1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የተገን ጠያቂዎች ችግሮች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 10 2010

ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች አብዛኛዎቹ ስለ ጀርመን የተገን አሰጣጥ  ህግ በቂ መረጃ ስለሌላቸው እና በተሰደዱበት ሀገር ያሏቸውን መብቶች ባለማወቃቸው ጀርመን ተረጋግተው እንዳይቆዩ ምክንያት እየሆነ ለዳግም ስደት እየዳረጋቸውም ነው። ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የሚሰጧቸው በግምት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችም ጉዳያቸውን እያበላሹባቸው ነው። 

https://p.dw.com/p/31cM0
Grenzen in Europa
ምስል picture-alliance/dpa

የኢትዮጵያውያን ተገን ጠያቂዎች ችግሮች

ጀርመን ጥገኝነት  የሚጠይቁ ወይም ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞች ለተለያዩ ችግሮች ይዳረጋሉ። ከመካከላቸው የመረጃ እጦት፣ጀርመንኛ ቋንቋን አለማወቅ ዋነኛዎቹ ናቸው። ወደ ጀርመን የተሰደዱባቸው መንገዶች ያሳደሩባቸው ተጽእኖዎች እንዲሁም እዚህ ከገቡ በኋላም የሚደርስባቸው መጉላላት፣ እና በሂደት የሚገጥሟቸው ልዩ ልዩ ስነ ልቦናዊ ችግሮችም ይገኙበታል። ለእነዚህ እና ተያያዥ ችግሮች ከሚዳረጉት መካከል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተጠቃሽ ናቸው። ስደተኞቹንም የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞች ለተለያዩ ጉዳዮች በሚሄዱባቸው መስሪያ ቤቶች በማስተርጎምና  የምክር አገልግሎት በመስጠት ይደግፏቸዋል። በዚህ ሥራ ከተሰማሩት መካከል ወጣት አብዲ አባጀበል አንዱ ነው። አብዲ በደቡብ ጀርመን በባየርን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ በሙኒክ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ይህን አገልግሎት የሚሰጥ የመንግሥት ሠራተኛ ነው። በተለይ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ጀርመን የተሰደዱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆነ ታዳጊ ወጣቶች የምክር አገልግሎት መስጠት መከታተል እና  ማስተርጎም ነው ዋናው ተግባሩ። አገልግሎቱን የሚሰጠውም በአካል  ብቻ ሳይሆን በስልክም ጭምር ነው። በዚህ ሥራ ከተሰማራ 6 ዓመት ሆኖታል። ቀደም ሲል  በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት ይህንኑ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። አብዲ እንደሚለው በተለይ ከዛሬ 5 ዓመት ወዲህ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞች አንዱ እና ዋነኛው ችግራቸው ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊትም ሆነ እዚህ ከገቡ በኋላ ሊጠብቃቸው ስለሚችለው ሁኔታ ምንም አለማወቃቸው ነው። ይህ የመረጃ እጦትም በርሱ አመለካከት መሠረታዊ ሊባል የሚችል ችግር ነው።በጀርመን ስደተኞችን የሚረዳ የተደራጀ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ አለመኖር እዚህ ከሚታዩ ጉድለቶች አንዱ ነው።
ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ አባዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ ጀርመንም ሆነ ወደ ተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የገቡት አደገኛ እና አሰቃቂ የበረሃ እና የባህር ጉዞ አልፈው መሆኑ በቀላሉ ለማይሽሩ ልዩ ልዩ ስነልቦናዊ ችግሮች አጋልጠዋቸዋል። በዚያ ላይ ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ መሆናቸው ሲጨመር በቋንቋ እጥረት እና የአንዳንዶቹም የተገን ጥያቄ ውድቅ ሲደረግ  የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ የሚወድቁ ጥቂት አይደሉም። አብዲ እንደሚለው በዚህ ምክንያት የከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሕይወታቸውንም ያጡ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ኤርትራውያን አሉ።
ይህን በመገንዘብ ነበር አብዲ  ስደተኞችን መርዳት የጀመረው። እነዚህ እና ሌሎችም «ከዐምሮየ ሊጠፋ ያልቻሉ»የሚላቸው በርካታ የስደተኞች አሳዛኝ ሁኔታዎች ሁሌም ይረብሹናል ይላል ለ16 ዓመታት ጀርመን የኖረው አብዲ። ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች አብዛኛዎቹ ስለ ሀገሪቱ የተገን አሰጣጥ  ህግ በቂ መረጃ ስለሌላቸው እና በተሰደዱበት ሀገር ያሏቸውን መብቶች ባለማወቃቸው ጀርመን ተረጋግተው እንዳይቆዩ ምክንያት እየሆነ ለዳግም ስደት እየዳረጋቸውም ነው እንደ አብዲ። ከዚህ ሌላ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የሚሰጧቸው በግምት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችም ጥያቄአቸው ተቀባይነት እንዳያገኝ ምክንያት እየሆኑ ነው። 
ለስደተኞች የምክር አገልግሎት የሚሰጠው አብዲ ከዚህ በመነሳት ተገን ጠያቂዎች  አስቀድመው ሊያውቋቸው እና ሊዘጋጁባቸው ይገባሉ ያላቸውን ጉዳዮች እንዲሁም ሊወስዱ ይገባቸዋል ያላቸውን ጥንቃቄዎችም በምክር መልክ አስተላላፏል።ሳምንት ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተሞክሮዎች ጋር እንመለስበታለን።

Migration aus Afrika in der Nähe der Stadt Gohneima, Lybien
ምስል picture-alliance/dpa/AP/Küstenwache Lybien
Deutschland - Äthiopische Flüchtlinge
ምስል DW/E. Bekele

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ