1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በካማሺና በመተከል አብዛኛው ነዋሪ ርዳታን ይሻል

ቅዳሜ፣ ጥር 7 2014

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺና መተከል ዞኖች አርሶ አደሮች ምርታቸውን ሳይሰበስቡ ተፈናቅለዋል። የጸጥታ ችግር በሚታይባቸዉ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ተረጅ ሆነዉ ይቀጥላሉም ተብሏል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈዉ ጥቅምት ወር ይፋ ባደረገዉ መረጃ በሦስት ዓመታት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 490 ሺ በላይ ደርሷል።

https://p.dw.com/p/45XEf
Äthiopien Assosa Flüchtlinge
ምስል Negassa Dessalegn/DW

በክልል ደረጃ እስካሁን ከ 11 ሚሊዩን በላይ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተካሄደው የምርት አሰባሰባብ ሂዴት እስካሁን 11 ሚሊዩን ኩንታል ያህል ምርት በክልል ደረጃ መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጸዋል፡፡ በ2013/14 የምርት ዘመን በጸጥታ ችግር ምክንያት  በምርት ለመሸፈን ከታቀደው  1 ሚሊዩን ሄክታር መሬት መካከል ግማሹ ብቻ  በምርት መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ  ተናግረዋል።

ያነጋገርናቸው በካማሺ እና መተከል ያሉ አርሶ አደሮችም ባለፈው ዓመት ያመረቱት ምርታውን ሳይሰበስቡ መፈናቀላቸውን፣ሌሎች ደግሞ ከተፈናቀሉ ረዥም ጊዜያት እንደሆናቸው ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የጸጥታ ችግር ያለባቸው ስፋራ ያሉ አርሶ አደሮች ተረጅ ሆኖ ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የጥቅምት ወር መረጃ መሰረት በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 490ሺ በላይ መድረሱን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Young Graduates in  Benishangul Gumuz Complain of unemployment
ምስል Negassa Desalegn/DW

በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ 5መቶ ሺ በላይ ሄክታር መሬት በምርት መሸፈኑን እና 31 ሚሊዩን ኩንታል ምርት ደግሞ ለመሰብሰብ ታሳቢ በማድረግ ስራ መጀመራቸውን  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ ተናግረዋል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ከ 1 ሚሊዩን በላይ ሄክታር መሬትን በምርት ለመሸፈን ታቅዶ የነበረ ቢሆን በተስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ በዕቅዱ መሠረት አለመከናወኑን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን 11 ሚሊዩን በይላ ኩንታል ምርት በክልል ደረጃ  መሰበሰቡን እንዲሁም እስከ 18 ሚሊዩን ኩንታል በሁሉም ዞኖች ለመሰብሰብ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

 በክልሉ ካማሺ ዞን እና መተከል አብዛኛው ስፍራዎች አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት ምርት አለመሰብሰቡን እና በዘንድሮ ዓመትም በስራ ላይ አለመቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በበተለይም ካማሺ ኣበዛኛው  አካባቢዎች  አለማምረታቸውን እንዲሁም ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚሹ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አብራርተዋል፡፡

 የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፎ አቶ ባበክር ሀሊፋ በካማሺና መተከል አብዛኛው  ነዋሪ በጸጥታ ችግር ምክንያት በስራ ላይ አልነበረም ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ያነሱት ሀሳብ ትክክለኛ መሆኑን ጠቅሰው በርካታ ነዋሪም ድጋፍ እንደሚሹም አረጋግጠዋል፡፡ በካማሺ 265ሺ ሄክታር መሬት ለማልት ስራ ቢጀመርም በዓመቱ 60ሺ ሄክታር መሬት ያህል ብቻ መልማቱንም አመልክቷል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በሰጡን ማብራሪያ በካማሺ ዞን ወደ መጠለያ ጣቢያ የገቡ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ ከ5ሺ በላይ ተፈናቃዩች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ለመስኖ ልማት  ምቹ በሆኑ ስፋራዎች  ጀነሬተሮችም የተሰራጩ ሲሆን በካማሺ ደግሞ ለጊዜ አለመድረሱንም የግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ