በድሬዳዋ 21 የጤና ባለሙያዎች በሥራቸው ላይ ሳሉ በኮሮና መያዛቸውን አስተዳደሩ አስታወቀ
ሰኞ፣ ሐምሌ 27 2012በድሬደዋ የኮሮና በሽታ ስርጭት አሁን ባለበት ደረጃ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን የመስተዳድሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል አስገዳጅ መመሪያዎችን ማስተግበር እና የእንቅስቃሴ ገደብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንድ የጤና ባለሞያ ተናግረዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ይዘሮ ለምለም በዛብህ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ባለው መዘናጋት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱንና ድሬደዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ከፍተኛ ስጋት ያለባት ከተማ ሆናለች።
በአስተዳደሩ አቅም በፈቀደ መልኩ እየተካሄደ ባለው የኮቪድ ምርመራ ቫይረሱ እየተገኘባቸው ካሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን ኃላፊዋ አስረድተዋል።
የጤና ባለሞው ዶክተር አቤል መልካሙ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት አስተያየት “የመመርመር እቅም ዝቅተኛ መሆን እንጂ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል” ጠቅሰው መደረግ አለበት ያሉትን አስተያየት ሰተዋል።
ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤት የኮሮና ስርጭት ስጋት ናቸው መባሉን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በፖሊስ ጣቢያዎች የጥንቃቄ አሰራር ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ገልፀው በማረሚያ ቤት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር እየተሰራ ያለውን ስራ ጠቁመዋል።
በአስተዳደሩ እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው አምስት መቶ ሰባ አምስት ሰዎች አስራ አምስቱ ህይወታቸው ማለፉን፤ አራት መቶ ሃያ አምስት የሚሆኑት አገግመው መውጣታቸውንና በአሁን ሰዓት አንድ መቶ ሰላሳ ሶስት የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ ህክምና ማዕከላት ውስጥ መኖራቸውን ወ/ሮ ለምለም በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡
መሳይ ተክሉ
ነጋሽ መሐመድ