1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጣና ላይ አደጋ በገጠማት ጀልባ ሲጓዙ ከነበሩ የሰባት ሰዎች አስከሬን ተገኘ

ሰኞ፣ ሐምሌ 12 2013

በጣና ሐይቅ ላይ አደጋ በገጠማት ጀልባ ሲጓዙ ከነበሩ ሰዎች መካከል የሰባት ሰዎች አስከሬን ተገኘ። ሌሎች ስድስት የጀልባዋ ተሳፋሪዎች የደረሱበት አልታወቀም። ሐምሌ 9 ቀን አስራ ሶስት ሰዎች ጭና ከደንቢያ ወረዳ፣ አዲስጌ ድንጌ ቀበሌ ወደ ጎርጎራ በመጓዝ ላይ የነበረችው ጀልባ ምን እንዳጋጠማት የታወቀ ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/3whSX
Tanasee in Äthiopien
ምስል picture alliance/Peter Groenendijk/Robert Harding

ጀልባዋ ምን እንደገጠማት የታወቀ ነገር የለም

ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ ም ሌሊት 13 ሰዎች እና ለሽያጭ የተዘጋጀ ድንችና የጫነች አነስተኛ ጀልባ መነሻዋን ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ፣ አዲስጌ ድንጌ ቀበሌ ልዩ ስሙ አባን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ በማምራት ላይ ነበረች። ሆኖም እንደሌላው ጊዜ ወደ ወደቡ በሰዓቱ መድረስ አልቻለችም፡፡ 

የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ ትናንት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ጀልባዋ ሰዎችንና እቃዎችን ጭና ነበር አድራሻዋ የጠፋው፡፡

ምክትል ኮማንደር ቸርነት ዛሬ ዛሬ ረፋዱ ላይ በስልክ እንደገለፁልን ደግሞ ከበርካታ ጥረትና ፍለጋ በኋላ የ7 ሰዎች አስከሬን በጎርጎራና አዲስጌ ድንጌ በተባለ የገጠር ቀበሌ መካከል በሀይቁ ላይ በማእበል ተገፍተው ተንሳፈው ተገኝተዋል፡፡

የቀሪ 6 ሰዎችን እጣ ፋንታ ለማወቅም ከፍተኛ ፍለጋ እየተደረገ እንደሆነ ምክትል ኮማንደር ቸርነት ገልፀዋል፡፡ ጀልባዋ አደጋ ያጋጠማት ሰጥማ፣ በማዕበል ተገፍታ ወይስ በሌላ ሁኔታ የሚለውን የሚያጠና ቡድንም መቋቋሙን አመልክተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጣና ትራንስፖርት ባለስልጣና ባልደረባ ችግሩ ከጭነት በላይ መጫንና ካለሰዓት መነሳት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው ከዚህ በፊትም እንጨት የጫነ ጀልባ ሰጥሞ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡

አንዳንድ በሐይቁ ዙሪያ የሚሰሩ የጀልባ ትራንስፖርት ባለቤቶች አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በተደጋጋሚ አደጋ የሚደርስባቸው ጀልባዎች ቁጥጥር የማይደረግባቸውና ከሚገባው በላይ የሚጭኑትና ባልተፈለገ ሰዓት በሌሊት አገልግሎት የሚሰጡት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ