1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በ2022 የአውሮጳና ጀርመን ዐበይት ክንውኖች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2015

በርካታ አባላቱ ከሩስያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ትስስር ያላቸው የአውሮጳ ኅብረት ሩስያ ጦርነቱን እንድታቆም የወሰዳቸው የማዕቀብ እርምጃዎች ጦርነቱን ማብቃት ያልቻሉበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሩስያ አውሮጳን በፈለገችው አቅጣጫ ለመዘወር ከመሞከር ያልተቆጠበችበትም ዓመት ነበር 2022።

https://p.dw.com/p/4LSv3
Ukraine | Kriegsgeschehen in Mariupol,
ምስል Azov Battalion/AP/picture alliance

በጎርጎሮሳዊው 2022 የአውሮጳና ጀርመን ዐበይት ክንውኖች

ጎርጎሮሳዊው 2022 በአውሮጳ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የከፋ የተባለው የዩክሬኑ ጦርነት የተካሄደበት፣ ከኮሮና በማገገም ላይ የነበረው አውሮጳ በጦርነት ምክንያት ለልዩ ልዩ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች የተዳረገበት፣ በየጊዜው በሩስያ ላይ ሲጣሉ የነበሩ ማዕቀቦችም የተጠበቀውን ያህል ውጤት ያላስገኙበት ዓመት ነበር። ከጦርነቱ አስቀድሞ ሩስያ፣ ለኔቶ የፀጥታ ዋስትና ጥያቄዎችን አቅርባ ነበር። ጥያቄዎቹም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዩክሬንን በአባልነት ላለመቀበል ቃል እንዲገባ በአጠቃላይ ኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቭየት ኅብረት ግዛቶች እንዳይስፋፋ የሚያሳስቡ ነበሩ።በምዕራቡ ዓለምና በሩስያ መካከል ውዝግቡ መካረር የጀመረውና ውጥረቱም የተባባሰው የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን እንገንጠል ለሚሉ ራሳቸውን ራሰ ገዝ ሪፐብሊኮች ብለው ለሚጠሩት ዶኔትስክና ሉሃንስክ እውቅና ከሰጡና በአጸፋውም ምዕራቡ ዓለም በሩስያ ላይ ልዩ ልዩ ማዕቀቦችን ከጣለ ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር። በተደጋጋሚ ዩክሬንን የመውረር እቅድ የለኝም ስትል የከረመችው ሩስያ በጎርጎሮሳዊው የካቲት 24 ቀን 2022 ዓ.ም. ሳይታሰብ የጀመረችው ጦርነት አውሮጳን ላልተጠበቀ ችግር ዳርጓል። አሁንም የቀጠለው ጦርነት ካስከተላቸው ችግሮች ውስጥ የከፋው የኃይል ቀውስ ሲሆን በዚህ ሰበብ የተባባሰው የኑሮ ውድነት የሸቀጦችና የእህልና የልዩ ልዩ ምርቶች እጥረትና እጦት እንዲሁም ሌሎች ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችም ይጠቀሳሉ። 
በርካታ አባላቱ ከሩስያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ትስስር ያላቸው የአውሮጳ ኅብረት ሩስያ ጦርነቱን እንድታቆም  የወሰዳቸው የማዕቀብ እርምጃዎች ጦርነቱን ማብቃት ያልቻሉበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሩስያ አውሮጳን በፈለገችው አቅጣጫ ለመዘወር ከመሞከር ያልተቆጠበችበትም ዓመት ነበር 2022። 
ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ሞስኮ ላይ በርካታ ማዕቀቦች ተጥለውባታል። ይሁንና ሩስያን ለማንበርከክ ተብለው የተጣሉት ማዕቀቦች መልሰው የአውሮጳ ኅብረት አባላትን የሚጎዱ ማዕቀቦች ሆነዋል የሚሉ ወቀሳዎች ከአባል ሀገራት አሰንዝረዋል። የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን ኅብረቱ በሩስያ ላይ የጣላቸው 6 ዙር ማዕቀቦች የተጠበቀውን ውጤት አለማምጣት ብቻ ሳይሆን ውጤታቸው ተቃራኒ ነበር ሲሉ በይፋ ተችተው ነበር ።
«ማዕቀቦቹ ከአውሮጳ ኅብረት ይልቅ ሩስያን ይበልጥ ይጎዳሉ ብለው ነበር ያሰቡት፤ግን ይህ ስህተት ነው።ይበልጥ እኛን ጎድቶናል።ማዕቀቦቹ ጦርነቱን ያሳጥራሉ፤ሩስያን በማዳከምም ፈጣን ስኬት ያስገኛል ነበር ሃሳባቸው። ይህም አልሰራም፤ጦርነቱ አለመቀነሱ ብቻ ሳይሆን እየተራዘመ ነው የሄደው፤ማዕቀብ አልረዳም።በመጀመሪያ እግራችን ላይ ተኮስን ብዬ ነው የማስበው።አሁን ደግሞ የአውሮጳ ምጣኔ ሀብት በራሱ ሳንባዎች ላይ መተኮሱን በግልጽ እናያለን።ይህን አድርጎም ትንፋሹ እንዳያጥርበት በየቦታው እየተጣጣረ ነው።»
ሞስኮም ለማዕቀቦቹ አጸፋ ወደ አውሮጳ ትልከው የነበረውን ጋዝ መጠን በእጅጉ ቀነሰች፤ ወደ ጀርመን ጋዝ ያስተላልፍ የነበረውን ኖርድ ስትሪም አንድ የተባለውን መስመር በነሐሴ ለተወሰነ ጊዜ ዘግታ ነበር።ጀርመን ከጦርነቱ በፊት ከውጭ ከምታስገባው ጋዝ አንድ ሦስተኛውን ከሩስያ ነበር የምታገኘው። ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት የአውሮጳ ሀገራት ከሩስያ ጋዝ መግዛትእንዲያቆሙ ሲወተውቱ ጀርመንና መሰል የሩስያ ጋዝ ጥገኛ የሆኑ ሀገራት ግን ወዲያውኑ መስማማት አልቻሉም ነበር። ጀርመን አስተማማኝ አማራጭ የኃይል ምንጮችን እስከምታገኝ ድረስ መጠበቅ ነበረባት።በመካከሉ የኃይል ቀውሱ ተባብሶ የነዳጅና የጋዝ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል።ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች የቅጣት እርምጃዎች ለመውሰድ አስቀድሞ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሩስያ ከዓለም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ስዊፍት እንድትወጣ ተደርጓል፤ ኖርድ ስትሪም ሁለት የተባለው የሩስያ ጀርመን የጋዝ ማስተላለፊያ ቧምቧ ፕሮጀክትም ተቋርጧል 
ህይወት ያጠፋው፣ በርካታ ንብረት ያወደመውና ሚሊዮኖችን ያሰደደው የዩክሬኑ ጦርነት ፣ጀርመን የፖሊሲ ለውጥ እንድታደርግ ሰበብ ሆኗል።የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጀርመን ያልተጠበቀ የውጭና የመከላከያ ፖሊሲ ለውጥ አድርጋለች።የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ  ጀርመን ለዩክሬን ከምትሰጠው የጦር መሣሪያ  ድጋፍ በተጨማሪ  በ2022 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ዩሮ ለአገራቸው ጦር ሠራዊት ለመመደብም ቃል የገቡት የጀርመን ምክር ቤት በወቅቱ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ጀርመን ከአሁን በኋላ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 2 በመቶውን ለመከላከያ እንደምትመደብም ነበር ሾልዝ ለጀርመን ምክር ቤት ያሳወቁት።
የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን በድጋሚ የተመረጡት በ2022 ዓም በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ነበር። የ66 ዓመቱ ሽታይንማየር በ2021 ዓም መጨረሻ ላይ አዲሱን የጀርመን ጥምር መንግሥት የመሠረቱትን የሦስቱን ፓርቲዎችን ድጋፍ ካገኙ በኋላ ነበር በምክር ቤት አባላት እና ከተለያዩ የአገሪቱ ፌደራል ግዛቶች በተውጣጡ ተወካዮች ለተጨማሪ አምስት አመታት በፕሬዝደንትነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት። በምርጫው ሌሎች ሦስት ተወዳዳሪዎችም ተካፍለዋል። 
2022 በብሪታንያ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው የገነነው ቦሪስ ጆንሰን የስልጣን ዘመናቸውን ሳይጨርሱ በግፊት ከሃላፊነታቸው የተነሱበት ዓመት ነበር።በ2022 ዓም መስከረም መጀመሪያ ላይ ደግሞ የቀድሞዋ የብሪታንያዋ ንግሥት ግርማዊት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ አረፉ ። ንግሥቲቷ 70 ኛ ዓመት በዓለ ንግሣቸውን ካከበሩ ከሦስት ወር በኋላ ነበር ፣ባደረባቸው ህመም በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።  ከመሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት የቀድሞውን የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን የተኩትን ሊዝ ትረስን በመኖርያ ቤታቸዉ ተቀብለዉ የጠቅላይ ሚኒስትርት ሹመታቸውን አፅድቀው ነበር። 
ንግሥት ኤልሳቤጥ የብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ስርዓት ሲዳከም ምስክር ነበሩ፤ቀዝቃዛውን ጦርነት አልፈዋል። ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት ስትወጣ አይተዋል። የኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝንም አልፈው ነበር ።በስልጣን ዘመናቸው ከዊንሰተን ቸርቸል እስከ እስከ ሊዝ ትራስ ድረስ 14 ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል።ንግስቲቱ 
የቀድሞ የብሪታንያ ቅኝ ግዛቶች በተሰባሰቡበት ኮመን ዌልዝ ተብሎ በሚጠራው የጋራ ብልጽግና ማኅበር አማካይነት ያደረጉት አስተዋጽኦ ከሌሎች የሀገሪቱ ነገሥታት ልዩ እንደሚያደርጋቸው በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ ለዶቼቬለ ተናግረው ነበር
የንግሥት ኤልሳቤጥ ስርዓተ ቀብር መስከረም 19 ቀን 2022 ዓም ነበር የተፈጸመው። ከቀብራቸው  በፊት በዌስትሚንስተር አቢ ቤተ ክርስቲያን በተካሄደዉ የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ከ 400 በላይ የቀድሞ እና የአሁን የሀገር መሪዎች እና ተወካዮች ተገኝተው ነበር።  
ከንግሥቲቱ ሞት በኋላ በብሪታንያ ታሪክ የመጀመሪያው ትውልደ እስያዊው ሪሺ ሱናክ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቁ ። 57ተኛው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ሥልጣኑን እንደተረከቡ ባሰሙት ንግግር በብሪታንያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አንድነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ነበር። 
«ብሪታንያ ታላቅ ሀገር ናት።ሆኖም በጣም ጠንካራ ኤኮኖሚያዊ ፈተና እንደገጠመን አያጠራጥርም።አሁን መረጋጋትና አንድነት ያስፈልገናል።ፓርቲያችንንና ሀገራችንን አንድ ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት የምሰጠው  ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ይህ የተጋረጡብንን ፈተናዎች መወጫውና ፣ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የተሻለች ይበልጥ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት  ብቸኛው መንገድ ነው።  »
በብሪታንያ የስድስት ዓመት ታሪክ አምስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ፣የመጀመሪያው መሠረታቸው የውጭ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆኑ በብሪታንያ የ200 ዓመታት ታሪክ ወጣቱ መሪም ናቸው። የ44 ዓመቱ ሱናክ ተቃውሞና ግፊት ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ ለንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው የተሰናበቱትን የወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሊዝ ትራስን ነው የተኩት።  ትረስ ፣ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ከመሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ ስልጣን ላይ የቆዩት ለ44 ቀናት ብቻ ነበር።
ኢጣልያ በታሪኳ የመጀመሪያዋን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የሰየመችውም በዚሁ ባገባደድነው በ2022 ዓ.ም. ነው። ቀኝ ጽንፈኛ የሚባሉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅዮ ሜሎኒ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ ኢጣልያ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ለማስቆም በገቡት ቃል መሠረት ባለፈው ህዳር ወር በህይወት አድን መርከቦች እገዛ ከባህር አደጋ የተረፉ ስደተኞች ወደ ኢጣልያ እንዳይገቡ ጥብቅ እገዳ ጥለው ስደተኞች ሲንገላቱ ነበር።
የመሀል ፖለቲካ የሚያራምዱት ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ለተጨማሪ አምስት አመታት ፈረንሳይን ለመምራት በድጋሚ  የተመረጡት ባለፈው ሚያዚያ አጋማሽ ላይ ነበር። ማክሮ ተፎካካሪያቸውን ቀኝ አክራሪዋን ማሪ ለ ፔንን ያሸነፉት  ከተሰጡት ድምጾች  58 ነጥብ 5 በመቶውን አግኝተው ነበር። ባለፉት 20 አመታት የፈረንሳይ የምርጫ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ሆነዋል ማክሮ ። 
የጀርመን መንግሥት የሀገሪቱን የዜግነት ሕግ ለማሻሻል  በዝግጅት ላይ መሆኑን ያሳወቀው ባለፈው ወር ነበር። አሁን በሚሰራበት ሕግ የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ማመልከት የሚችሉት  ጀርመን ስምንት ዓመታት ከኖሩ በኋ ነው።በሕጉ መሠረት ከጥቂት ሀገራት ዜጎች በስተቀረ አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ጥምር ዜግነትም አይፈቀድላቸውም። የጀርመን መንግሥት ባረቀቀው አዲስ ሕግ ግን ለጀርመን ዜግነት ለማመልከት ጀርመን 5 ዓመት  መኖር ብቻ በቂ ይሆናል። በረቂቅ ደረጃ በተዘጋጀው ሕግ ጥምር ዜግነትም ይፈቀዳል ተብሏል። 
የጀርመን ፖሊስ በታህሳስ መጀመሪያ ላይ ነበር ከዓመት በላይ ባካሄደው ክትትልና በቅርቡም ባደረገው አሰሳ  የጀርመንን መንግሥት ለመገልበጥ በማሴር የተጠረጠሩ ያላቸውን ከ25 በላይ ራይሽስቡርገር የተባለው ንቅናቄ  አባላት ወይም ደጋፊዎች ማሰሩን ያሳወቀው።ለጀርመን ፌደራዊ መንግሥት ዕውቅና አይሰጡም ከተባሉት በአሸባሪነት ከተፈረጁት ከዚህ ቡድን አባላት ውስጥ ዳኛና የቀድሞ የጀርመን ፓርላማ አባል የቀድሞ የጀርመን ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል የቀድሞ የጦር ሰራዊትና የፖሊስ ባልደረቦች  ይገኙበታል። ናዚ ጀርመን ከተሸነፈበት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ለተመሰረተው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ እውቅና የማይሰጡት አሸባሪና ጽንፈኛ የተባሉት የዚህ ቡድኑ አባላት መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ ብቸኛ አማራጭ ኃይልን መጠቀም ነው ብለው ያምናሉ።  የጀርመን የሕገ መንግሥት ጥበቃ ቢሮ የሀገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት እንደሚለው የራይሽስቡርገር አባላት ቁጥር 21 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል። ከመካከላቸው አምስት በመቶው ደግሞ ቀኝ ጽንፈኛ ናቸው ተብሏል። ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት በሆኑ ይዞታዎች ባካሄደው አሰሳ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።

Festnahme  Heinrich XIII Prinz Reuß /Razzia Reichsbürger-Szene - Frankfurt
የራይሽስቡርገር ንቅናቄን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በመምራት የተጠረጠሩት ሃይንሪሽ 13 ተኛ ልዑል ሮይስ በፖሊስ ሲወሰዱምስል Boris Roessler/dpa/picture alliance
 Emmanuel Macron
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮምስል Thibault Camus/AP/picture alliance
Italien Ministerpräsidentin Giorgia Meloni
የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅዮ ሜሎኒ ምስል Roberto Monaldo/LaPresse/AP/picture alliance
UK Premierminister Rishi Sunak
57ተኛው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክምስል Jacob King/empics/picture alliance
Großbritannien Royals l Queen Elisabeth
የብሪታንያዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከልጃቸው ከአሁኑ ንጉሥ ቻልርስ ሳልሳዊ ጋር ምስል Reuters/V. Jones
Deutschland Bundespräsident Steinmeier mit Kissinger-Preis geehrt
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ምስል Julia Nikhinson/APPhoto/picture alliance
የጀርመን መራኄ mneግሥት ኦላፍ ሾልዝ በቡንደስታግ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ