1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለማችን ከፍተኛ ረሃብ ይከሰታል ሲሉ የእርዳታ ድርጅቶች አስጠነቀቁ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013

ከ260 በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ እርዳታ ድርጅቶች በተለያዩ የዓለም ሃገራት ከባድ ረሃብ ሊከሰት ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ። የርዳታ ድርጅቶቹ  በፃፉት ግልጽ ደብዳቤ „በዓለም ላይ 34 ሚሊዮን ዜጎች ላይ ሊከሰት የሚችለዉን ረሃብ በአስቸኳይ ለመግታት ተጨማሪ 5.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰበሰብ ጥሪ እናቀርባለን”ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3sIFl
Äthiopien Hunger Hungerhilfe
ምስል Reuters/T.Negeri

ከ260 በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ እርዳታ ድርጅቶች በተለያዩ የዓለም ሃገራት ከባድ ረሃብ ሊከሰት ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ። የርዳታ ድርጅቶቹ ፊርማቸዉን በማኖር ለተለያዩ የዓለም ሃገራት መንግስታት ዛሬ በጻፉት ግልፅ ደብዳቤ እንዳሳሰቡት ፤ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2021 ዓመት ሊከሰት የሚችለዉን ረሃብ ለመታደግ ተጨማሪ 5,5 ቢሊዮን  ዶላር ያስፈልጋል። የዓለም ሃገራት መንግሥታት እንዲያዋጡ የተጠየቀዉን ድምር ገንዘብ ያሰሉት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO መሆናቸዉ ተነግሮአል። የርዳታ ድርጅቶቹ  በፃፉት ግልጽ ደብዳቤ „በዓለም ላይ 34 ሚሊዮን ዜጎች ላይ ሊከሰት የሚችለዉን ረሃብ በአስቸኳይ ለመግታት ተጨማሪ 5.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰበሰብ ጥሪ እናቀርባለን”ብለዋል።  የህፃናት አድን ፣ ወርልድ ቪዥን ፣ ኦክስፋም፤ ኬር ኢንተርናሽናል የተካተቱበት የግብረሰናይ ድርጅቶች ቡድን በግምት ወደ  270 ሚሊዮን ከሚሆኑ በዓለም ላይ ከተራቡ ወይም የረሃብ አደጋ ከተደቀነባቸዉ ዜጎች ጋር እየሰሩ ያሉ የርዳታ ድርጅቶች  ናቸዉ። በየመን ፣ አፍጋኒስታን ፣ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ፣ ሆንዱራስ ፣ ቬንዙዌላ ፣ ናይጄሪያ ፣ ሃይቲ ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ ኡጋንዳ ፣ ዚምባብዌ ፣ እና ሱዳን የሚገኙ ርዳታ የሚሹ ዜጎች ተጨማሪ ቀናትን በህይወት እንዲቆዩ እንረዳለን፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ የሚራቡ ሳይሆኑ የተራቡ ናቸዉ ማለታቸዉ የርዳታ ድርጅቶቹ  በፃፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ተጠቅሶአል። በዓለማችን የሚራበዉ ሰዉ ቁጥር ሊጨምር ይችላል ሲሉ መግለጫቸዉን ይፋ ያደረጉት የርዳታ ድርጅቶች ለረሃቡ መከሰት በተለያዩ ሃገራት የሚታዩ ግጭቶች ፤ የከባቢ አየር ሁኔታ መቀያየር ፤ ፍትሃዊ ያልሆነ ተጠቃሚነት እና የኮሮና ተኅዋሲ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።  

 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ