1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በድሬደዋ ግምብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ተንዶ ሶስት ህፃናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ሞቱ

እሑድ፣ ሚያዝያ 24 2013

በድሬደዋ ግምብ ሶስት መኖሪያ ቤቶች ላይ ተንዶ ዘጠኝ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። አደጋው ከመድረሱ በፊት በከተማው ከባድ ዝናብ ሲጥል ነበር። ከሟቾች መካከል የሶስት ወር ጨቅላ፣ የሁለት አመት እና የአምስት አመት ሕፃናትም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሟቾቹ መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3srpc
Äthiopien Unfall in Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

በድሬደዋ ከተማ በዛሬው ዕለት ለሰዓታት ከባድ ዝናብ በመጣሉ በድንጋይ የተሰራ ግምብ ከመኖሪያ ቤቶች ላይ ተንዶ ዘጠኝ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። ከሟቾች መካከል የሶስት ወራት ዕድሜ ያለው ጨቅላን ጨምሮ ሶስት ሕፃናት ይገኙበታል። ግምቡ ከተናደባቸው ሶስት መኖሪያ ቤቶች በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው የለም።

የዶይቼ ቬለ የድሬደዋ ወኪል መሳይ ተክሉ እንደዘገበው አደጋው ከመድረሱ በፊት በከተማዋ ከማለዳ ጀምሮ ከባድ ዝናብ ሲጥል ነበር። በድሬደዋ ፖሊስ መረጃ መሠረት አደጋው የደረሰው በከተማው 03 ቀበሌ ሸመንተሪያ ተብሎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ወይም በቀድሞው የስሚንቶ ፋብሪካ ዙሪያ ነው።

በሶስት መኖሪያ ቤቶች ላይ የተናደው እስከ 50 ሜትር የሚደርስ ባሻንፈር ትሬዲንግ የተባለ የአንድ የግል ድርጅት የአጥር ግምብ መሆኑን የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

Äthiopien Unfall in Dire Dawa
በአደጋው ዘጠኝ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።ምስል Messay Teklu/DW

"የባሻንፈር ትሬዲንግ ይዞታ የሆነ እስከ 50 ሜትር የሚገመት የግምብ አጥር ከሥር የነበሩ ሶስት መኖሪያ ቤቶች ላይ ፈርሶ በመውደቁ፤ በሶስቱ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል" ሲሉ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ ተናግረዋል።  

ከሟቾች መካከል የሶስት ወር ጨቅላ ይገኝበታል። የሁለት አመት ገደማ እና ሌላ የአምስት ሕፃናትም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሟቾቹ መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው።

Inspector Bantalem Girma Dire Dawa Police
የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ ምስል Messay Teklu/DW

ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም እንዳሉት ግምቡ ሲደረመስ በመኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

"የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አደጋው እንደደረሰ በሥፍራው ያሉ ፖሊሶች እና አጠቃላይ ከዋናው መምሪያ ጭምር የየአድማ ብተና እና ዋናው ኃይላችን በሥፍራው ተንቀሳቅሶ ሕይወት ለማትረፍ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ምክንያቱም የአጥር ግምቡ የድንጋይ እና የብሎኬት እንደመሆኑ ክብደት ያለው ነው። ቤቶቹን ሙሉ በሙሉ ነው ያፈረሰው" ብለዋል።

በሶስቱ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ሰዎች "ወዲያው አደጋው እንደተከሰተ ሕይወታቸው አልፏል" ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም የአካባቢውን ማሕበረሰብ በማስተባበር ድንጋዩን በማንሳት የሟቾች አስከሬን እንዲወጣ መደረጉን አስረድተዋል።

Äthiopien Unfall in Dire Dawa
ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ቀሪው የግንቡ አካል ተመሳሳይ ስጋት ያለበት በመሆኑ ፖሊስ መፍትሔ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።ምስል Messay Teklu/DW

"አደጋው የደረሰበት ቦታ ላይ ይኸ ድርጅት ለማልማት ወስዶ ረዥም ጊዜ ታጥሮ የቆየ ቦታ ነው። አሁንም ቀሪ የግምቡ ክፍሎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሟቸው በዙሪያው ባሉ ቤቶች ላይ ጉዳቶች እንዳይደርሱ" ፖሊስ እየሰራ መሆኑን የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት በከተማው ከባድ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል አመላካች የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ወጥተው እንደነበር መሳይ ተክሉ ዘግቧል።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ