1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት ለመግታት ያስችላል የተባለ ዘመቻ መጀመሩን፡፡

ሐሙስ፣ ግንቦት 11 2014

ከሩብ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሸታ የተጠቁበት የደቡብ ክልል የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት ያስችለኛል ያለውን የህዝብ ንቅናቄ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

https://p.dw.com/p/4BYvi
Äthiopien | Malaria Berater Henok Bekele
ምስል S. Wegayehu/DW

ወባን የመከላከል ዘመቻ በደቡብ ክልል

በደቡብ ክልል ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ ስርጭቱን እያሰፋ የመጣው የወባ በሽታ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገራል፡፡ በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት ታመው ወደ ተለያዩ የምርመራ ማዕከላት ከመጡት ህክምና ፈላጊዎች መካከል 242ሺህ ያህሉ የወባ በሽታ ተጠቂ ሆነው መገኘታቸውን  ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቢሮው የበሽታዎች መከላከልና ጤና ማጎለበት ዳይሬክቶሬት የወባ ማስወገድ አማካሪ የሆኑት አቶ ሔኖክ በቀለ አሁን ባለው ሁኔታ ክልሉ 28 በመቶ የሚሸፍን ሀገራዊ የወባ ስርጭት የሚታይበት አካባቢ ሆኗል ብለዋል፡፡

በክልሉ በከምባታ ጠምባሮ ፣ በሀዲያ ፣ በወላይታ ፣ በጋሞ ፣ በጎፋ ዞኖችና በባስኬቶ ልዩ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ 34 ወረዳዎች የበሽታው ስርጭት ጎልቶ የሚታየበቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

በአነኝሁ አካባቢዎች በየሳምንቱ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ እየተጠቁ እንደሚገኙ  ነው  ባለሙያው የጠቀሱት ፡፡

ቀደም ሲል ከጤና ሚኒስቴር ይቀርብ የነበረው  የአልጋ አጎበር ፣ የፀረ ወባ መድሃኒት መርጫ ኬሚካል መዘግየትና የህብረተሰቡ በሽታውን የመከላከል ጥረት መቀዛቀዝ ለበሽታው ስርጭት ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከል የጤና ማጎለበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሌ ማቴ በበኩላቸው ክልሉ ካለው መልከአምድራዊ አቀማመጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ለወባ በሽታ ተጋላጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አሁን የሚታየውን የወባ በሽታ ስርጭት ባለበት ለመግታትና በሂደትም ለመቀነስ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክልል አቀፍ የንቅናቄ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

እየተካሄደ ከሚገኘው የንቅናቄ ስራ ጎን ለጎን ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የአልጋ አጎበርን ጨምሮ ሌሎች የበሽታ መከላከያ ግብአቶችን ለዞኖችና ወረዳዎች ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉንም የቢሮው የወባ ማስወገድ አማካሪው አቶ ሄኖክ በቀለ ተናግረዋል፡፡

 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ