በፀጥታ ኃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር በውስን ሰዎች የተከበረው ኢሬቻ ሆራ አርሰዲ
እሑድ፣ መስከረም 24 2013
ከፍተኛ የፀጥታ አካላቱ ፍተሻ እና ዝውውር ከትናንት ጀምሮ ነግሶባት የቆየው የቢሾፍቱ ከተማ ዛሬ እሬቻ ሆራ አርሰዲን አክብራ ዋለች፡፡ የቢሾፍቱ እሬቻ ሆራ አርሰዲ በቁጥር እጅግ ውስን ሰዎች ብቻ በተገኙበት ነው ተከብሮ የዋለው፡
ወትሮም ከተማዋ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ እንግዶችን ለእሬቻ ሆራ አርሰዲ ከአራቱም አቅጣጫዎች ተቀብላ ስታስተናግድ ለኖረች ቢሾፍቱ ይህ ከተለመደው አንጻር ቁጥሩ እጅጉን ያነሰ ከመሆኑ ባለፈም፤ ያዘን ያህል የተቀዛቀዘ ነው፡፡
ከቅዳሜ ጀምሮ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ መግባት የሚፈቀድለት ሰው የይለፍ ካርድ የያዘ አለዚያም የከተማዋ የነዋሪነት መታወቂያን የያዘ ብቻ ነው፡፡ በየአቅጣጫው ከተማዋን የከበቡ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የመግቢያ ካርድ እና የከተማዋ የነዋሪነት መታወቂያ ከያዙት ውጪ ወደ ከተማዋ መግባት የሚሻን ማንኛውንም ሰው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያስገድዱ ነበር፡፡
ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ወደ ሆራ አርሰዲ ሃይቅ የሚደረግ ጉዞ ሲጀምርም ሲደረግ የነበረው ፍተሸና ብርበራ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ወደ ስፍራው ሲጓዙ የነበሩ አምቦላንሶችና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች አንኳ ሳይቀሩ ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ ሲደረግባቸው ነበር፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር መከላከያ እና የኦሮሚያ ልዩ ሃይሎች በከተማዋ ወዲያ ወዲህ ስዘዋወሩም ይታያሉ፡፡
ወትሮም በሚሊዮኖች የሚጨናነቀው የሆራ አርሰዲ ሃይቅ አባገዳዎች፣ ሃዳሲንቄዎችና ወጣቶች በተገኙበት በውስን ሰዎች ብቻ ነው የተከበረው፡፡ ከለሊት እስከ ማምሻው በውስጧ በሚርመሰመሱ የበዓሉ ታዳሚ እንግዶች የምትጨናነቀው ቢሾፍቱ ዛሬ ግን የገበያን ያህል አንኳ ሳትደምቅ ነው የዋለችው፡፡ የኢሬቻ ስነስርዓቱም ቢሆን ገና በሶስት ሰዓት ገደማ ተፈጽሞ ተጠናቋል፡፡
በየቦታው ተቧድነው የተለያዩ አከባቢዎች የኦሮሞ ባህላዊ ጨዋታዎችን የሚያደምቁ ወጣቶችም ዛሬ በዚያ የሉም፡፡ መግቢያ ያልያዙ በርከት ያሉ ወጣቶችና አንግዶች ወደ እሬቻው ስፍራ ለመጓዝ ጥረት ቢያደርጉም መግቢያ ካርድ አልያዛችሁም በሚል በፀጥታ ኃይሎች ተከልክለዋል፡፡
በዘንድሮ የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ ውስን ሰዎች ብቻ እንዲታደሙ ውሳኔ የወሰደው መንግስት ምክኒያቱንም የኮሮና ተዋሲ ወረርሽኝ ሲል ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ የሰው ቁጥር አንሶ እሬቻ እንዲደረግ የተወሰነው በኮሮና ምክኒያት ብቻ አይደለም ብለው የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡ በእሬቻ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥረ በጥቅ ተሳታፊዎች እንዲወሰን ወቅታዊው የፖለቲካ ትኩሳቶች መንግስት ላይ ተቃውሞ እንዳያስነሳ ስጋት በመፈጠሩም ጭምር ነው ሲሉ በሆራ አርሰዲ ከታደሙት ተሳታፊዎች ለዶይቼ ቨሌ የተናገሩ አሉ።
ስዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ