1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእርግጥ የሱዳን የለውጥ ሙከራ ለዓለም ተምሳሌት?

ቅዳሜ፣ የካቲት 21 2012

ጀርመን ሙይኒክ ከተማ ውስጥ በተደረገው የጸጥታ ጉዳይ ጉባኤ ላይ የሱዳን ጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዱክን የዶይቸ ቬለዋ ዓያ ኢብራሒም ስለ ሱዳን የሲቪል እና ወታደራዊ የጋራ መንግሥት፤ የፍትህ ሒደት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ቃለ መጠይቅ አድርጋላቸዋለች። በዝርዝር መልስ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/3Yc7Z
Deutschland Berlin PK sudanesischer Premierminister Abdalla Hamdok und Angela Merkel
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሥትር ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ

ከሁለት ሳምንት በፊት ጀርመን ሙይኒክ ከተማ ውስጥ በተደረገው የጸጥታ ጉዳይ ጉባኤ ላይ የሱዳን ጠቅላይ ሚንሥትር አብደላህ ሐምዶክን የዶይቸ ቬለዋ ዓያ ኢብራሒም ስለ ሱዳን የሲቪል እና ወታደራዊ የጋራ መንግሥት፤ የፍትህ ሒደት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ቃለ መጠይቅ አድርጋላቸዋለች። ለዶይቸ ቬለ ቴሌቪዥን በእንግሊዝኛ የተላለፈውን ዝግጅት እንደሚከተለው ለሬዲዮ በሚመች መልኩ ተርጉመን አቅርበንላችኋልን። 

ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሥትር  አብዳላ ሐምዱክ በመጀመሪያ የቀረበላቸው ጥያቄ፦ በታሪካዊ አጋጣሚ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች በምትገኘው ሀገራቸው የመሪነቱን ሥፍራ ለመያዙ ጥርጣሬ ገብቷቸው እንደሁ ነው። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ሲመልሱ አንዳችም ጥርጣሬ እንዳልነበራቸው በመጥቀስ፤ እንደውም ኃላፊነት መውሰዱን ከስንት አንዴ ከሚከሰት የዓለማችን ታሪካዊ አጋጣሚዎች  ጋር አመሳስለውታል።

Bundespräsident Steinmeier im Sudan
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

ሐምዱክ፦ በእውነቱ ይኼ የግል ምኞትም አይደለም። ይኼ ኃላፊነትን ለመወጣት ለተላለፈው ጥሪ መልስ ነው። ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ደግሞ አንዳችም ጥርጣሬ አልገባኝም፤ በተግዳሮቶች የተሞላ፤ እጅግ ተቀያያሪ፤ አንድ ወጥ ያልኾነ መኾኑን በሚገባ እያወቅኹትም ቢኾንም ማለት ነው።  ዛሬ ቢኾንልሽ ጋሬጣው እና መሰናክሉ ነገ ይጠብቅሻል። ይህን ሥራ መቀበል ለሀገሪቱ ጥሪ  ምላሽ ነበር። በተለይ በእኛ ሀገር ታሪክ የለውጥ ሒደት ከስንት አንዴ የሚከሰተውን አጋጣሚ የሀገሬ ሰው ለዓለም ሕዝብ ማሳየት ለቻለበት አጋጣሚ ምላሽ ነበር። ይኽ ታሪካዊ አጋጣሚ ከበርሊን ግንብ መደርመስ ጋር፤ ከስንት ዘመናት ወዲያ ደግሞ ከፈረንሳይ አብዮት ጋር አቻ ነው። ያ ቅጽበት ለእኔ እና ለበርካቶች መጥተን አዲሲቱን ሀገር ለመገንባት ምቹ ኹኔታን ፈጥሮልናል። አኹን ንጋት ነው።

ሚያዝያ ወር ላይ ከሱዳን ወታደራዊ እዝ ፊት ለፊት የመቀመጥ አድማ ሲደረግ በቦታው በርካታ ሰዎችን እንዳየች በመግለጥ አኹን ያለው የሱዳን መንግሥት የተቃውሞ አድራጊዎችን ምኞት እያሳካ እነደኹ ጋዜጠኛ ዓያ ጠቅላይ ሚንሥትር ሐምዱክን ጠይቃቸው ሲመልሱም ቀጣዩን ብለዋል።

እኛን እንዲህ ያነቃቃንም ይኸው ተስፋ፤ አንዳች ነገር መጠበቃችን፤ መንግሥቱ በሕዝባችን የመለወጡ ነገር ነው። ይኽን በራሳችን ብቻ ለማድረግ ፈጽሞ ቃል አልገባንም። ይኽ የጋራ ኃላፊነት ነው። በሒደቱ የምንነሳውም የምንወድቀውም በጋራ  ነው፤ ያሉን ኹለት አማራጮች ናቸው ብለን ቆርጠናል፦ ወይ ስኬት አለያም ስኬት ነው በሚል። እናም እንደሚመስለኝ ወደዚያው መንገድ እያቀናን ነው። 

ኾኖም በርካታ ሱዳናውያን ወጣቶች ወደ ጎዳና ያወጣቸው የዳቦ ጥያቄ የመሠረታዊ ሕይወት ጥያቄ ዛሬም መልስ እንዳላገኘ ይናገራሉ። እናስ ሕዝቡ ከለውጡ ይጠብቅ የነበረው እጅግ ከፍ ያለ ነበር ማለት ነው? ጠቅላይ ሚንሥትሩ አጭር መልስ አላቸው።

ይጠብቁ የነበረው ፈጽሞ እጅግ የበዛ አልነበረም። በየትኛውም መንግሥት በየትኛውም ሕዝብ የሚጠበቅ አይነት ነበር። ግን ደግሞ የተረከብነው ለ30 ዓመታት የዘለቀ ተስፋ አስቆራጭ ተግዳሮት መኾኑን ተረድተው እንደሚያበረታቱንም እርግጠኛ ነኝ። በአንድ ጀምበር መቀየር የሚቻል አይደለም፤ ይልቁንስ ከሕዝባችን ጋር በቁርጠኝነት እና በትጋት ሠርተን የምናሳካው ነው። ያን በማድረግ እነዚህን ተግዳሮቶች እንደምንወጣ አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም።

Bundespräsident Steinmeier im Sudan
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

በሕይወታቸው ላይ  በአኹኑ ወቅት አንዳች ለውጥ ፈልገው ምናልባትም መታገሱ የረዘመ ለመሰላቸው  ወጣቶች የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሥትር  አንዳች ነገር መፈለጉ የመንግሥታቸውም ጭምር መኾኑን ነው የሚናገሩት።

ይኽን ጉዳይ በተመለከተ ማለት የምፈልገው አንድ ነገር በጋራ እንሥራ ነው። አንዳች ነገር መጠበቁ አንድ ነገር ነው። ግን እስኪ ይኽን አንዳች ነገር መጠበቅ በጋራ መልስ እንስጠው። ፍላጎታችን የጋራ ነው።  እኛ ከሕዝቡ የተለየ ፍላጎት የለንም። የምንጠብቀው እንደ ሕዝቡ ነው። እናም እነዚህን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ ኃይላት በሙሉ እንሰባሰብ ነው የምለው።

ሱዳን በአኹኑ ወቅት የምትመራበትን ለየት ያለ የሲቪሉ እና የወታደሩ ክፍል ጥምር መንግሥት በተመለከተ ተጠይቀውም ጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዱክ ይኽ የሱዳን ሙከራ ዲሞክራሲን በመገንባቱ ረገድ ለሌሎችም አብነት ሊኾን የሚችል ነው ብለዋል።  ወታደሩ ከሲቪሉ ጋር ተጣምሮ በመንግሥት ውስጥ መሥራቱ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም በኹለቱም ወገን ያለው ቁርጠኝነት ግን ወደ ስኬት ሊያመጣቸው እንደሚችል ነው የሚያምኑት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሥትር። በየትም ቦታ በተደላደለ መንገድ የሚጓዝ ለውጥ የለም ያሉት አብዳላ ሐምዱክ ሱዳን የጀመረችው ለየት ያለ የመንግሥት አስተዳደር ሙከራ እጅግ ሳቢ ነው ብለዋል።

በእርግጥ የሲቪሉን ማኅበረሰብ ለሚወክሉት  አብደላህ ሐምዱክ በመንግሥታቸው ስር የታቀፈውን ወታደራዊ ክፍል ያምኑት ይኾን?

አዎን፤ ይኽም እኮ ነው የሱዳናውያን የአስተዳደር ሙከራን ለየት ያለ ጠባይ እንዲኖረው ያደረገው። ይኽንንም ዲሞክራሲን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት የተጀመረውን የሲቪሉ እና የወታደሩ ትብብር የሱዳን ሞዴል ብለን ለዓለም በኩራት ማቅረብ እንሻለን። ይኽ ትብብር የሚሠራ ነው። ከትግዳሮቶች የጸዳ አይደለም። በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። ስኬታማ እንዲኾን ግን በኹለታችንም በኩል ቊርጠኝነቱ አለ፤ የምንተገብረውም በትክክል ያንን በማጤን ነው። በአካባቢያችን ያሉ ሃገራትን ብትመለከቱ ብዙ ቦታዎች ላይ ክሽፈት ይታያል፤ ያም የኾነው ሀገሪቱን ለማራመድ እንዲህ ያለ ትብብርን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነትን  መፈጸም ባለመቻላቸው ይመስለኛል። እኛ እዚያ ላይ ሙከራ እያደረግን ነው። አልጋ በአልጋ የኾነ ለውጥ የለም። ለውጥ ምንጊዜም የተተረማመሰ፤ ወጣ ገባ ነው እናም ያ በራሱ የሙከራው አካል ለመኾን ይበልጥ አጓጊ ያደርገዋል።

Sudan Neuer Premierminister Abdalla Hamdok
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

እንደ አብዳላ ሐምዱክ አባባል፦  አብረው በሚሠሩት ወታደራዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ እምነት አላቸው።  ግን ደግሞ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው አንዳንድ ወጣቶች ይኸው የወታደር ክፍል አንዳንድ ቦታዎች ላይ በርካታ ተቃዋሚዎችን በመግደል ጭቆና በማስፈን እጁን አስገብቷል ሲሉ ቅሬታ ያሰማሉ። አብዳላ ሐምዱክ ለዚህም መልስ አላቸው።

በወጣቶቻችን ለሚገለጠው ምልከታ አድናቆት አለኝ። አስታውሱ፦ እነዚህ ወጣቶች እኮ ናቸው ለኹሉም አይነት ጭቆና ተጋልጠው የነበሩት።  ያንም በነዚያ ዐሥርተ-ዓመታት በጎዳናዎቹ የኖረው ወጣት ያውቀዋል። ለዚያም እኮ ነው ይኽ ምልከታ ያለን። እንደሚመስለኝ ግን ይኽን የጋር ትብብር እንገነባዋለን። ይኽችን አዲስ ሀገር ለመገንባት አንዳችንም በራሳችን መንገድ ብቻ መሄድ አይቻለንም። እነዚያን ምልከታዎች አደንቃለሁ ግን ምላሽ ለመስጠት በጋራ እየሠራን ነው።

በሰኔው የቁጭታ አድማ ግድያ የፈጸሙ ወታደሮች ጉዳይ በኮሚቴ እየታየ መኾንን ውጤቱንም በሱዳን «የተከበሩ» ካሏቸው ጠበቆች ከተዋቀረው ኮሚቴ በቅርቡ እንደሚጠብቁ ጠቅላይ ሚንሥትር አብደላ ሐምዶክ ዐስታውቀዋል።

የቀድሞው የሀገሪቱ የረዥም ዘመን ፕሬዚደንት ዑመር ሐሠን አህመድ አል በሽር ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በፈለገው መንገድ ኔዘርላንድ በሚገኘው ዘ ሔግ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ አለያም እዛው ሱዳን ውስጥ ባለ የፍርድ ሒደት የሚታይ ጉዳይ መኾኑን ጠቁመዋል። በደል የደረሰባቸውን ሰዎች በሚክስ መልኩ ግን ፍትኅ እንደሚሰፍን ቊርጠኝነታቸውን ዐሳውቀዋል። 

በጀርመን ቆይታቸው ከመራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዱክ በሱዳን እና በጀርመን የኹለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውን ውይይቱም ፍሬያማ እንደነበር ተናግረዋል። ጀርመኖች ሱዳን ውስጥ በምጣኔ ሐብቱ በመሳተፍ፤ የሞያ ሥልጠናዎችን ለመስጠት፤ በማዕድን ማውጣት እና የግብርናው ዘርፍ ሴሚናሮችን ማካፈል መሻታቸውን ተናግረዋል። ሐብታም ባሏት ሀገራቸው ሱዳን ውስጥ የመዋዕለ-ንዋይ አፍሳሾችን ቀልብ ሊስብ የሚችል ድባብ ለመፍጠር እየተጉ መኾናቸውንም ገልጠዋል።

Sudan Neuer Premierminister Abdalla Hamdok
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

ጠቅላይ ሚንሥትሩ፦ ሕዝባዊ ዓመጾች እና እንቅስቃሴዎችን በሚያስተናግዱ በርካታ ሃገራት በተከበበችው ሱዳን ለውጡ በሀገራቸው ከሌሎቹ ለየት ያለ መሀል ላይ የሚገኝ መኾኑን ተናግረዋል። እናም በሀገራቸው የተጀመረውን ለውጥ ስኬታማ ለማድረግ ወዳጆቻቸው እና ተባባሪዎቻቸው አብረዋቸው መሥራቱን ማየት እንደሚሹም እምነታቸው መኾኑን ገልጠዋል። እናስ ጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዱክ «የሱዳናውያን ሙከራ» ያሉት የወታደራዊ እና የሲቪሉ ጥምር መንግሥት አስተዳደር የበርካቶችን ፍላጎት አሟልቶ በእርግጥ ጠቅላይ ሚንሥትሩ እንደሚመኙት የሌሎችም ተምሳሌት ይኾን? ያ ወደፊት የሚታይ ነው።

አንድ ነገር እርግጠኛ መኾን ይቻላል። ሱዳናውያን ለዘመናት ተጭኗቸው የነበረውን ብቸኛ የወታደራዊ አገዛዝ ለጊዜውም ቢኾን ከሲቪሉ ጋር መቀየጥ ችለዋል። ለዚያም ፊቱን አዙሮባቸው የከረመው የምዕራቡ ዓለም ቀርቧቸዋል። የጀርመን የምጣኔ ሐብት እና የልማት ሚንሥትር ጌርድ ሙይለር በሱዳን ለትምህርት ጉዳዮች ማስፋፊያ 80 ሚሊዮን ዩሮ ሀገራቸው መፍቀዷን በቅርቡ ዐሳውቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ