1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን አንድነት ተከበረ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 24 2010

እርቁ ከተከናወነ ማግስት ጀምሮ የሁለቱንም ፓትርያሪኮች አባትነት እንቀበላለን። ሁለትነትን የፈጠረዉ ያ ስልጣን ይዞ የነበረዉ መንግሥት ነዉ። ሁለቱም የቤተ-ክርስትያናችን አባቶች ናቸዉ። ይህ ታሪክ የፈጠረዉ ስለሆነ፤ ይህን ቤተ-ክርስትያንን እናከብራለን ብለን ካህናቱንም ሊቃዉንቱንም አባቶችንም አሰባስበን እናክብር በሚል አክብረናል።

https://p.dw.com/p/343yW
Deutschland Treffen der beiden Synoden der äthiopisch-orthodoxen Tewahdo-Kirche in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse Hahn

የሁለቱንም ፓትርያሪኮች አባትነት እንቀበላለን

«አገር ቤት ያለዉ የሰላም ንፋስ እግዚአብሔር በነ ዐብይ በነ ለማ ለየት ባሉ ኢትዮጵያዉዊነት ከሚሰማቸዉ ሰዎች የመጣልን ሠላም እግዚአብሔር እስከ መጨረሻዉ የሁልጊዜም ምኞታችን ነዉ። »  

በፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ካህን መሪ ጌታ ብሥራት ካሳሁን የተናገሩት ነዉ። እዚህ ፍራንክፈርት ጀርመን የሚገኘዉና ቀደም ሲል ገለልተኛዉ የሚል መጠርያ የነበረዉ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስትያን ነሐሴ 18 እና 19 ታላቅ የምስጋና መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሂዱዋል። እጅግ ደማቅ በነበረዉ በዚህ  ዝግጅት ላይ በስቶክሆልም ስዊድን ነዋሪ የሆኑት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን የአዉሮጳና የአፍሪቃ ሃገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን የመላዉ አዉሮጳ  ጳጳስ ሆነዉ የተሾሙት፤ ብፁዕ አቡነ ድዮናስዮስ፤ የምስራቅ ወለጋ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል ፤ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ኃላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ፤ እንዲሁም በፍራንክፈርት የምስካኤ ዙናን መድሐንያለም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ መላከ መዊ ልሳነ ወርቅ ዉቤና ሌሎች በርካታ የሃይማኖት አባቶች ካህናት ዲያቆናት እና ወደ ሰባት መቶ የሚሆኑ ምዕመናን ተገኝተዋል።  በሊቃዉንት ሥርዓተ ማኅሌት፤ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ኪዳን እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ መርሃ ግብሮች ተከናዉነዋል። የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት ሕጻናት መንፈሳዊ ጉባኤዉን ከአደመቁት መካከል ነበሩ ።

Deutschland Treffen der beiden Synoden der äthiopisch-orthodoxen Tewahdo-Kirche in Frankfurt
ምስል DW/A. Tadesse Hahn

የምስጋና መንፈሳዊ ጉባዔዉ የተካሄደበት በፍራንክፈርት የሚገኘዉ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስትያን ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ ከመሆናቸዉና በቤተ -ክርስትያኒቱ ላይ የሰላም ንፋስ ከመንፈሱ በፊት ገለልተኛዉ እንደሚባል የነገሩን የቤተክርስትያኒቱ አስተዳዳሪና አገልጋይ ቆሞስ አባ ስብሃት ለአብ፤ ጥንታዊትዋ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን አንድነትን በማግኘትዋ ምዕመኑ ካህናቱ ሁሉ መደሰታቸዉን ተናግረዋል።  

«ቤተ-ክርስትያናችን ከተመሰረተ ወደ ስምንት ዓመት ሆኖታል። ለ 27 ዓመታት በዉጭ የነበሩ ፓትርያሪክ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ይህን እድል በመጠቀም እናም የመጀመርያዎቹ ሆነን ይህን ብስራት፤ የሰላም፤ የአንድነት፤ የምስጋና  ጉባኤ ብለን አዘጋጀን።  ዋናዉ ትልቁ ነገር ፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ቦታቸዉ ሲመለሱ ያልተደሰተ የቤተ- ክርስትያኒቱ ሰዉ የለም። ለመላዉ ኢትዮጵያዊ ልዩ ታሪክ ነዉ የሆነዉ። ይህን ታሪክ ደግሞ እግዚአብሔር ፈቅዶ እዚህ ለማክበር እና ጀማሪዎች ሆንን። የተጠሩት አባቶች ሁሉም መተዋል ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ ለእርቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ነበሩ።»

እዚህ ጀርመን በሚገኘዉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ -ክርስትያን ኢትዮጵያዉያን ብቻ ናቸዉ ወይስ የሌላ አገር ዜጎችም ይካፈላሉ?

The reunion of the two Synods of the Ethiopian Orthodox Church
ምስል DW/Fitsum Arega _Chief of Staff, Prime Minister Office, Ethiopia

« ቤተ-ክርስትያኒቱ በምታዘጋጀዉ በዓል ላይ ብዙዎች ተሳትፈዋል። በመሠረቱ ቤተ-ክርስትያኒቱ ዓለም አቀፋዊት ናት። እዚህ እኛ ቤተ-ክርስትያን ዉስጥ ክርስትና የተነሱ ጀርመኖች አሉ። ሌላ የሃይማኖት ተከታዮችም ይመጣሉ። እኛ አሁን የምንጠቀምበት ቤተ-ክርስትያን የሰርቢያ ቤተ ክርስትያን ነዉ። ሰርብያዎችም ተጠርተዋል። ግሪካዉያንም መጥተዉ ነበር ፤ በፀሎት ጊዜም ወደኛ ይመጣሉ። ኤርትራዉያንም ቤተክርስትያኑ ሲመሰረት ጊዜ አንስቶ ከኛዉ ጋር ሆነዉ ሲገለገሉበት ነበር ። አሁንም ከኛዉ ጋር ናቸዉ። ያካሄድነዉም ጉባኤ እነዚህን ሁሉ ነዉ ያስተናገደዉ።       

በአዉሮጳ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን የኛ ትንሽ ለየት ያለ ነበር ያሉን በፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ካህን መሪ ጌታ ብሥራት ካሳሁን በበኩላቸዉ፤ « አዎ ምክንያቱም ስርዓቱ አገር ቤት ባለዉ  የፀሎት ሥነ ስርዓት እና ሲኖዶስ ይመራል የሚል ሕግ ነበር የነበረዉ። ግን የአባቶችን ስም አይጠራም፤ በተለይ በአገር ቤት ያሉት አባት በመንግስት እየታገዙ ነዉ እና አባትነታቸዉን በትክክል አልተወጡም በሚል ስም አንጠራም ነበር። አሁን ግን እርቁ ከተከናወነ ማግስት ጀምሮ የሁለቱንም ፓትርያሪኮች አባትነት እንቀበላለን ። ሁለትነትን የፈጠረዉ ያ ስልጣን ይዞ የነበረዉ መንግሥት ነዉ ። ሁለቱም የቤተ-ክርስትያናችን አባቶች ናቸዉ። ይህ ታሪክ የፈጠረዉ ስለሆነ ይህን ቤተ-ክርስትያንን እናከብራለን ብለን ካህናቱንም ሊቃዉንቱንም አባቶችንም አሰባስበን እናክብር በሚል አክብረናል። ይህ ክብረ በዓል በአዉሮጳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ፈር ቀዳጅ ነዉ።»

በዝግጅቱ ላይ ምን የተለየ ነገር ነበር?

« የነበረዉ ለየት ያለ ነገር የቤተ-ክርስትያኒቱ ልዩነት ሲያስጨንቀዉ የነበረ ምዕመን ነበረ። አባቶችን አስመጥተን በተለይ ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ከስዊድን መምጣታቸዉን ብዙ ሰዉ ይናፍቅ ነበረ። ብፁዕ አቡነ ድዮናስዮስ፤ እንዲሁም ብፁዕ ብአቡነ ናትናኤል እንዲሁ ያልተጠበቁ ግን ፈጣሪ ወደኛ የላካቸዉ እንግዶቻችን ነበሩ።  

አብዛኛ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት በዐብይ ዘመን ቂምን ትቶ በመሃል የቆመ ግንብ አፍርሶ መደመር ብቻ ነዉ። የመላዉ አዉሮጳ ጳጳስ ሆነዉ የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ድዮናስዮስ እንዳሉት ያከበርነዉ በዓል እስከ ዛሬ ገለልተኛ ሆኖ የቆየዉን የፍራንክፈርቱን ቤተ-ክርስትያን በአንድ ሲኖዶስ ስር መሆኑን ለማወጅ ነዉ።  

በፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል በተካሄደዉ ደማቅ መንፈሳዊ ጉባኤና በዓል እጅግ መደሰታቸዉን የተናገሩት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኃላፊ እና በኮለኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ናቸዉ። የኮሎኙ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያን በአዉሮጳ ከተቋቋሙት ቤተ-ክርስትያናት ሁሉ፤ የመጀመርያና እና ፋና ወጊም ሆና ቆይቷል። ከትምህርት በኋላ ይህን ቤተ-ክርስትያን ያቋቋሙት ሊቀ ካህናት መርዓዊ ክፍፍሉ ትልቅ ጫና እንደነበር ተናግረዋል።  

የሁለቱን ሲኖዶሶች የ 27 ዓመታት የልዩነት ጉዞ ለመቋጨት መሽምግልና በማደራደር ተሳታፊ የነበሩት ብሎም የዛሬ 27 ዓመት ፓትሪያርኩን ወደ ኬንያ ይዘዉ የተሰደዱት መላከ መዊ ልሳነ ወርቅ ዉቤ በፍራንክፈርት የምስካኤ ዙናን መድሐንያለም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ናቸዉ። በፍራንክፈርት የሚገኘዉ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስትያን  ከተቋቋመ 8 ዓመት ሆነዉ ያሉን የቤተክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ  ቆሞስ አባ ስብሃት ለአብ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ለእርቀ ሰላሙ ጥረት ያደረጉትን ሁሉ አመስግነዋል።

Deutschland Treffen der beiden Synoden der äthiopisch-orthodoxen Tewahdo-Kirche in Frankfurt
ምስል DW/Fitsum Arega _Chief of Staff, Prime Minister Office, Ethiopia

የቤተ-ክርስትያኒቱ ወደ አንድነት መምጣትዋ ጉዳይ ጀምርነዉ እንጂ ገና ብዙ ይጠብቀናል ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የመላዉ አዉሮጳ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድዮናስዮስ በዉጭ ያለነዉ ምዕመናን ይበልጥ ለመቀራረብ መስራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

«እንግዲህ አሁን በአባቶች ደረጃ የነበረዉ ልዩነት ጠፍቶአል ። አንድ ሲኖዶስ ነዉ ያለን። ከአሁን በኋላ ግን ይህ የተጀመረዉ አንድነት የበለጠ እንዲጠነክር ፤ ልዩነቱ ገዝፎ ይታይ የነበረዉ በዚሁ በዉጭ ሃገር ስለነበረ ፤ ያ ልዩነት ጨርሶ እንዲጠፋ የከፋፈለንን ነገር ሁሉ እየተዉን የሚያቀራርበንን አንድ የሚያደርገንን የሚያስተባብረንን ነገር እንድናደርግ በዚህ አጋጣሚ ላሳስብ እወዳለሁ። ቃለ ምልልስ የሰጡንን አባቶች በዶይቼ ቬለ ስም እናመሰግናለን።  

የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉዉን ቅንብር እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ