1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በከረዩ አባገዳዎች ግድያ የኢሰመኮ መግለጫ

ረቡዕ፣ ጥር 25 2014

በኦሮሚያ ክልል በከረዩ አባገዳዎች ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ። ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥም ኮሚሽኑ አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/46QFe
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ጉዳት ለደረሰባቸው ተገቢው ካሳ እንዲሰጥ ኮሚሽኑ አሳስቧል

በኦሮሚያ ክልል በከረዩ አባገዳዎች ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ። ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥም ኮሚሽኑ አሳስቧል። 

ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የከረዩ ‘የሚችሌ ገዳ የጅላ’ አባላት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ስለመገደላቸው የሟቾች ቤተሰቦችና የአይን እማኞች በወቅቱ ተናግረው የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግስት ‘ሸነ’ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ግድያውን እንደፈፀመ አስታውቆ ነበር፡፡ ይሁንና ኢሰመኮ ከታኅሣስ 7 እስከ 12 ቀን፣ 2014 በቦታው ተገኝቼ አደረኩ ባለው ምርመራ ግድያውን የፈፀሙት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት የገዳ ስርዓት ከሚፈጽሙበት አርዳ ጅላ ተወስደው ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በማስታወስ ይጀምራል፡፡ ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 7 እስከ 12፤ 2014 ዓ.ም. ለ 6 ቀናት በቦታው በመገኘትና ተጎጂዎችን፣ የአይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማነጋገር ባካሄደው ምርመራ፤ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአይን እማኞች እንደነገሩት ኢሰመኮ አስረድቷል። 

ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከእነዚህ በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉ  የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16  ሰዎች  ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14 አባላት መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው መገደላቸውንና 2 ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ ሮጠው ማምለጣቸውን ተረድቷል። እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ ተከልክለዋል፡፡ አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ በመቆየታቸው በከፊል በዱር እንስሳ መበላታቸውን እንዲሁም ከጀርባ ወገባቸውና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩም ተገልጿል።  

በእለቱ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱት 39 የጅላ አባላት 23ቱ ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል ሕይወቱ አልፎ አስክሬኑ በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ለቤተሰብ መሰጠቱት፤ በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች ይታዩ እንደነበረ ከቤተሰብ መረዳቱን የገለጸው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ የተቀሩት ከሳምንታት በኋላ መለቀቃቸውን አክሎ አብራርቷል። 

ኢሰመኮ ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች በምርመራው እንዳረጋገጠም፤  ግድያው “ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ (extra judicial killing)” መሆኑን በሪፖርቱ አመልክቷል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት የተገደለው ተጨማሪ አንድ ሰው ላይም የተፈጸመው ግድያ የህግ ሂደትን የጣሰ ግድያ ነው ብሎታል። በመሆኑም በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት እና በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ወንጀሉን የፈጸሙና ያስፈጸሙት በሕግ ተጠይቀው ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ስለሁኔታው እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት ማደስ እንደሚጠበቅም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መምከራቸው በመግለጫው ተጥቅሷል።

ዶይቼ ቬለ ስለ ዛሬው የኢሰመኮ መግለጫ ከኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤህግ፣ ፖሊስ እና ከኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽብ ቢሮ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አዱኛ አህመድ ከዚህ በፊት በዶይቼ ቬለ ተጠይቀው በተፈጸመው ወንጀል ላይ ቢሮያቸው ምርመራ እንደሚያካሄድ ገልጸው ነበር። የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን በበኩሉ ግድያው በተፈጸመበት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል መንግስትን የሚዋጋው “ኦነግ ሸነ የሽብር ቡድን” ያለው አካል ግድያውን እንደፈጸመ ማሳወቁም አይዘነጋም፡፡ 

ሥዩም ጌቱ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ