1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም ዙሪያ ለማያዳላ ጋዜጠኝነት በቊርጠኝነት ቆመናል፤ አምባገነኖችንም እንቅልፍ እንነሳለን  

ማክሰኞ፣ መስከረም 12 2013

በዓለም ዙሪያ፦ ዲሞክራሲ ተግዳሮት እየገጠመው ነው፤ ነጻነትም የጥቃት ሰለባ ኾኗል። ኃይለኞች  ዜናውን በተቆጣጠሩባቸው ሃገራት ሕዝቡ ከመጥፎ አማራጮች መካከል ለመምረጥ ይገደዳል። 

https://p.dw.com/p/3iqBQ
Insomnia | Free Speech | Campaign
ምስል DW

ተልእኳችን፤ የማያዳላ መረጃ ለነጻ አእምሮዎች 

በዓለም ዙሪያ፦ ዲሞክራሲ ተግዳሮት እየገጠመው ነው፤ ነጻነትም የጥቃት ሰለባ ኾኗል። ኃይለኞች ዜናውን በተቆጣጠሩባቸው ሃገራት ሕዝቡ ከመጥፎ አማራጮች መካከል ለመምረጥ ይገደዳል። ለዚያም ነው ሥራችን የማያዳላ መረጃን በማቅረብ እና ለመናገር ነጻነት በመቆም በዓለም ዙሪያ ከ180 በላይ ሃገራት ውስጥ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ ያስችል ዘንድ አምባገነኖችን ተገዳዳሪ እንዲኾን ያደረግነው። አምባገነኖችን እንቅልፍ መንሳታችን እናረጋግጣለን።

የመናገር ነፃነትን እንዴት ነው የምንደግፈው 

ዶይቸ ቬለ (DW) የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰለባዎች፤ እንዲሁም ቀውሶች ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ ቀዳሚ ርምጃዎችን ይወስዳል፤ በመናገር ነፃነት እና በመገናኛ አውታሮች ነጻነት ዙሪያ ያሉ ውስብስብ ጉዳዮችንም ለመዳሰስ ጥረት ያደርጋል። አኹን ያሉት ኹኔታዎች ላይ ብርቱ ውይይት እንዲደረግ በማበረታታትም ኹኔታዎቹ እንዲሻሻሉ ይጥራል። 

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አራማጆችን፣ ምሑራንን፤ የጥበብ ባለሞያዎችን፤ ካርቱኒስቶችን እና ደራሲያንን ቃለመጠይቅ በማድረግ እና ዘገባቸውን በማካተት ለመናገር ነጻነት እና ሐሳብን በነጻነት ለመግለጽ የሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ምንጊዜም ትኩረት እንሰጣለን። 

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2015 አንስቶም ዶይቸ ቬለ (DW) ሐሳብን በነፃነት በመግለጹ ዘርፍ  የሚንቀሳቀሱ የዶይቸ ቬለ (DW) ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማትን ሲሰጥ ቆይቷል።  ሽልማቱ ነጻ ሚዲያ እንዲጎለብት ጥረት የሚያደርጉ በእስር ላይ የሚገኙ ጦማሪያን እና ደፋር ጋዜጠኞችን አካቷል። 

 መልእክቱን ማዳረስ

Zensurumgehung - Software Psiphon
ምስል DW/O. Linow

በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች በአኹኑ ወቅት ከምን ጊዜውም በተሻለ መረጃዎችን መለዋወጥ እና በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ኾኖም መንግሥትን የሚቃወሙ ጽሑፎችን የሚያትሙ ሰዎች በበርካታ ቦታዎች ቅጣት እንደሚደርስባቸው እና የነፃ መረጃ ፍሰቱም እገዳ እንደሚጣልበት መዘንጋት አያሻም።  

ዶይቸ ቬለ (DW) አፈናን መታገል ዋና መርኁ ነው።  በየትም ቦታ የሚገኙ ሰዎች ችግራቸውን እንዲረዱ እና ማኅበረሰባቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዲገነዘቡም የሚያስፈልጋቸውን መረጃዎችን ያለመታከት ያቀርባል።  

በበርካታ ሃገራት መንግሥት የሚቆጣጠራቸው መሠረተ አውታሮች መረጃዎች ላይ ቊጥጥር ወደማድረግ ወይንም ሙሉ በሙሉ ወደ መቊረጥ ሊያመሩም ይችላሉ። ለዚያም ነው ዶይቸ ቬለ ቊጥጥሮችን ሰብሮ በማለፍ መረጃዎች ሰዎች ጋር እንዲደርሱ የሚሠራው። ለአብነት ያኽል፦ ገለልተኛ ዜና እንዳያገኙ መንግሥታቸው ቊጥጥር በሚያደርግባቸው ሃገራት የሚኖሩ ሰዎች አኹን የዶይቸ ቬለ ዘገባዎችን በምሥጢር እና ማንነታቸው ሳይታወቅ መከታተል ይችላሉ። ለዚያም የሚያገለግሉ እንደ OTF (Open Technology Fund) እና ቶር የተሰኙ ፕሮጀክቶች አሉ። ሰዉ ከdw.com ድረገጽ መረጃዎችን ማግኘት እንዲችል ዶይቸ ቬለ በቶር የኢንተርኔት መረብ ውስጥ አነስ ያለ የዶይቸ ቬለ ድረገጽ ተመሳሳይ ማገናኛ አስገብቷል።  

በቶር Tor (The Onion Routing) በኩል የሚገኙ ድረገጾችን ለመጠቀምም በቶር የሚታወቅ ለየት ያለ ፋይርፎክስን መሰረት ያደረገ የቶር ድራለማቀፍ ማሰሺያ መጫን ያስፈልጋል። ከዶይቸ ቬለ ባሻገር በአኹኑ ወቅት እንደ ኒውዮርክ ታይምስ እና ቢቢሲ ያሉ ድረገጾችን በቶር በኩል ማግኘት ይቻላል። 

ባለፉት ዐሥር ዓመታት ዶይቸ ቬለ የመረጃ እገዳ በተጣለባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች መረጃዎቹን ያለገደብ ማግኘት ይችሉ ዘንድ ከሚኖሩበት አካባቢ ኔትወርክ አቅራቢ ውጪ በኾነ ማገናኛ በሚሠራው ፒሲፎን (Psiphon) በተሰኘው [ተጠቃሚውን እና ኢንተርኔት ላይ ያለውን ምንጭ አገናኝ በኾነው] የተለየ ማገናኛ በኩል ሰብሮ በመግባት መረጃዎቹን ሲያደርስ ቆይቷል። በዚህ ሥነ-ቴክኒክ እንደ ቻይና እና ኢራን ባሉ ሃገራት የሚኖሩ ተጠቃሚዎች አስተማማኝ ከኾኑ ምንጮች ወደ አንድ ወገን ያላደሉ መረጃዎችን በማግኘት ላይ ይገኛሉ።   

እነዚህን ሥነ-ቴክኒኮች ስንጠቀምም ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት አለ፦ ዶይቸ ቬለ ነጻ ኢንተርኔት የማበረታታት፤ አድሏዊ ያልኾኑ፣ ጥራት ያላቸው መረጃዎች እና ዜና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተጠቃሚዎቹ  እንዲዳረስ የማድረግ ሙከራውን መቼም ተስፋ አይቆርጥበትም። 

 ብዝኃነት ውይይት አጭሯል 

JaafarTalk aus dem jordanischen Flüchtlingslager Zatari
ምስል DW

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓረቡ ዓለም የሚዲያ ምኅዳሩ እና የሚዲያ ተሳትፎው በፈጣን ኹኔታ ተቀይሯል። ያ ታዲያ በወጣቶች ብቻም አይደለም። እያንዳንዱ ነገር እየተቀየረ ነው። ሰዎች በሥነ-ቴክኒኩ ረገድ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችን እና መተግበሪያዎችን እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ስልኮች ግንኙነትን በመጠቀም ከምንጊዜው በላይ ለመረጃ ልውውጥ እና ውይይት ክፍት በኾኑበት ወቅት፤ ከሙግቱ እና ውይይቱ ራሳቸውን የማራቅ ኹኔታ ያለ ይመስላል።   

ጃፋርቶክ (JaafarTalk) ያን መቀየር ይፈልጋል። የቴሌቪዥን ውይይት ዝግጅቱ በሌሎች ጣቢያዎች የማይቀርቡ ርእሰ ጉዳዮችን ጭምር በማቅረብ፤ ሌላው ቀርቶ በዓረቡ ዓለም እንኳ ድምፅ የተነፈገውን የእያንዳንዱ ሰው ድምጽ እንዲስተጋባ ያደርጋል። ከተለያዩ ሃገራት የመጡ እና የተለያዩ ምልከታዎችን የሚወክሉ እንግዶችን መሠረት በማድረግም በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ አነጋጋሪ ውይይቶችን ያቀርባል። በቴሌቪዥን ዝግጅቱ መዝጊያ ላይ ስቱዲዮ የተገኙ ተጋባዥ ታዳሚያንም ኾኑ ተመልካቾቹ በውይይቱ አመለካከቱን በአሳማኝ መንገድ ያቀረበውን ተወያይ እንዲመርጡ ይደረጋል። እናም በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት ላላቸው ሰዎች እጅግ የሚመች መድረክ ነው።  .  

ጃፋርቶክ የዓረቡ ዓለም ብዝኃነትን የሚያንጸባርቅ አሳታፊ የውይይት መድረክ ነው። የዝግጅቱ አቅራቢ አብዱል ካሪም፦ ፍትኃዊ እና ተወዳጅ ግን ደግሞ ትልቊን ምስል ለመከሰት የሚያግዙ በምርምር፣ በተጨባጭ መረጃዎች እና በአሓዞች የታገዘ ውይይት ለማድረግ ቃጣናውን የሚወክሉ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቊ እንግዶችን ይጋብዛል። አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት ጃፋርቶክን Instagram Facebook እና YouTube መከተል ይቻላል። 

ርእሰ ጉዳዮቹን በምስል መከሰት

#speakup barometer key findings Word cloud No. 4#speakup barometer key findings Word cloud No. 4
ምስል DW

ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ዩክሬን ከሚኖሩት አመለካከታቸውን በዲጂታል መድረኮች በይበልጥ መግለጥ ይችላሉ? ይኽ #speakup barometer የተሰኘው መለኪያ DW አካዳሚ የመገናኛ አውታሮችን ለማሳደግ በተለያዩ የተመረጡ ሃገራት ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች በዲጂታል ተሳትፎ፣ ሐሳብን በመግለጽ ነጻነት እና መረጃዎችን በማግኘት መካከል ያሉትን ግንኙነቶች የሚመረምርበት ፕሮጀክት ነው። 

ዓላማውም በሃገራቱ ውስጥ ያሉትን ወቅታዊ የዲጂታል ተሳትፎዎች መዳሰስ ብሎም አዲስ አቅም እና አደጋዎችን መለየት ነው። የ#speakup መለኪያ መገናኛ አውታሮች እንዲጎለብቱ የሚሠሩ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ተጓዳኝ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት የዲጂታል ቅየራ ሒደት፣ ሀሳብን የመግለጥ ነፃነት እና መረጃን የማግኘት መንገዳቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳል።      

የመገናኛ አውታር ነፃነት መቃኚያ  

በሀገርዎ የመገናኛ አውታሮች ምን ያኽል ነፃ ናቸው? የመገናኛ አውታሮች መቃኚያ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ነፃነት መለኪያዎችን ዳሰሳ ያቀርባል። በእያንዳንዱ ሀገር ያለውን የመገናኛ አውታሮች ነፃነት መረጃ እና በማውጪያው ላይ ያሉትን ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት የዓለም ካርታውን መቃኘት ትችላላችሁ። 

በተዛቡ መረጃዎች ባሕር ውስጥ ተአማኒነት 

Plus 90, +90, türkischer Youtube Kanal, Deutsche Wele, BBC, France 24, VOA
ምስል DW

ቱርክ ውስጥ የጋዜጠኝነት ተግባር ከባድ ፈተና ገጥሞታል። የቱርክ ቋንቋ ተናጋሪ ተከታታዮች ተአማኒ መረጃዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል ይረዳ ዘንድ ዶይቸ ቬለ  ከቢቢሲ፣ ፍራንስ 24 እና ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በመተባበር የዩቲዩብ መስመር ከፍቷል። 

የዩቲዩብ መስመሩ YouTube channel +90 ይሰኛል፤ ስያሜውን ያገኘውም ከቱርክ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪ መግቢያ በመነሳት ነው። የዩቲዩብ መስመሩ ገለልተኛ እና ተአማኒ መረጃ ያቀርባል፤ የመናገር እና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ያከብራል ብሎም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች መንጸባረቃቸውን ያከብራል። በርካታ በዩቲዩብ መስመሩ የተላለፉ ቪዲዮዎች አንዳንዶቹ ወደ ጀርመንና ቋንቋ የተተረጎሙ ናቸው ከሚሊዮን ጊዜ በላይ ተመልካች አግኝተዋል።  +90 የተሰኘው የዩቲዩብ መስመር አንዳንድ ጊዜ ቱርክ ውስጥ በሚገኙ የመገናኛ አውታሮች የማይቀርቡ እንደ ስደተኞች፤ LGBTQ እና የሴቶች መብቶች ርእሰ ጉዳዮችን ይሸፍናል። እናም +90  እነዚህ ርእሰ ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመር ተቀያያሪ እና በተሟሟቀ ሀገር ውስጥ የዕለት ተዕለት ሕይወት ይበልጥ ሚዛናዊ ዕይታ እንዲኖረው ያስረግጣል።