1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት የተጎዱ የአማራ አከባቢዎች

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015

ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ጦርነት ባስፋፉ ጊዜ ከ240 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዘጎች ላይ የተለያዩ ሰብዓዊ ጥቃቶች መድረሱንና በትንሽ ግምት ከ292 ቢሊየን ብር የላቀ ሃብት መውደሙን በክልሉ የተደረገ ጥናት አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4HXk0
Äthiopien | Teile der Amhara-Region nun unter Kontrolle der Regierung
ምስል Waghemra Communication office

በክልሉ ከ 292 ቢሊየን ብር በላሽ ኃብት ወድሟል

ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ጦርነት ባስፋፉ ጊዜ ከ240 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዘጎች ላይ የተለያዩ ሰብዓዊ ጥቃቶች መድረሱንና በትንሽ ግምት ከ292 ቢሊየን ብር የላቀ ሃብት መውደሙን በክልሉ የተደረገ ጥናት አመልክቷል።

በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ በአማራ ምሁራን መማክርት እና በአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጋራ አጥንተናል ያሉት የሳይንሳዊ ጥናት ውጤት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ሲያደርጉ ነው ይህን ያሉት፡፡

የአጥኚዎች ጥምረቱ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫው በጥናቱ በሕዝቡ ላይ የደረሰውን ሁለንተናዊ ጥቃትና ውድመት ማኅበረሰቡ ውስጥ በመግባት (Census) ማጥናታቸውን ነው ያመለከቱት፡፡ ጥናቱ ውድመቱ በደረሰባቸው አከባቢዎች የፌዴራል ተቋማት ውድመት እና አሁንም ድረስ በመረጋጋት ላይ ያልሆኑ የተጎዱ አከባቢዎችን አለመካተቱም ተነግሯል፡፡

ጥናቱን አስመልክተው በጋራ መግለጫ የሰጡት የሶስቱ ተቋማት ተወካዮች ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ያለውን ጉዳት ብቻ በዚህ ጥናት ማካተታቸውን አመልክተዋል፡፡ ጥናቱ ትኩቱን ያደረገውም በአማራ ክልል የሚገኙ 8 ዞኖች ውስጥ በ87 ወረዳዎች- 945 ቀበሌዎች እንዲሁም የደሴ ከተማ አስተዳደር ላይ ማጠንጠኑም ነው የተብራራው፡፡ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ይህ ጥናት ለማንም ያላዳላ እና ሳይንሳዊ ጥናት ሆኖ እንዲወጣ ሰፊ ጥረት መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

Äthiopien - IDPs in Debark, Amhara Region
ምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office

ከመግለጫው ጋር በጥናቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በክልሉ የደረሰው ጥፋትና ውድመቱን በግልፅ በቦታና መጠን በፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር ተደግፎ ያሳያል የተባለው ድረገጽ እና በዚሁ ላይ የተዘጋጀው መጽሃፍም ይፋ ሆኗል፡፡ እነዚህ መረጃዎች የተሰበሰቡት የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ ጥምር ጦር ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች እንዲለቁ በተደረገ ማግስት ውሎ ሳያድር ባለሙያዎችን በማሰማራት መሆኑን ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ መግለጫው ላይ የተሳተፉ ዶ/ር ዮናስ ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤቱ እና ድረገጹ “በአማራ ክልል በትግራይ ኃይሎች የደረሱ የጅምላ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈር፣ ከጦርነቱ ጋር የማይገናኙ የማህበረሰብ መገልገያ ተቋማት ውድመትን እና በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቁ ድርጊቶችን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ማስገንዘብ ነው” ተብሏልም፡፡

የጥናቱን አበይት ይዘት ለጋዜጠኖች ያብራሩት የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ጸሐፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን፤ በጥናቱ ሂደት 837 ሺህ 687 የተለያዩ ጉዳቶች የደረሰባቸውን ሰዎች መድረስ መቻሉን አመልክተዋል።

እንደ ጥናቱ ጉዳት ጋስተናገዱት የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ከ409 ሺህ በላይ የሚሆኑቱ ሴቶች ሲሆኑ ከ263 ሺህ የላቁ ደግሞ ህጻናት ናቸው፡፡ ግድያ፣ ከባድ የአካላዊ ድብደባ፣ እገታ፣ ከኢትዮጵያ ጥምር ጦር ጋር በሚደረገው ጦርነት ማህበረሰቡን ከፊት ለፊት አሰልፎ የጥይት ማብረጃ ማድረግ እና ስነልቦናን የሚጎዱ ድርጊቶች ከተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶች ናቸው ብሏልም ጥናቱ፡፡ እንደ ጥናቱ ከ7 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቶ እስካሁንም የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ በጦርነቱ ተሳትፎ ሳይኖራቸው መገደላቸው የተረጋገጠ ደግሞ 7 ሺህ 3 ናቸው ተብሏል፡፡

Äthiopien | ausgebrannte Häuser in Molale
ምስል Efratana Gidm woreda Communication

በተቀመጠው የጥናቱ የጊዜ ማእቀፍ ብቻ በጦርነቱ በአማራ ክልል ከግለሰብ እስከ ክልላዊ ተቋማት 292 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ከጥቅም ውጪ ተደርጎ ወድሟል፡፡ ጥናቱ በክልሉ የሰቆጣ 2 ወረዳዎችን እና ራያ አከባቢ እንዲሁም ወልቃትን፤ በሌሎች አከባቢም እንደ ባንክ ያሉ የፌዴራል ተቋማት ውድመት አለማካተቱም ነው በአጥኚዎቹ የተገለጸው፡፡

በጥናቱ የተካተቱ ውድመቶች እና ሰብዓዊ ጉዳቶች በጦርነቱ ተሳትፎ ያልነበራቸውና የጦርነቱ ኢላማ መሆን ያልነበረባቸው ግለሰቦችና ተቋማት መሆናቸውም አጽእኖት ተሰትቶታል፡፡

በአማራ ክልል ከ40 በላይ ሆስፒታሎችን፣ 1 ሺህ 116 ትምህርት ቤቶች እና 46 የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ ውድመት ያስከተለው ጦርነቱ በአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች 12 ሚሊየን ህዝብ ገደማን ለተለያዩ ጉዳቶች መዳረጉ ነው የሚነገረው፡፡

የዚህ ጥናት የመጨረሻው ግብም በግጭት የሚፈጠሩ አውዳሚ ውጤቶችን በእውነተኛ ጥናት በማስቀመት ለተሻለ መፍትሄ መንገዶችን ማመልከት ነው ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አባተ ጌታሁን ናቸው፡፡

አውዳሚው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም ለሶስተኛ ዙር ተቀስቅሶ በመስፋፋት በቀጣይ ሊደርስ ለሚችለው ሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ስጋትን እንዳጫረ ያለእልባት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ