1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነትና ግጭት የተጎዳዉ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2014

በኢትዮጵያ በቱሪዝም መስዕብነት የሚያገለግሉ ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮ ናቸው፡፡ በተለይም ከታሪክ ጎብኚዎች አንጻር ትልቁ የቱሪስቶች መስዕብ በሰሜን የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ ይሁንና አከባቢው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጦርነት መጎዳቱ ዘርፉ ትልቁ ኪሳራ ውስጥ እንዳስገባው የአስጎብኚ ድርጅትች ይገልጻሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4FkSB
Äthiopien | Tourismus Woche
ምስል Ethiopian Tourist Office

የተጎዳዉን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዴት እናሻሽል?

በኢትዮጵያ በቱሪዝም መስዕብነት የሚያገለግሉ ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮ ናቸው፡፡ በተለይም ከታሪክ ጎብኚዎች አንጻር ትልቁ የቱሪስቶች መስዕብ በሰሜን የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ ይሁንና አከባቢው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጦርነት መጎዳቱ ዘርፉ ትልቁ ኪሳራ ውስጥ እንዳስገባው አስተያየቱን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት ማዮ-ኢትዮጵያ የተሰኘን የአስጎብኚ ድርጅት በባለቤትነት የሚመሩት አቶ ዮሴፍ አልታዬ ገልጸውልናል፡፡ ዮሴፍ ቀደም ባሉ ጊዜያት ስራቸውና መተዳደራቸውን ያደረጉት፤ ብሎም ለሌሎች በርካቶች የስራ እድልን ፈጥረው የቆየት ኢትዮጵያ በምታስተናግዳቸው ከተለያዩ አገራት ከሚመጡ ጎብኚዎች በሚገኝ ገቢ ነበር፡፡ ዓለማቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ያቀዘቀዘው ዘርፉን ለመታደግ በርካታ ስራዎች በኢትዮጵያ ቢሰሩም፤ ድህረ ኮቪድ በዓለም በጉልህ ከሚጎበኙ ጢቂት አገራት ተርታ እስከ ፎርብስ መጽሔት የኢትዮጵያ ስም ከቀዳሚዎቹ ቢቀመጥም፤ ያንን ተከትሎ በአገሪቱ የተስፋፋው ጦርነት ግን ዘርፉን ክፉኛ ፈትኖት ቆይቷል፡፡ 
በድህረ ኮቪድ-19 በጦርነት የተፈተነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም የመነቃቃት ተስፋ እና ተግዳሮቶቹ በርካቶችን ሚያነጋግር ነው፡፡
የማዮ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤቱ ዮሴፍ አልታዬ ከኮቪድ ማግስት በተስፋ ሲጠበቅ የነበረውን የቱሪዚሙን ተስፋ በሰሜን ኢትዮጵያ ተጀምሮ በተለያዩ አገሪቱ አከባቢዎች የተስፋፋው ግጭትና ጦርነት ለዘርፉ መጥፎ ዜናን ይዞ እንደመጣበት ያሰምራል፡፡ እራሱን ጨምሮ ሌሎች በተመሳሳይ ዘርፍ ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ያስተዳድሩ የነበሩ ጓደኞቹም ጭምር የእለት ጉርሳቸውን እንኳ ለመሸፈን ከለመዱት ሙያ ውጪ ባገኙት ስራ መሯሯጥን ከተላመዱ ቀናት ወራትን፣ ወራትም ዓመታትን እየጨመሩ መምጣታቸውን ያወሳል፡፡ ምክኒያት በአገር ውስጥ በነበረው አለመረጋገት ብቅ የሚል ቱሪስት ማግኘት አዳጋች ሆኗልና፡፡ 
ዩባ የተሰኘው የሌላኛው የአስጎብኚ እና ጉዞ ወኪል ጄኔራል ማናጀር ቅድስት ደመቀ  በበኩላቸው ባጋሩን አስተያየት፤ በኮቪድም ሆነ በአለመረጋጋቱ ምክኒያት እንደማንኛውም አስጎብኚ ድርጅቶች ፈተናው ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ይሁንና አሁንም ግን ተስፋ አለን ይላሉ፡፡ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የተቀዛቀዘውን የቱሪዚሙን ኢንደስትሪ የማነቃቃት ዓላማን ይዞ በአዲስ አበባ የቱሪዝምና ቴክሎሎጂ ሳምንት በሚል ባለድርሻ አካላትን ያሰባሰበ አውደ ርዕይ አሰናድቶ ነበር፡፡ በአውደ ርዕዩም ለቱሪዝም ኢንደስትሪ የቴክኖሎጂ ጥምርታ ያለው ጉልህ ሚና ተወስቷል፡፡ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማውሳት ጀምሮ የተለያዩ ድርጅቶችም ምርትና አገልግሎቶቻቸውን አስተዋውቀውበታል፡፡ ከእጅ ጥበብ ስራዎች እስከ የቱሪዝም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችም በመድረኩ ጎልተው ታይተዋል፡፡
ከተመሰረተ ገና 2 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረው የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በኦሮሚያ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ዓለማቀፍና የአገር ውስጥ ገቢያውን የማስፋት ተግባርን ከቀዳሚ ዓላማዎቹ አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡ አቶ ነጋ ወዳጆ የኮሚሽኑ ምክትል ሃላፊ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ የቱሪዝም ኮሚሽኑ ተመስርቶ ወደ ስራ በገባበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ተግዳሮቶች ብፈተንም የማይናቅ መሰረት መጣሉንም ግን ያወሳሉ፡፡ 
አሁን ላይ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ የራሱን ጥላ ያጠላው አለመረጋጋት ከቱሪዝም ጋር ሆድና ጀርባ ናቸው የሚሉት የማዮ ኢትዮጵያው አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ዮሴፍ አልታዬ አሁንም ተስፈኛ ናቸው፡፡ ከጦርነቱ ድብርት መውጣቱ እምብዛም ጊዜ እንደማይወስድም በመግለጽ፤ የተዘነጋ የመሰለውን ዘርፉን የማነቃቃቱ ስራ ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ነው ይላል፡፡ ሰሞነኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንቅስቃሴም በየደረጃውና በየዘርፉ ባሉ የአገሪቱ የቱሪዝም ባለድርሻዎች ሊሰፋ የሚገባ ነው ባይ ናቸው፡፡ 
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ ወዳጆ አጅን አጣጥፎ፣ በተግዳሮቶች ተገድቦ ከመቀመጥ ይልቅ ዘርፉን ለማነቃቃት በተሄደበት መንገድ አዳዲስ መዳረሻዎችን ማፍጠር መቻሉንም ያመለክታሉ፡፡ በዝዋይ/ባቱ ኃይቅ ላይ የሚከበረውን የጥምቀት በዓልን በልዩ ሁኔታ ትኩረት በሚስብ መልኩ ማክበር መጀመርን ጨምሮ የቱሪስት ትኩረት የሚስቡ ፋብሪካዎችንም ጭምር መዳረሻ በማድረግ እምርታ ተገኝቶበታልም ብለዋል፡፡ 
የቱሪዝም ኢንደስትሪው ዘርፍ በኢትዮጵያ ባሁን ወቅት ከ5 ቀዳሚ የልማት ትኩረት አንዱ ተደርጎ መቀመጡን የሚያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመባል ሁለቱን አቅፎ ሲንቀሳቀስ የነበረው መስሪያ ቤቱ በተያዘው ዓመት የቱሪዝም ሚኒሰቴር ተብሎ ሲደራጅ ለዘርፉ የተሰጠውን አይነተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው ተብሎለታልም፡፡ በመሆኑም ዘርፉን በአዲስ መልክ የማደራጀቱ ተግባር እየተከናወነ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ ትኩረት ተነፍጎ ቆይቷል ያሉት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ጨምሮ የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ኮንፌሬንስ ቱሪዝምንም ጭምር የማዘጋጀት እድሎችን የሚያሰፉ መሰረተ ልማቶች የማጥናት ተግባራት ሲከወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ 
አቶ ዳውድ ሙሜ ከፓርኮች አስተዳደር ጀምሮ እስከ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊነት ከቱሪዝም ጋር ጥብቅ ትስስር ባላቸው ተግባራት ለዓመታት ተሰማርተው ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ማነቃቃት፤ ብሎም ማበልጸግ የሚቻለው ከማስተዋወቅ ጀምሮ ዘርፉ የሚፈልገውን የማዳረሻ ልማትን እውን ማድረግ ሲቻል ነው ባይ ናቸው፡፡ 
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶችን ከሞላ ጎደል የማበልጸጉ ስራ በመስሪያ ቤታቸው ትኩረትን ካገኙ ተግባራት ናቸው ይላሉ፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የትራንስፖርት እና ቴሌኮም ተደራሽነትን ጨምሮ ለጎብኚዎች በመዳረሻዎቹ መደላድል መፍጠር ሚኒስቴሩ አተኩሮ ከሚሰራባቸው ተግባራት ተደርጎም ተጠቅሷል፡፡
የቱሪዝም ባለድርሻ አካላቱ አለመረጋጋቱና ጦርነት በኢንደስትሪው ላይ ያሳረፈውን ጥላ በአንድ ሃሳብ ይመሰክራሉ፡፡ ኮሽታን ለማይወድ ዘርፉ ግጭቶች አሉታዊ ሚናን ተጫውተዋል ባይ ናቸው፡፡ 
ከኮቪድ ወረርሽኝ ማግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ኢንደስትሪውን አስካፊ ሁኔታ ውስጥ ማስገባቱ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ጦርነቱ ያደረሰው ጉዳት ግልጽ ቢሆንም ተስፋዎቹ ላይ በመስራት ዘርፉ እንዲንሰራራ መስራት ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ 

Äthiopien | Tourismus Woche
ምስል Ethiopian Tourist Office
Äthiopien | Tourismus Woche
ምስል Ethiopian Tourist Office
Äthiopien | Tourismus Woche
ምስል Ethiopian Tourist Office


ስዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ