1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮሮና ወቅት በርካታ ሃገራት ረሐብ ተደቅኖባቸዋል

ዓርብ፣ ሰኔ 5 2012

የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ የበርካታ ሃገራት ምጣኔ ሐብት እንዲንኮታኮት ከማድረጉም ባሻገር የእጅግ ደሃ በኾኑት ላይ የረሐብ አደጋም ደቅኖባቸዋል። በአፍሪቃ እና እስያ ደሃ ሃገራት ዘንድ ምናልባትም ረሐቡ ከኮሮና ተሐዋሲው በባሰ የሰዎችን ሕይወት እንዳይቀጥፍ አስግቷል።

https://p.dw.com/p/3debD
Südsudan WFP Hilfe in Rubkuai
ምስል Reuters/S. Modola

ዘንድሮ ረሐብ የሚያጠቃቸው ሰዎች በእጥፍ ይጨምራል ተብሏል

የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ባስከተለው የምጣኔ ሐብት መንኮታኮት የተነሳ በዚህ ዓመት የበርካታ ሃገራት ነዋሪዎች ብርቱ የረሐብ አደጋ ከፊታቸው ተደቅኗል።  ዓለም ለዚህ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ «ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት ያልታየ የከፋ» የምግብ እጦት ቀውስ ሊከሰት ይችላል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስጠንቅቋል። 

ምንም እንኳን በአኹኑ ወቅት ዓለምን ለመመገብ በቂ የምግብ አቅርቦት ቢኖርም ኹሉም የመግዛት አቅም አለው ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪቃ የሚገኙ ሃገራት ከኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ባሻገር ተደጋጋሚ የበረሃ አንበጣ መንጋን ሲታገሉ ቆይተዋል። በዚያ ላይ የአየር ንብረቱም በነዚህ ሃገራት በተደጋጋሚ ጉዳት አድርሷል፤ ሥራ አጥነቱም ተባብሷል። እናም እነዚህ ኹሉ ሲደማመሩ የምግብ አቅርቦቱ ላይ ብርቱ ችግር በማስከተል በየጊዜው ወደሚከሰት የረሐብ አዙሪት ነዋሪውን ሊገፉ እንደሚችሉ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) የምጣኔ ሐብት ኃላፊው ማክሲሞ ቶሬሮ ተናግረዋል። «በተለይ በሚቀጥለው ዓመት ከፍተኛ የምርት መቀነስ ይከተላል። ያ ማለት ግን የምግብ አለመኖር ችግር ይከሰታል ማለት አይደለም። ዋነኛው ችግር ሰዎች ስለሚታመሙ ምርት ወደ ውጪ ሃገራት መላክ እና ማምረት ያቆማሉ። እናም ያ በሚቀጥለው ዓመት ችግር ይፈጥራል። ከዚያ ባሻገር ግን በግልጽ የምግብ አቅርቦት ችግር ነው የሚፈጠረው፤ ብርቱ የኾነ የምግብ አቅርቦት ችግር።»

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ መርሐ-ግብር አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን ውስጥ በጆንያ ምግብ ወደመሬት ሲልክ
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ መርሐ-ግብር አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን ውስጥ በጆንያ ምግብ ወደመሬት ሲልክምስል Reuters/S. Modola

የኮሮና ወረርሽ መጀመሪያ ላይ በተቀሰቀሰበት ወቅት ሃገራት እንቅስቃሴያቸውን ገትተው እንዲዘጋጉ በማድረጉ በዓለም ዙሪያ የምግብ ስርዓቱ ላይ አስደንጋጭ ኹኔታ ፈጥሮ ነበር። ገበሬዎች በየቤታቸው እንዲቆዩ በመደረጉ እና ሃገራት ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸው በተፈጠረው የሰው ኃይል እጥረት በሚሊዮን ቶን የሚገመቱ የምግብ እህሎች በየማሳዎቹ የሚያነሳቸው ጠፍቶ ባሉበት ረግፈው በስብሰዋል። በአኹኑ ወቅት ግን የምግብ አቅርቦት መረጋጋት ይታያል፤ በእርግጥ በአንዳንድ ሃገራት ዘንድ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለቱ ጥገና ያሻዋል።  

በዓለም ዙሪያ የበርካታ ሃገራት ድንበሮች በመዘጋታቸውም ችግሩ እየከፋ መኬዱ አይቀርም። በወረርሽኙ የተከሰተው የምጣኔ ሐብት መንኮታኮት ከተፈጥሯዊ ክስተቶች ጋር ተደማምሮ በዐሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ድህነት አረንቋ ሊገፋ እና ለረሐብ  ሊያጋልጥ ይችላል። ዓለም አቀፍ ድርጅቱ የምግብ እጥረት ስጋት የተደቀነባቸው ካላቸው ጥቂት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ ትገኛለች።

ስደተኛ ህጻን ከትልቅ ድስት ውስጥ ምግብ ፍለጋ
ስደተኛ ህጻን ከትልቅ ድስት ውስጥ ምግብ ፍለጋምስል picture-alliance/dpa

«የምግብ ቀውስ ከሚከሰትባቸው ሃገራት መካከል በርካታዎቹ ኹሉን አቀፍ በኾነ የምግብ እጥረት ደረጃ መለያ 3 ወይንም 4 ውስጥ ነው የሚገኙት። ይኼ ሃገራቱን ወደ 5 ሊገፋቸው ይችላል። ያ ማለት ሰዎች የሚሞቱበት ጠኔ ማለት ነው። በምሥራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ መንጋ መስፋፋት አስደንጋጭ ነው። እንግዲህ ኮቪድ-19 አለ፤ የምግብ ቀውስ እና በዛ ላይ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ። የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙን መቆጣጠር ከተሳነን፦ ኢትዮጵያ፣ ርዋንዳ እና ኬንያ ወደ ከፍተኛው ደረጃ ማለትም ወደ 4 አለያም 5 ደረጃ ሊያመሩ ይችላሉ።»

እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዘገባ ደግሞ ዓለማችን ምጣኔ ሐብቷ ዘንድሮ በ3 ከመቶ ዝቅ ብሏል። በውጭ ሃገራት ነዋሪ ከኾኑ ወደ እየ ሀገር ቤት ይላክ የነበረው የውጭ ምንዛሪ 20 ከመቶ ማሽቆልቆሉን ደግሞ የዓለም ባንክ አትቷል። በድህነት አረንቋ ውስጥ ነዋሪ የኾኑ በርካታ ዜጎች የእነዚህ እውጭ ሃገራት ነዋሪ የኾኑ ዜጎችን እጆች የሚጠብቊ ናቸው። ባለሞያዎች በድሃ ሃገራት ዘንድ የምግብ ቀውስን ለመታደግ የሚውል ገንዘብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችልም እያስጠነቀቊ ነው። የአፍሪቃ እና የእስያ በርካታ ሃገራት ምጣኔ ሐብታቸውን ለማነቃቃት ብርቱ የገንዘብ እጥረት ሊገጥማቸውም ይችላል። 

 የበረሃ አንበጣ መንጋ ኦልዶኒሮ ኬንያ አቅራቢያ የሚገኝ መንደርን ወሮ
የበረሃ አንበጣ መንጋ ኦልዶኒሮ ኬንያ አቅራቢያ የሚገኝ መንደርን ወሮምስል picture-alliance/AP Photo/FAO/S. Torfinn

የዓለም ምግብ ድርጅት ሚያዝያ ወር ላይ እንደተነበየው ከኾነ ዘንድሮ ረሐብ የሚያጠቃቸው ሰዎች በእጥፍ ጨምሮ 265 ሚሊዮን ይደርሳል። በዓለማችን ከሚኖሩ 100 ሰዎች ከ3 በላይ በየቀኑ ይራባሉ ማለት ነው። የምግብ እጥረት፤ ግጭቶች፤ የአየር መዛባት እና ወረርሽኝ ተደራርቦ ዓለማችን 821 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ በተለያዩ መንገዶች ለረሐብ ይዳረጋሉ ብሏል ዓለም አቀፉ ድርጅት። 

ከጥር ወር በፊት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የምግብ ቀውስ የተከሰተባቸው ሃገራት ዘንድሮም በግጭቶች እና ፖለቲካዊ አመረጋጋት የሚታመሱ ናቸው ብሏል። ከሃገራቱ መካከል ኢትዮጵያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሱዳን፤ ናይጀሪያ እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ይገኙበታል። እንደ የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት የቅርብ ዘገባ በኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ሶማሊያ፤ ጅቡቲ እና ኤርትራ የሚገኙ 18 ሚሊዮን ነዋሪዎች አንድም ምግብ ሙሉ ለሙሉ አልቆባቸዋል ወይንም ደግሞ በኾነ ጊዜ ቀኑን ሙሉ የሚቀመስ ሳይኖራቸው የሚውሉ ናቸው ብሏል። 
ማንተጋፍቶት ስለሺ/አጂት ኒራንጃን