1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን የጸጥታ ሁኔታ

ሰኞ፣ ጥር 9 2014

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች ግድያ እና ዘረፋ እየፈጸሙ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ። ከሰዮ ወደ አምቦ የሚወስደው መንገድ በታጣቂዎች መዘጋቱን የሰዮ ከተማ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ችግሩን ለመቅረፍ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን የገለጹት የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳሕሉ ድሪብሳ "ነገሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይተካከላል" ብለዋል

https://p.dw.com/p/45eKd
Äthiopien | Wahlen | Oromia

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን የጸጥታ ሁኔታ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተምዕራብ 250 ኪ.ሜ ገደማ ላይ የምትገኘዋ የዳኖ ወረዳ ዋና ከተማ ሰዮን መኖሪያቸው ማድረጋቸውን የሚገልጹት፤ ነገር ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ ከከተማዋ ውጪ ያሉት በርካታ ስፋራዎች ለመንቀሳቀስ ስጋት መሆኑን ነሳሉ፡፡ ታጣቂዎች በርካታ የወረዳው ገጠር ቀበለያትን በመቆጣጠራቸውም ወደ ከተማዋ ምንም አይነት ምርት እንደማይገባ በመግለጽ፤ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠለ አንድም የከተማ ነዋሪ ከመራብ አይተርፍም ብለዋል።
እንደ አስተያየት ሰጪው በወረዳው የገጠር ቀበለያቱ የአርሶ አደሩ ሃብት ይዘረፋሉ፤ የተወቃ እህልም ወደ ጎተራ አይገቡም፡፡ በወረዳው መድኃኒትና የትኛውንም ሸቀጣሸቀጥ ለማግኘትም ፈታኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሌላም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የአከባቢው ነዋሪ አየሁ ያሉትን እንዲህ በማብራራት አከሉ፡፡ እንደ የአይን እማኞቹ የአከባቢው ነዋሪዎች ገለጻ በየጊዜው ሰዎች ይገደላሉ፤ አንዳንዴም አንስተው ለመቅበር እንኳ አይፈቀድላቸውም፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia

በወረዳው የመንግስት መዋቅር እና የፀጥታ ሃይሎች ምላሽ ምን እንደሚመስልም ነዋሪዎቹን ጠየቅናቸው።
በነዋሪዎቹ ስጋትና እሮሮ ላይ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳህሉ ድሪብሳ ጋ ደውለን ስለ ሁነታዎቹ አንስተንላቸዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪውም በዞናቸው በርካታ ወረዳዎች እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት ኦነግ ሸኔ ያሏቸው ታጣቂ ቡድን በዚ የዳኖ ወረዳም እንደሚንቀሳቀስና በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ያሉት ሰቆቃ እንደሚያደርስ ይታወቃል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆኑ የተቀናጀ ያሉትን እርምጃ በታጣቂዎች ላይ የመውሰድ ስራ እተከናወነ ነውም ብለዋል። የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳህሉ ታጣቂዎችን የብሔር ግጭት ለማስነሳት ጥረት እንደሚያደረጉም በማመልከት፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ ግን ግድያ እንደሚፈጽሙም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጣቸው መግለጫዎች ታጣቂዎች በተለያዩ አከባቢዎች ላይ ከሚያደርሱት ጥቃት ባሻገር፤ በኦሮሚያ አንድም በታጣቂዎች ስር የሚገኝ ቀበሌ አለመኖሩን ያወሳል፡፡ የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡት ግን በክልሉ በታጣቂዎች ብቻ ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ መፈናቀሉን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ