1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም መድረክ ጀግና የተባለችዉ ኢትዮጵያዊት   

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2012

አሸናፊ መሆኔ የሚገርም ነገር ነዉ። ብቻ እንደ ግለሰብ በጣም ያኮራል። ትልቁ ነገር ግን ሃገርን ማስጠራት ማለት ኩራት ነዉ። ለአፍሪቃም ቢሆን ኩራት ነዉ። ስለዚህ ይህን ጉዳይ ጉዳያችን ብለን ለዓለም ሕዝብ፤ ለመጀመርያ ጊዜ ለመላዉ ዓለም ያሳወቅንበት ነዉ። የሴቶች ጉዳይ ደግሞ ለዘመናት የቆየ ጮክ ብለን የማንናገርለት ችግራችን ነበር።

https://p.dw.com/p/3Ui6E
Freweini Mebrahtu CNN Hero of the year
ምስል Getty Images/M. Loccisano

ፍረወይኒ መብርሃቱ

«በአጠቃላይ በሃገራችን ሴቶች ዘርፈ ብዙ የሆነ ችግር ነዉ ያለባቸዉ። አስገድዶ መድፈር፤ ግርዛት፤ ያለ እድሜ ጋብቻ፤ በተፈጥሮ ምክንያት ከሚመጣ የወር አበባ ጋር በተያያዘ ብዙ መገለል ጉዳዮች ይደርሳሉ። ተማሪዎች ላይ በተለይ ደግሞ አብዛኛዉ ህዝባችን የሚኖረዉ ምንም ምንጭ በሌለበት በገጠር አካባቢ በመሆኑ ነዉ። ሴቶች ቀና ያላሉበት ሃገር ሊቀና አይችልም የሚል አስተያየት ነዉ እኔ ያለኝ። የሴቶች ነገር እየተረሳ ሃገር የሆነ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል የሚል እምነት የለኝም። በአጠቃላይ የሴቶች ነገር የተሻለ ትኩረት አግኝቶ በሁሉም ዘርፍ በጥንካሪ እንዲሰራ ነዉ እኔ ማሳሰብ የምወደዉ» ስትል የገለፀችልን በሴቶች መብት ጉዳዮች ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግዋ የምትታወቀዉ እና በአሁኑ ወቅት በዩናይትድስቴትስ ነዋሪ የሆነችዉ መቅደስ አስራት ናት። መቅደስ ይህን አስተያየት የሰጠችን ኢትዮጵያዊትዋ ፍረወይኒ መብርሃቱ የ «CNN»  ጀግኖች የዘንድሮ የጎርጎረሳዉያን 2019  አሸናፊ መሆንዋ ይፋ ከተደረገ በኋላ የተሰማትን ደስታ በገለፀችበት ወቅት ነዉ።  

Freweini Mebrahtu
ምስል DW/M. Hailesselassie

ፍረወይኒ መብርሃቱ ሽልማትዋን ከ «CNN»  ስትቀበል ባሰማችዉ ንግግር   «በጣም አመሰግናለሁ! ምን ማለት እንዳለብኝ እንኳ አላዉቅም። በጣም ተደስቻለሁ ፤ «CNN» ይህን ዉቅና ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ። እዉቅናዉ በሁሉ ቦታ ላሉ ሴቶች ሁሉ ይሁን ። ክብር ለሴቶች ሁሉ!  ይህ የሽልማት ደስታ ወቅት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለወጣት ሴቶች ሁሉ ነዉ። በዓለም በሁሉም ቦታ ይህን  ችግራችንን ወጥተን ተናግረን አናዉቅም። «CNN » ድምፅችን በጥራትና በከፍታ እንዲሰማ ስላደረገ አድናቆቴን እገልጻለሁ። ክብር ለሁላችሁም!»       

ኢትዮጵያዊትዋ ፍረወይኒ መብርሃቱ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቅያን ለገጠር ሴት ተማሪዎች ለማዳረስ እና በኢትዮጵያ በሴቶች የወር አበባ ላይ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ለማረም የሚያግዙ ስራዎችን ላለፉት 13 ዓመታት ስታከናዉን ቆይታለች። ለዚህ ሁሉ አስተዋጽኦዋ ከ«CNN» ወደ 100 ሺህ ዶላር እና ከበርግ ፋዉንዴሽን ነጻ የአመራር ስልጠና እድል ሽልማትን ተቀብላለች። ፍረወይኒ የ «CNN» ጀግኖች ሽልማት አሸናፊ መሆንዋ በተገለፀ በነጋታዉ ከኒዮርክ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በጉዞ ላይ ሳለች ነበር በስልክ ያገኛት። ከርካታ ሚዲያ ለቃለ-መጠይቅ ጥያቄዎችና ቀጠሮ ቢኖራትም ጊዜ ሰጥታ፤ ከ ዶይቼ ቬለ «DW» የእንኳን ደስ ያለሽ መልክታችን ተቀብላለች።  

« አሸናፊ መሆኔ የሚገርም ነገር ነዉ። ብቻ እንደ ግለሰብ በጣም ያኮራል። ትልቁ ግን ግን ሃገርን ማስጠራት ማለት ኩራት ነዉ። ለአፍሪቃም ኩራት ነዉ። ስለዚህ ይህን ጉዳይ ጉዳያችን ብለን ለዓለም ሕዝብ ፤ ለመጀመርያ ጊዜ ለመላዉ ዓለም ያሳወቅንበት ነዉ። ጥሩ ስራ ተሰርቶአል እስካሁን ድረስ ፤ ግን ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን ነዉ የሚያሳየን።  ሆኖም ግን ብቻችንን የምንሰራዉ ስራ ስላልሆነ፤ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ድምፅ ሰጥቶ እዚህ ደረጃ ላይ አድርሶናል። ዘንድሮ ለዉድድር ከኔጋ የቀረቡት አስሩም ጀግኖች በጣም ጥሩ ስራን ሰርተዉ ነዉ የቀረቡት። ሆኖም ግን የኛ በለጥ ብሎ የታየበት ምክንያት፤  ሁሉንም ማኅበረሰብና ዜጋ የሚነካ ጉዳይ በመሆኑ ነዉ። የሴቶች ጉዳይ ደግሞ ለዘመናት የቆየ ጮክ ብለን የማንናገርለት ችግራችን ነበር።  አሁን ግን እዚህ ላይ የደረስነዉ የችግሩን መፍቺያና የግንዛቢ ማስጨበጫ በመስራታችን ነዉ።  እናም ለሃገር በተለይ ጥሩ ጥሩ መፍትሄ ነዉ የሚሆነዉ። እንደ አፍሪቃዉያንም በጣም ትልቅ ኩራት ነዉ። አንድ የ «CNN» ጀግና ከአፍሪቃ ሲገኝ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። ለ «CNN» ኖች ስለሸለሙኝ ምስጋናዬን ገልጬላቸዉ ነበር።  ነገር ግን « ድምፅ የሰጠሽን ህዝብሽን አመስግኝ»  ነዉ ያሉኝ መላዉ ኢትዮጵያዉያንን አመሰግናለሁ!            

Freweini Mebrahtu
ምስል DW/M. Hailesselassie

በሃገራችን በአብዛኛዉ ቦታ አንደኛ የወር አበባ ሲጀመር ተፈጥሮዋዊ ግዴታ ሳይሆን አፀያፊ ነገር ተደርጎ የሚወሰድበት ፤ ሁለተኛ ሴት ልጅ የወር አበባዩ መጣ ብላ መናገር ባማትችልበት፤ ለሴት ልጆች ምንም አይነት ግንዛቤ እና እዉቀት ሳይኖራቸዉ የወር አበባ በሚያዩበት፤ አንዳንድ ቦታ እንደዉም አንዴት ልጃገረድ ታዳጊ ህጻን የወር አበባዋ ከታየባት ከወንድ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርጋለች ተብሎ በምትወገዝበት ይሄንን መፍትሄ ይዞ መዉጣት ለብዛኛ ወጣት ሴቶች እፎይታ ይመስለናል።   

የኢትዮጵያን ስም አስጠርታ የ«CNN » የዘንድሮን የጀግና ሽልማት በማሸነፍዋ መደሰትዋን የገለፀችልን በሴቶች ጉዳይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግዋ የምትታወቀዉ ከመቅደስ አስራት እና ከዘንድሮዋ የ «CNN»  ጀግና ተሸላሚ ፍረወይኒ መብርሃቱ ጋር ያደረግነዉን ቃለ ምልልስ ሙሉ ጥንቅር እንዲያዳምጡ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ