1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትችት በሠራተኛ ውል እገዳ መነሳት ላይ

ሐሙስ፣ የካቲት 1 2010

ከዋና ዋና የሰራተኛ ተቀባይ  ሀገራት ጋር የስራ ውል ስምምነት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት በውጭ ሀገር የሰራተኛ ጉዞ ላይ የጣለውን እገዳ አንስቻለሁ ማለቱ ትርጉም አልባ መሆኑን ሪያድ ከተማ የሚገኙ አንድ የሰው ኃይል ልማት ባለሙያ ተቹ፡፡

https://p.dw.com/p/2sNOT
Äthiopische Hausfrauen in Saudiarabien und VAE
ምስል DW/S. Shibru

ትችት በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔ ላይ

ከሰማኒያ አምስት በመቶ በላይ የኢትዮጵያን  ሰራተኞች ተቀባይ ከሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የተፈረመው የስራ ውል ስምምነትም ላለፉት አስር ወራት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አልጸደቀም መባሉም ግራ የሚያጋባ መሆኑን እኚሁ ባለሙያ ይገልጻሉ፡፡በሌላም በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ፍቃድ የሚወስዱ የሰራተኛ ላኪ ኤጀንስዎች ከገንዘባቸው በላይ ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባቸው ከዚህ ቀደም በኤጀንሲ ወኪልነት ይሰሩ የነበሩ አንድ የሪድ ነዋሪ ጠይቀዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ እና ኢትዮጵያ የሰራተኛ የስራ ውል ስምምነት ከተፈራረሙ አንድ ዓመት ሊሆናቸው ሁለት ወራት ብቻ ነው የቀራቸው ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ህገወጥ ያለቻቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ባለፈው ዓመት ማስወጣት ከጀመረች በኋላ ነበር የስራ ውል ስምምነት ጂዳ ከተማ መፈረሙ የተነገረው ፡፡ ይሁንና ከቀናት በፊት ስለ ውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እገዳ መነሳት መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ መንግስት የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች   90 በመቶ ያህል ሰራተኞችን ከኢትዮጵያ የመቀበል አቅም እና ፍላጎት ካላቸው ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር የስራ ውል ስምምነቱ ገና ያለመጠናቀቁን ነው የተናገሩት ፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሰው ኃይል ልማት ባለሙያ ታዲይ ከዋናዎቹ ተቀባዮች ጋር የተደረገው ስምምነት እልባት ሳያገኝ እግድ አንስቻለሁ ማለት ከመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ የዘለለ ጥቅም የለውም ይላሉ ፡፡

Äthiopische Hausfrauen in Saudiarabien und VAE
ምስል DW/S. Shibru

የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ ጋር የተፈራረመወው የሰራተኛ ውል ስምምነትም ቢሆን ፓርላማው ሳያጸድቀው ለአስር ወራት ያህል መቆየቱ የጤና እንደማይመስል እኚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሰው ኃይል ልማት ባለሙያ ይተቻሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሳዑዲ እና የኢትዮጵያ መንግስታት በተለይ በደሞዝ ክፍያ መጠን ላይ ያለመግባባት ነበራቸው ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት 1200 ሳዑዲ ሪያል ዝቅተኛው ደሞዝ ይሆን ሲል የሳዑዲ  መንግስት ደግሞ  700 ሳዑዲ ሪያል በቂ ነው ባይ ነበር ፡፡ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ስለ ደሞዝ መጥን በመግለጫቸው ምንም ባይሉም ለመዘግየቱ ምክንያቱ ይህ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በሱዳን የሚደረግን ህገወጥ ጉዞ አንስተው መኮነናቸውን በማንሳት ምን ማለት ነው ብለው የሚሞግቱት አስተያየት ሰጪው  ከሁሉም ሀገሮች ጋር ውሉ ባግባቡ ታስሮ ጉዞ ባልተጀመረበት ሁኔታ የሱዳኑን ህገወጥ መንገድ ማንሳት ሌላ አማራጭ መንገድ አለላችሁ እንደማለት ቆጥረውታል፡፡አቶ ባህሩ ሀሰን ደግሞ ለ 7 ዓመታት የሰራተኛ ላኪ ኤጀንሲ የበላይ ወኪል ሆነው  ሰርተዋል፡፡ የእግዱ መነሳት በጎ ጎን ቢኖረውም ከዚህ በፊት የነበሩ ህጸጾችን በማይደግም መልኩ ሊካሄድ እንደሚገባው ያሰምሩበታል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት የሰራተኛ ላኪ ኤጀንሲዎች ላይ ጠበቅ ያለ አዋጅ ማውጣቱን ያወደሱት አቶ ባህሩ የኤጀንሲ ባለቤቶችም ከገንዘብ ይልቅ ለዜጎች ደህንነት ከፍተኛ ግምት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡በመካከለኛው ምስራቅ ሰራተኞችን የሚያቀርቡ የእስያ ሀገሮች በየ ተቀባይ ሀገሮች ካሏቸው ኤምባሲዎች ውጭ የሰራተኛ ዜጎቻቸውን የዕለት ተዕለት ሁኔታ የሚከታተል ጠንካራ ቢሮም አላቸው፡፡

ስለሺ ሽብሩ 

ኂሩት መለሰ