew - Wissenschaftlerin
ምስል Privat

ወጣት ሳይንቲስቱ ከጎሮጎሪያኑ ካለፈው ጥቅምት አእጋማሽ ጀምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ በነበራቸው የአንድ ሳምንት ቆይታ ሳይንሳዊ የፈጠራ፣ የክህሎት እና የልምድ ልውውጦችን  ያደረጉ ሲሆን፤ ሳይንሳዊ  ፈጠራዎችን ለማዳበር የሚስችሉ የተፈጥሮ ሳይንስ ማዕከላትን ፣ዩኒቨርሲቲዎችንና  ሙዚየሞችንም ጎብኝተዋል።በዚህም በኢትዮጵያ ሊተገበሩ የሚገባቸው  በርካታ ልምዶች ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ