1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
እምነትአፍሪቃ

በኢትዮጵያ የፀጥታ ሥጋትና መንግሥት

እሑድ፣ ጥር 28 2015

በኢትዮጵያ የግለሰቦችና ተቋማት ደኅንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ እያነጋገረ ነው። የሰሜን ሸዋው ጥቃትና ግድያ ጥቁር ጠባሳ ሳይሽር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ላይ በሻሸመኔ «ፖሊስ በወሰደው ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል» እንደተፈጸመ ሲኖዶስ ገልጧል። (ሐሙስ የተካሄደውን ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማድመጥ ይቻላል።)

https://p.dw.com/p/4N5c0
Infografik Karte Äthiopien AM

ወከባና ግድያው ቀጥሏል

በኢትዮጵያ የግለሰቦች እና ተቋማት ደኅንነት ብሎም ጥበቃ ከምን ጊዜውም በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ከሰሞኑ በድጋሚ አገርሽቶ በነበረው የሰሜን ሸዋው ጥቃትና ግድያ ብሎም ከፍተኛ የንብረት ውድመት ጥቁር ጠባሳ ሳይሽር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ላይ ሻሸመኔ ውስጥ «ፖሊስ በወሰደው ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል» እንደተፈጸመ ሲኖዶስ ገልጧል። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግሥት ፀጥታ አካላት ውድመቱን በጊዜ ለማስቆም ሲጥሩ ዐይታይም በሚልም ይወቀሳሉ። ብዙዎች በሀገሪቱ ሕግ እና ሥርዓት ሊከበር ሲገባ መንግስት ችላ ብሏል ሲሉ አጥብቀው ይተቻሉ።

በዚህ ረገድ፦ ካሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ሕግጋትን ጥሰዋል በሚል ያወገዘቻቸው አካላት ቤተክርስቲያን ላይ አደጋ ደቅነዋል፤ መንግሥት ለቤተክርስቲያኒቱ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ስትል ብታሳስብም፤ አለመተግበሩ እንዳሳሰባት ገልጣለች። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሳምንት ቤተክርስቲያኒቱን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር፦ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችን እና ምእመናን እጅግ አስቆጥቷል። ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን መብት የማያከብር ከሆነ ሀገር አቀፍም ሆነ በመላው ዓለም ቅዱስ ፓትሪያሪኩን ያካተተ ሰላማዊ ሰፍል እንደሚጠራ አስጠንቅቋል። የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሕይወት እጅግ አስጊ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይዘገባል። መንግሥት ለአንድ ወገን እያደላ ነው በሚልም በብርቱ ይተቻል።

በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው። 

  1.  ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም እና ሰብአዊ መብት እንዲሁም የሕግ መምሕር እና ተመራማሪ 
  2.  አቶ ሙላቱ ገመቹ፦ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
  3.  አቶ አመሓ መኮንን፦ የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበር ዋና ኃላፊ እንዲሁም
  4. አቶ ያሬድ ኃይለ ማሪያም፦ የሕግ ባለሞያ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማእከል ዋና ኃላፊ ናቸው

ውይይቱ የተካሄደው ሐሙስ ዕለት መሆኑን በድጋሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

ሙሉውን ውይይት ከድምፅ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ