1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጥንታዊ ቤቶች ላይ ስጋት የደቀነዉ አዲስን የማስዋብ ፕሮጀክት

ሐሙስ፣ ሰኔ 4 2012

አንበሳ ፋርማሲ ይፈርሳል አልያም ይነሳል መባሉ ስጋት ቀስቅሶአል። ጀርመናዊዉ የመድሐኒት ቤቱ ባለቤት ይፈርሳል አልያም ከቤቱ ዉጡ እንደማይባሉ እምነት አላቸዉ ። እዉነት ያሸንፍል ባይም ናቸዉ።  ፍትሃዊ ዉሳኔም እንደሚሰጣቸዉ ሙሉ እምነታቸዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3deRK
Lion Pharmacy in Addis Ababa - Lion Apotheke
ምስል Fasika Kebede

አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጄክትና ሥጋቱ

የመፍረስ ወይም የመነሳት ስጋት ያጋጠመዉ አንበሳ ፋርማሲ ከተመሰረተ  75 ኛ ዓመቱን ይዞአል። የከተማዋ ነዋሪዎች የማምነዉን መድሃኒት መግዛት የምወደዉ ከዚህ መድሐኒት ቤት ነዉ ሲሉ ሌሎች ደግሞ፤ ለቆዳም የሚሆን መድሐኒት ይቀምማሉ ሲሉ አንበሳ መድሐኒት ቤት ምርጫቸዉ መሆኑን ብሎም ስለጥንታዊነቱ ታሪካዊነቱ እና ቅርስ መሆኑን ይናገራሉ።  

ቅርስ የአንድን ሃገር ታሪክን ባህልን ጠብቅቆ ወይም አቅፎ ከዘመን ዘመን የሚያሸጋግር ሰነድ ነዉ። ይህ ሰነድ ቅርሱ በተገኘበት ሃገር የሚኖር ማኅበረሰቡ፤ ዋጋ የከፈለበት የታሪክ የባህሉ አሻራም  እንደሆን ምሁራን የታሪክ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች ይናገራሉ። አዲስ አበባን ለማስዋብ በጀመረዉ ፕሮጀክት ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ ጥንታዊ ቤቶችን እንዲሁም ሱቆችን ሁሉ እንደሚያስፈርስ እየተነገረ ነዉ። አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘዉ አንበሳ ፋርማሲ ይፈርሳል መባሉ እንዳሳሰባቸዉ ብሎም እንዳሳዘናቸዉ የመድሐኒት ቤቱ ባለቤቶች መናገራቸዉን ከዘገብን በኋላ በመድሐኒት ቤት እየመጡ መታወቅያ አምጡ ፤ በሦስት ቀን ዉጡ የሚላቸዉ ሰዎች አንድ ጊዜ መምጣታቸዉን ከዝያም ከቤት ክራዮች ጋር ለስብሰባ ተጠርተዉ እንደነበር።  በጀርመናዉያን ሁለተኛ እና በሦስተኛ ትዉልድ እየተንቀሳቀሰ ያለዉ አንጋፋዉ አንበሳ መድሐኒት ቤት የመድሐኒት ሽያችና ቅመማ ብቻ ሳይሆን የመሕክምና ቁሳቁስ አስመጭና አገር ዉስጥ አከፋፋይም ነዉ። የድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ጀርመናዊዉ ካርል ሂልደብራንት ቤቱ ይፈርሳል አልያም ከቤቱ ዉጡ እንደማይባሉ እምነት አላቸዉ ። እዉነት ያሸንፍል ባይም ናቸዉ።  ፍትሃዊ ዉሳኔም እንደሚሰጣቸዉ ሙሉ እምነታቸዉ ነዉ።

በኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ 1950ዎቹ አጋማሽ  የአጼ ኃይለሥላሴ አማካሪ ዶክተር በነበሩት በጀርመናዊዉ ዴቪድ ሃን በኩል ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘመናዊ የመድሐኒት ቤት ለማቋቋም ከጀርመን ሃገር የመጡት ኩርት ሂልደብራንት የዛሬዉን የመድሐኒት ቤት በዋና ተጠሪነት የሚያገለግሉት ልጅ ካርል ኪልደበራንት ናቸዉ። ካርል ለመጀመርያ ጊዜ  ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር 1952 ዓም ነዉ ።  በስልክ መስመር መበላሸት ምክንያት ታሪካቸዉን በጽሑፍ ላኩልን።  ጊዜዉ ታህሳስ ግርግር በመባል በሚታወቅበት ጊዜ ነበር። በንጉሰነገስቱ ላይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉበት ወቅት ሲሉ ታህሳስ ግርግርን  ያስታዉሳሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ  ከትንሽ ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን ተመልሰዉም ነበር ። ዳግም በ 1957 ዓ.ም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ የሚገኘዉን መዘጋጃ ቤት ሲያስመርቁ ተገኝተዋል። ከዝያም ወደ ላይቤርያ ሄደዉ በላይቤሪያ በመኖር ላይ ሳሉ  ኢትዮጵያ ትዳር የመሰረተዉ ወንድማቸዉ ሰርግ ላይ ለመገኘት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በ 1959 ዓ.ም ተመልሰዋል። ከዝያም ነዉ ካርል ሂልደብራንት እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር  ከ 1959 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮአቸዉን የመሰረቱት። አባታቸዉ መድሐኒት ቤትም ማገልገል የጀመሩት።  እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1964 ይላሉ ካርል ሂልደብራንት ከቆንጆዋ ኢትዮጵያዊት እጮኛዬ ከሮዚ ከበደ ጋር ትዳር መሰረትን። ከሮዚ ጋር ሦስት ልጆችን አፈራን ፤ ሦስቱም ልጆቼ አሁን ከ 45 ዓመት እድሜ ክልል በላይ ናቸዉ። ሁለቱ ልጆቼ እዚሁ በማስተዳድረዉ መድሐኒት ቤትና የሕክምና ቁሳቁስ አስመጭዉ ድርጅት ዉስጥ አብረዉኝ ይሰራሉ። ከባለቤቴ ጋር በትዳር ዓለም ለ 45 ዓመት አብረን ቆይተናል ። ግን ባለቤቴ ሮዚ ከበደ በጣና ታማ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየችኝ  ሦስት ዓመት ሆንዋታል። የ 66 ዓመት ሴት ነበረች። ታላቁ ወንድሜ ክርስትያን  ሂልደብራንት ኢትዮጵያ መጥቶ ኮንቦልቻ ይገኝ በነበረዉ በንጉሰነገስቱ የመንገድ ባለስልጣን መስርያ ቤት ዉስጥ ይሰራ ነበር ። ግን ባቲ ዉስጥ የመኪና አደጋ አጋጠመዉና ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። የወንድሜ ሞት በቤተ ክርስትያን መዝገብ ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበ መሆኑም ይታወቃል።  የአሁንዋን አንበሳ ፋርማሲ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፋሲካ ከበደን  በጀርመን የፋርማሲ ሞያን እንድትከታተል  ወደ ጀርመን ልክያት ተምራ መጥታ ስራ ከጀመረች ስድስት ዓመት ሆንዋታል። ሟችዋ ባለቤቴ በደብረ ብርሃን የአቦ ቤተ ክርስትያን እድሳትን ጀምራ ነበር። አሁን እኔ እሱን ስራ አስቀጥዬ በእድሳቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንገኛለን።  ይህንን የባለቤቴን ስራ በማስቀጠሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ ምንም እንኳ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ባልሆንም ፤ ሁላችንም በአንድ በፈጣሪ እናምናለንና፤ ሲሉ ታሪካቸዉን በአጭሩ አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያንን በልቤ ይዣለሁ ለሃገሪቱ ፍቅር አለኝ ያሉን ካርል ሂልደብራንት፤ በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመን ኤምባሲ ለአንበሳ መድሐኒት ቤት ድጋፍ መስጠትን ይመለከታል በሚል ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከቲባ ኢንጂኔር ታከለ ኡማ በፃፈዉ ደብዳቤ አዲስ አበባን ብሎም ኢትዮጵያን የጀርመን የመዋለ ንዋይ ፍሰት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚያበራተታ አንድ ኤምባሲ ጉዳዩ ሕጋዊ መንገድን መከተል አለበት ብለን እናምናለን። ምክንያቱም በእድሜ ጠገቡ የአንበሳ መድሐኒት ቤት ላይ አስተዳደሩ ይወስዳል የተባለዉ ርምጃ ሌሎች የጀርመን ባለ ኃብቶችን ሊያሸሽ ይችላል ሲል ደብዳቤ ዉን ለአዲስ አበባ ምክትል ከቲባ ልኮአል። ኤንባሲዉ በደብዳቤዉ አያይዞም ኮቪድ 19 እየተዛመተ ባለበት በዚህ ወቅት ደረጃቸዉን የጠበቁ መድሐኒት ቤቶች በጣም አስፈላጊ መሆናቸዉን ግምት ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋልም ብሎአል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ