1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮሮና ወረርሽ የተደናቀፈዉ የፕሬስ ነጻነት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013

ጀርመን በዓለማችን የፕሬስ ነፃነት መከበር ከሚታይባቸዉ የዓለም ሃገራት መካከል እስከዛሬ ከነበረችበት አስራ አንደኛ ደረጃ ወደ አስራ ሦስተኛ ዝቅ ተደርጋለች። ኢትዮጵያ ከ180 ሃገራት መካከል 99 ደረጃ ላይ ትገኛለች።    

https://p.dw.com/p/3sICY
Pressefreiheit Symbolbild
ምስል picture-alliance/EPA/N. C. Naing

በዓለማችን የኮሮና ተኅዋሲ መዛመት ከጀመረ ወዲህ ጀርመን ይታይ የነበረዉ ጥሩ የተባለለት የፕሬስ ነፃነት ማሽቆልቆሉን ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን «ሪፖርተርስ ዊዝአዉት ቦርደርስ» አስታወቀ። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በዚህ ዓመት የ 180 ሃገራትን የፕሬስ ነጻነት ጉዳይ ተመልክቶ ይፋ ባደረገዉ መዘርዝር፤ እስከዛሬ ጀርመንን ጥሩ ሲል ያስቀመጠዉን ዉጤት ዘንድሮ «አጥጋቢ » ሲል በደረጃ ዝቅ አድርጎታል። በጀርመን የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ዝቅ ያለበት ምክንያት ኮሮናን ለመከላከል በሃገሪቱ የወጣዉን ጥብቅ የዝዉዉር ገደብን ተከትሎ በተካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ጋዜጠኞች ላይ በደረሰ ወከባ ምክንያት መሆኑም ተመልክቶአል። በዚህም ጀርመን በዓለማችን የፕሬስ ነፃነት መከበር ከሚታይባቸዉ የዓለም ሃገራት መካከል እስከዛሬ ከነበረችበት አስራ አንደኛ ደረጃ ወደ አስራ ሦስተኛ ዝቅ ተደርጋለች። ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ዘንድሮ ጥናት ካካሄደባቸዉ 180 ሃገራት መካከል ኖርዌይ፤ ፊላንድ እና ስዊድን የፕሬስ ነጻነት የሚከበርባቸዉ የዓለማችን ቀዳሚዎቹ ሃገራት ሲሆኑ፤ቱርክሜኒስታን፤ ሰሜን ኮርያ እና ኤርትራ ደግሞ የፕሬስ ነጸነት የተደፈለቀባቸዉ የመጨረሻዎቹ ሃገራት ናቸዉ ተብሎአል። ኢትዮጵያ ከ180 ሃገራት መካከል 99 ደረጃ ላይ ትገኛለች።