1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመኑ ታዋቂ ሆቴል ዋና ምግብ አብሳዩ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 27 2013

ሕይወት የኑሮ ግብ ግብ መድረክ ናት በኑሮ ዉጣ ዉረድ ዉስጥ ደስት ሐዘን ማግኘትና ማጣት መዉደቅ እና መነሳት ድል አድራጊነት እና ተረቺነት እምነት እና ክህደት ወዘተ በየትኛዉም ጊዜ እና ቦታ ያጋጥማል። ዋናዉ ቁም ነገር በተስፋና በጽናት ሰርቶ ድል ማድረግ ነዉ። ኑሮ ትግል ነዋ። በርትቶ የሰራ ከሕይወት አዝመራ የድል ፍሬ ያፍሳል።

https://p.dw.com/p/3zoN0
Bilder von Anteneh Defabachew, Flüchtling aus Äthiopien
ምስል privat

የኢትዮጵያዉ ዲፕሎማዬ እና የሥራ ልምዴን በጀርመን ተቀባይነት አግኝቶ ዲፕሎማዉን ሰጥተዉኛል

«አንተ ብዙ ትምህርት ነዉ ያለህ፤ በወረቀት የያዝካቸዉ መረጃዎችህም ብዙ ናቸዉ፤ ጀርመንኛ ጥሩ ትናገራለህ ፤ ለምን የተማርከዉን ሞያ እንደገና ትማራለህ? የትምህርት መረጃዎችን በሙሉ ሰብስበን ወደ ጀርመን የሞያ ጉዳይ መረጃ ማጣርያ ቦታ እንላከዉ እና ተቀባይነት ካገኘህ ጥሩ ነዉ እንሞክር እድላችንን ተባለ። የትምህርት ማስረጃዎቼን በሙሉ ላኩ። ከዝያም ከሁለት ወር በኋላ መልስ ላኩልኝ፤ የላከዉን መረጃዎች በሙሉ ትክክለኛ ስለሞሆናቸዉ ወደ ኢትዮጵያ ልከን እናጣራለን አሉ። አጣሩ፤ ትክክለኛ መሆኑን አወቁ እና ፈተና ፈተኑኝ። ከዝያም   ከሦስት ወር በኋላ የጀርመንን ሃገር ዲፕሎማ ላኩልኝ። የኢትዮጵያዉ ዲፕሎማዬ እዚህ በጀርመንም እኩል እንደሚሰራ የሚያረጋግጥ ፤ የጀርመን ዲፕሎማ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የተማርኩት የዓለም አቀፍ የምግብ አዘገጅነት ነዉ»   

Bilder von Anteneh Defabachew, Flüchtling aus Äthiopien
ምስል privat

አንተነህ ድፋባቸዉ ይባላል። በጀርመን ባቫርያ ግዛት ዉስጥ በሚገኝ ባለ አምስት ኮከብ ታዋቂ ሆቴል በዋና ምግብ አስብሳይነት ተቀጥሮ እየሰራ ነዉ። አንተነህ ምግብ አብሳይነትን የተማረዉ በኢትዮጵያ ነዉ። በኢትዮጵያ ሳለም በአፍሪቃ ኅብረት ዋና ፅፈት ቤት ማዕድ ቤት ዉስጥ ጨምሮ ታዋቂ በሚባሉ በተለይ በዉጭ ዜጎች በሚጎበኙ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ዉስጥ አገልግሎአል። አሁን ደሞ በጀርመን። እዚህ እስኮደርስ ግን ብዙ ዉጣ ዉረዶችን አይቶአል። የሰዉ ልጅ በህይወት ዘመኑ በተለያዩ መንገዶች ያልፋል። ሁሉም ሰዉ የሚያልፍበት የሕይወት ጎዳና ፈተናዉና ስኬቱም የአንዱ ከሌላኛዉ ይለያል። ሰዎች ኑሮ ከበደኝ እያለፍኩት ያለዉ ፈተና ከአቅሜ በላይ ነዉ…. የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚሰማቸዉ ከሆነ ይህን የመከላከያዉ አንዱ መንገድ፤ የሌሎችን የሕይወት ዉጣ ዉረድ መስማት እና ማንበብ ብዬ  አምናለሁ ሲል አንተነህ ድፋባቸዉ የሕይወት ታሪኩን በመጽሐፍ መልክ አቅርቦአል። ታዋቂዉ ምግብ አብሳይ አንተነህ ድፋባቸዉ ይህን ችግር አላልፈዉም ከዚህ በላይ መቋቋም የምችለዉ መከራ የለም፤ በቃን ለምንል ሰዎች፤ የተለያዩ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸዉ ሰዎች ያለፉበትን የኑሮ ዉጣ ዉረድ እና ድል ስንሰማ ስናነብ እና ስንመለከት የሕይወት ስንቅና ብርታት ይሆነናል የሚልም እምነት እንዳለዉም አንተነህ ይገልፃል። አንተነህ በሕይወቱ ያየዉን ዉጣ ዉረድ፤ ብሎም ስኬት ሸክኖ በመጽሐፍ መልክ ሲያቀርብ፤ ብዙ ጊዜ በተለይ በልጅነት በወጣትነት ያሳለፍኩትን የሕይወት ዉጣ ዉረድ መዉደቅ እና መነሳት፤ ተስፋ ማጣት እና ተስፋ ማድረግ ለመጻፍ ጉጉት ነበረኝ እግዚአብሔር ፈቅዶ አሁን ምኞቼ በዚህ መልኩ እዉን ሆኗል ይላል። የአንተነህ ድፋባቸዉ የሕይወት ታሪክ በመቀጠል በጀርመኑ የባህል ማዕከል ጎተ ተቋም በኩል በጀርመንኛ እየተተረጎመ ነዉ።    

« ዉልደቴ እና እድገቴ አዲስ አበባ ነዉ። ጀርመን ሃገር በስደት የመጣሁት በጎርጎረሳዉያኑ 2013 መጨረሻ 2014 መጀመርያ ላይ ነዉ። ጀርመን ስኖር ስምንት ዓመት አካባቢ ሆኖኛል። ጀርመን ከገባሁ በኋላ እንደማንኛዉም ስደተኛ ጥገኝነት ጠይቄ ፤ ስኖር፤ ፈቃድ አላገኘሁም። ምክንያቱም ወደ አዉሮጳ ስመጣ መጀመርያ የገባሁት ስፔን በመሆኑ ስፔን መመለስ ነበረብኝ። ይሁንና ጀርመን ዉስጥ አንድ ቤተ ክርስትያን አግኝቼ ጠለላ ሰጡኝ ፤ ቤተ ክርስትያኑ ዉስጥ ፖሊስ መጥቶ እኔን መያዝ ስለማይችል፤ የትም ሳልወጣ ቤተ ክርስትያን ዉስጥ ብቻ አንድ ዓመት ተኩል ኖርኩ።በቆይታዬ የጀርመንኛ ቋንቋን ጠንቅቄ ተማርኩ....»

Bilder von Anteneh Defabachew, Flüchtling aus Äthiopien
ምስል privat

አንተነህ ወደ አዉሮጳ ሲሰደድ መጀመርያ ያረፈዉ ስፔን አገር በመሆኑ ጀርመን መቆየት ፈቃድ አልነበረዉም፤ በዚህም ነዉ በጀርመን ቤተክርስትያን ዉስጥ መጠለያ አግኝቶ ወደ አንድ ዓመት ተኩል ከቤተክርስትያኑ ተጠልሎ የቆየዉ ። እንደተናገረዉ እዝያም ጀርመንኛን መናገርና መጻፍን ጠንቅቆ ተማረ። በአሁኑ ወቅት ማሪቲም በሚባል ታዋቂ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ዉስጥ በምግብ አብሳይነት ይሰሰራል። በሆቴሉ ስራን ያገኘዉም ምንም አይነት ተጨማሪ ስልጠና ሳያስፈልገዉ ነበር ።

« ኢትዮጵያ  የተማርከዉ የዓለም አቀፍ ምግብ አብሳይነት ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያገኘሁት ዲፕሎማዬ ፤ እዚህ በጀርመን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አገኘ።  ፋታ በማይሰጠዉ የጀርመን ሃገር የስራ ባህል፤ ጊዜ አግንቼ ለመፃፍ የበቃሁት፤ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት በጀርመን እጅግ ጨመረና ሆቴሎች ሁሉ በመዘጋታቸዉ እና ከስራ ይልቅ ቤት በመዋላችን ነዉ ። መጽሐፉን ለመጻፍ ወደ አራት ወር ግድም ወስዶብኛል። የሕይወት ታሪኬን ሌላ ሰዉ እንዲያነበዉ የፈለኩት ለሌላዉ ትምህርት ይሰጣል፤ ጥንካሪንም ሊቸር ይችላል፤ ምክንያት ለሚሰጡ ሰዎች ምክንያት መስጠቱ መፍትሄ እንዳልሆነ ያሳያል ብዬ ስለማምን ነዉ»

ሕይወት የኑሮ ግብ ግብ መድረክ ናት በኑሮ ዉጣ ዉረድ ዉስጥ ደስት ሐዘን ማግኘትና ማጣት መዉደቅ እና መነሳት ድል አድራጊነት እና ተረቺነት እምነት እና ክህደት ወዘተ በየትኛዉም ጊዜ እና ቦታ ያጋጥማል። ዋናዉ ቁም ነገር በተስፋና በጽናት ሰርቶ ድል ማድረግ ነዉ። ኑሮ ትግል ነዋ። በርትቶ የሰራ ከሕይወት አዝመራ የድል ፍሬ ያፍሳል። አንተነህ የብርቱ ጽናት ዉጤት ነዉ። ግለ ሕይወት ታሪኩን ስናነብ ከጥረቱ እና ከግልፀኝነቱ አያሌ ፋይዳዎችን እናገኛለን፤ ሲሉ  መምህር እና ደረሲ ኃይለመለኮት መዋዕል መጽሐፉን አንብበዉ ካስከመጡት አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ስደተኛዉ ሼፍ የተሰኘዉ በጀርመን ማሪቲም በተሰኘ አምስት ኮከብ ሆቴል ታዋቂ አብሳይ የሆነዉ መጽሐፍ ሰሞኑን፤ በጎተ ተቋም በኩል በጀርመንኛ እየተተረጎመእንደሆን አንተነህ ድፋባቸዉ ነግሮናል።  ተሞክረሮዉን ያካፈለንን አቶ አንተነህ ድፋባቸዉን በማመስገን ሙሉዉን ዝግጅት እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ