1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወላይታ 21 ሰዎች መገደላቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተናገሩ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 5 2012

በወላይታ ዞን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ ለዶይቼ ቬለ ገልጹ። የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ "አምስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ አስራ አምስት ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3gmxz
Karte Sodo Ethiopia ENG

በወላይታ ዞን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ ለዶይቼ ቬለ ገልጹ። የጸጥታ አስከባሪዎች በዞኑ ሰዎች በጅምላ ማሰር መጀመራቸውን የገለጹት አቶ አንዱዓለም በሶዶ እና በአካባቢው ወታደሮች በብዛት መሰማራታቸውን አክለዋል። እንደ አቶ አንዱዓለም ከሆነ "መንገዶች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች" ተዘግተዋል።

የዐይን እማኞች እንደሚሉት የዞኑ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የወላይታ ክልል እንዲመሠረት ግፊት በማድረግ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ማሕበረሰቦች ተወካዮች ባለፈው እሁድ መታሰራቸው ከተሰማ በኋላ በተለይ ሶዶ እና ቦዲቲ ከተሞች የበረታ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸዋል።

ከአዲስ አበባ 295 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቦዲቲ ከተማ የጸጥታ ኃይሎች በትንሹ ስምንት ሰዎች ተኩሰው መግደላቸውን በከተማዋ የሚገኝ የጤና ማዕከል ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ተመስገን ሕሊና ለሬውተርስ ተናግረዋል።

ሟቾቹ “ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸው እና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመተዋል" ያሉት ተመስገን “የመጀመሪያ ሕክምና የሰጠኋቸው እኔ ነኝ። ከዚያ ሞቱ" ሲሉ ተናግረዋል። እንደ አቶ ተመስገን ከሆነ ከሟቾች መካከል የ14 አመት አዳጊ ይገኝበታል።

የወላይታ ዞን አስተዳደር መቀመጫ በሆነችው እና ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ 315 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሶዶ በትንሹ አራት ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።

በሶዶ እና በቦዲቲ ሰዎች መገደላቸውን ያረጋገጡት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ማቴዎስ ባልቻ "ሕዝቡ የእስራት እርምጃውን ተቃውሞ በወጣበት ሰዎች ከወታደር በተተኮሰ ጥይት ሞተዋል" ብለዋል።

Äthiopien Proteste Wolita Zone
በሶዶ መንገዶች፣ መገበያያዎች በተቃውሞ ተዘግተዋልምስል Addis Standerd

በሶዶ ነዋሪ የሆኑ አንድ የሕክምና ባለሙያ ትናንት ሰኞ "አንድ ወጣት እግሩ ላይ በጥይት ሲመታ በአይኔ አይቻለሁ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ባለሙያው "ሆስፒታል ያሉ ጓደኞቼም ነግረውኛል። ሶዶ ከተማ ውስጥ አራት ወጣቶች ሞተዋል። በርካታ ወጣቶች የቆሰሉበት ኹኔታ ነው ያለው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እኚሁ የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በቦዲቲ ከተማ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል የሚል መረጃ ደርሷቸዋል።

የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ "አምስት የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ አስራ አምስት ሰው መካከለኛ እና አነስተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ሲሉ ለብሔራዊው የቴሌብዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ ግን የሟቾች ቁጥር 21 መድረሱን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። አቶ አንዱዓለም እንዳሉት ከ105 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

የጉታራው ስብሰባ

በወላይታ ዞን ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻ የሆነው የወላይታ ክልል ምሥረታ አስተባባሪ ኮሚቴ በሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉታራ አዳራሽ ያደረገው ስብሰባ ነው። ኮሚቴው ከዞኑ የመንግሥት መዋቅር የተወከሉ ባለሥልጣናት፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የንግድ ምክር ቤት እንዲሁም የዞኑ ምክር ቤት አባላትን እና የሕግ ባለሙያዎች ያካተተ ነው። ባለፈው እሁድ በተጠራው ስብሰባ "በቤተሰብ ዕክል ምክንያት" ያልታደሙት እና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ማቴዎስ ባልቻ "የተዘጋጀ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት አለ። እሱ ላይ ውይይት ለማድረግ ነበር የእሁዱ ስብሰባ የተጠራው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Äthiopien - Der äthiopische Premierminister Abiy Ahmed und der Administrator der Wolayta-Zone, Dagato Kumbe
ከታሰሩ መካከል የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ይገኙበታልምስል Amt des äthiopischen Ministerpräsidenten

አቶ ማቴዎስ ባልቻ "በስብሰባው የነበሩ በሙሉ ነው የታሰሩት። ወደ 25 ይሆናሉ። የታሰሩት በከተማው የግብርና ኮሌጅ ግቢ አለ። ለጊዜው እዚያ ግቢ ውስጥ ነው የቆዩት። ያሰራቸው አካል የመከላከያ ሰራዊት ነው። በደንብ ልብሳቸው ትለያቸዋለህ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ፣ የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ የወላይታ የአገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና ምክትላቸው፣ የንግድ ምክር ቤት ተወካዮች ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አመራሮች፣ የላጋ የተባለው የወጣቶች ንቅናቄ ተወካዮች እና የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባላትም ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል። የደቡብ ክልል የዞኑ አመራሮችን ጨምሮ 26 ሰዎች መታሰራቸውን አረጋግጧል። 

ለምን ታሰሩ?

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሶዶ ከተማ ነዋሪ "ያለ ክልል መንግሥት እውቅና የሚደረግ ስብሰባ ሕገ-ወጥ ስብሰባ ነው በሚል" መታሰራቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። "ሕዝቡ እያሰበ ያለው አሁን የተሰራው ሥራ የክልል ጥያቄውን ለማደናቀፍ እንደሆነ ነው" የሚሉት አቶ ማቴዎስ በበኩላቸው የመንግሥት እርምጃ ወላይታ የራሱን ክልል ለመመሥረት የዞኑ ልሒቃን እያደረጉ ከሚገኘው ግፊት ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ አስረድተዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው "ጥቂት" ያሏቸው የዞኑ አመራሮች የወላይታ ክልል የመመሥረት ጥያቄ በኃይል ለማስመለስ ግፊት አድርገዋል ሲሉ ወንጅለዋል። "በጋራ የተቀመጠውን ሥምምነት በመጣስ አቅጣጫውን እንዲስት በማድረግ እንደገና ወደ ኃይል አማራጭ እንዲሔድ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር" ብለዋል ርስቱ።  

የወላይታ ዞን የራሱን ክልል ለማቆም በሚያደርገው ግፊት ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጋር ብርቱ መቃቃር ውስጥ ገብቷል። የወላይታ ተወካዮች ባለፈው ሰኔ በዚሁ ሰበብ በደቡብ ምክር ቤት መሳተፍ ማቆማቸውን ገልጸው ነበር። ተወካዮቹ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ የወላይታን "በክልል የመደራጀት ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ስህተቱን በማረም ይቅርታ ጠይቆ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ ከእንግዲህ ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ የሕዝባችንን ጥያቄ በአግባቡ በማያስተናግድ" ምክር ቤት መሳተፍ አንፈልግም ብለዋል።

የደቡብ ምክር ቤት ከወላይታ ዞን የቀረበለትን ክልላዊ መንግሥት የመመሥረት ጥያቄ ተቀብሎ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማስተላለፍ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሔድ አለማድረጉ የወላይታ ተወካዮች ራሳቸውን ለማግለል ያበቃቸው ምክንያት ነበር። የወላይታ የለውጥ አራማጆች እና የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የደቡብ ምክር ቤት የዞኑን ጥያቄ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለማቅረቡ የሰላ ትችት ይሰነዝሩበታል።

ከዚህ ባሻገር የዞኑ ምክር ቤት የወላይታን የጸጥታ ጥበቃ ከክልሉ የመንግሥት መዋቅር በማፈንገጥ ራሱ ለማከናወን ወስኖ ነበር። የወላይታ ዞን ምክር ቤት "የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅር በሚመሩ አካላት እምነት ስለሌለንና ገለልተኛ ባለመሆናቸው" የጸጥታ ጥበቃ በዞኑ መዋቅር እንዲከናወን መወሰኑን ባለፈው ሰኔ አጋማሽ አስታውቋል።

Äthiopien | Wolaita Women's March
የወላይታ ክልል የመመሥረት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ተደጋጋሚ ሰልፎች ተደርገዋልምስል Facebook/Author-Wolaita Times

ወላይታ የራሱን ክልል የማቆም ጥያቄ ያቀረበው ታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ሲሆን ሐሳቡን በመደገፍ እና አፋጣኝ ምላሽ በመጠየቅ በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተደጋጋሚ ሰልፎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሶዶ ባቀኑበት ወቅት ከዞኑ አመራሮች እና ከተለያዩ ማሕበረሰቦች ተወካዮች ከመከሩባቸው ጉዳዮች ዋንኛው ይኸው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ ይገኝበታል።

በሶዶ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና የጸጥታ ኃይሎች ከወሰዱት እርምጃ በኋላ ሥጋት ማረበቡን ዶይቼ ቬለ ከከተማዋ ነዋሪዎች ለመረዳት ችሏል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ "የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤ ባንኮች እና ሱቆች ዝግ ናቸው። ሰውም በነጻነት እየተንቀሳቀሰ አይደለም" ሲሉ ድባቡን አስረድተዋል።

"ከሐዋሳ ወደ ሶዶ የሚያመጣው መንገድ ቀርጀሌ የሚባል አካባቢ ተዘግቷል። ወደ አርባ ምንጭ መሔጃውም ወደ ሑምቦ አካባቢ ተዘግቷል። አረካም በሆሳዕና አድርጎ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል" ሲሉ የሶዶ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ጊንቺ በተባለች አነስተኛ የወላይታ ዞን ከተማ የሚገኙ የዐይን እማኝ ከዕሁድ ጀምሮ "ወደ ሶዶ መሔድ አይቻልም። መንገዱ ዝግ ነው" ብለዋል።