1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ላይ የመከረው የፍራንክፈርት ውይይት 

ረቡዕ፣ ጥር 20 2012

ባለፈው ሳምንት በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ምርቶች ኢንዱስትሪን ዘርፍ በጥራትና በተፈላጊነት ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያለመ ውይይት ተካሒዷል። በውይይቱ የጀርመን አምራቾች፣ የንግድ ጥናት ምርምርና አማካሪ ድርጅቶች፣ ኢትዮጵያውያንና በዘርፉ ተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።   

https://p.dw.com/p/3WyMx
Äthiopien Eröffnung der ITACA Textilfabrik in Tigray
ምስል DW/M. Haileselassie

በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ላይ የተደረገዉ ውይይት 

የጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና የኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪቃውያን የጀርመን ንግድ ማህበርና አምራቾች የንግድ ሥራ አፈፃፀማቸውን እንዲያሻሽሉ ሙያዊ ፣ የቴክኒክና የምክር አገልግሎት ከሚያበረክተው ዓለማቀፉ የሲስተምስ ፎር ቢዝነስ ሶልሽንስ ድርጅት ጋር በመተባበር በኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ለተሰማሩ የጀርመን አውራቾች፣  ለንግድ ጥናት ምርምርና አማካሪ ድርጅቶች ፣  ለኢትዮጵያውያን እና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ባለፈው ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም በፍራንክፈርት ከተማ ባዘጋጁት የ 2020 ዓ.ም የኢትዮጵያ የፓይለት ፕሮጀክት ወርክሾፕ ከዘንድሮው የአውሮጳውያን ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ምርቶች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በጥራትም በዓለማቀፍ ገበያ ተፈላጊነትም ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ለበርካታ የአገሪቱ ዜጎች አማራጭ የስራ ዕድልን ለመፍጠር በሚቻልበት ስልት ላይ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ውይይት አካሂደዋል። 
በዚሁ ወርክሾፕ የጀርመን የኢኮኖሚና ልማት ትብብር ሚኒስቴር የምስራቅ አፍሪቃ ልዑካኖችና የንግድና ኢንቨስትመንት ተወካዮች ፣ እንደ አጋቶን ኢንተርናሽናል እና ኦይለር ኤርሜስ ያሉ የንግድ ጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም የጨርቃጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ማሽነሪዎች አምራቾች፣  ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች፣  የጀርመን ሜካኒካል እና የኢንዱስትሪ ማሽኖች መገጣጠሚያ ምህንድስና ማህበር /VDMA/ ፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማካሪ ኤክስፐርቶች ፣ በጀርመን የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶች ተወካዮች በተጨማሪም በመስኩ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል:: የጀርመን የንግድና ኢንቨስትመንት ተወካዮች የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አጠቃላይ ገፅታ በዳሰሱበት የውይይት ርዕሰ ሃሳብ አሁን ላይ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ለውጥና መንግሥት የነደፈውን አዲስ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ለዓለማቀፍ ኢንዱስትሪዎች አመቺ መሆኑን ነው የገለፁት::
"በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ ከለውጡ ወዲህ መሻሻል ማሳየቱ የጨርቃጨርቅና ቆዳ ወጤቶች አምራች ድርጅቶችን የሳበበት ሁኔታ ፈጥሯል:: የጀርመን አምራች ካምፓኒዎች በቀጣይ ለሚኖራቸው እንቅስቃሴም የአገሪቱ መረጋጋት ወሳኝ ነው:: አልፎ አልፎ በአገሪቱ የሚታየው የሕዝቦች መፈናቀል፣ የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት፣ በፌደራልም ሆነ በክልል አስተዳደሮች ደረጃ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ውስብስብ  ሁኔታ ፣ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም የቢሮክራሲው ማነቆ በኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ዛሬ ላይ የመንግሥትን ትኩርት የሚሹ ችግሮች ሆነዋል:: " ሲሉ አብራርተዋል::
ጥናት አቅራቢ ተጋባዥ እንግዶቹ "የንግድ ስራ እና ባህላዊ አቀራረብ በኢትዮጵያ"፣  "የህግ እና የቀረጥ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ" ፣ "የጀርመን የንግድ አውራቾች የጤና እና አስተማማኝ ደህንነት በኢትዮጵያ" እንዲሁም "የምርት ሽያጭ ግንኙነት እና ሎጂስቲክስ በኢትዮጵያ" በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያም የመወያያ ሃሳቦች አቅርበው ስለ አገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጠቃሚ ግንዛቤን አስጨብጠዋል:: የጀርመን የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ሚኒስቴር በዓለማቀፉ የጀርመን የልማት ተራድዖ ድርጅት /GIZ/ አማካኝነት በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤት ምርቶች ደረጃቸውን በማዘመን ጥራታቸው እና በዓለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምር እንዲሁም ማህበራዊና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ባገናዘበ መልኩ የማኑፋክቸሪንግ ክፍለ ኢኮኖሚውን ዘርፍ ዘላቂነት እና ዋስትና ለማረጋገጥ በተለይም እንደ ሃዋሳ እና መቀሌ ባሉ የኢንዱስትሪ ዞኖች ከተለያዩ የውጭ አምራች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከፍተኛ በጀት መድቦ የፓይለት ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እንቅስቃሴ ሲያከናውን ቆይቷል:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2016-2020 ዓ.ም ለሚዘልቀው ለዚሁ መርሃግብሩ ማስፈፀሚያም ከፍተኛ በጀት የተመደበ ሲሆን ከኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው በዚሁ የልማት ትብብርም የአገሪቱ የቆዳና የቆዳ ቴክኖሎጂ ምርቶች የወጭ ንግድ ከያዝነው የአውሮጳውያኑ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 1 ቢልዮን ዶላር ከፍ እንዲል ለማስቻል እና እስከ ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም ከ 350 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች በመስኩ ተጨማሪ የስራ ዕድልን የመፍጠር ዕቅድ አለ::
"የአፍሪቃን የቢዝነስ እና ማርኬቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም ፓይለት ፕሮጀክቶችን" በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት በጀርመን የኢኮኖሚ ጉዳዮችና የኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ንግድ ቢሮ ተወካይ በበኩላቸው  ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ በሞሮኮ በጋና በግብፅ እና በሌሎችም የአፍሪቃ አገራት የተዘረጉት የፓይለት ፕሮጀክቶች የወጪ ንግድ ገቢን ከማሳደጉ በተጨማሪ አማራጭ የስራ ዕድልንም ከፍ እንደሚደርግ አረጋግጠዋል:: "አፍሪቃውያን በአገራቸው የተፈጥሮ ሃብታቸውን ተጠቅመው በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እገዛ የስራ ዕድል እና የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲያስመዘግቡ ማገዝም የእኛ ሃላፊነት ነው" ብለዋል ኃላፊዋ:: ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች የሚቀርብው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት መኖሩ በጭርቃጨርቅ አልባሳትና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ኢንዱስትሪው ፈታኝ መሆኑ በስብሰባው ላይ መወሳቱን የሚገልፁት በጀርመን ከ 37 ዓመታ በላይ የኖሩትና በባድ ሾንቦርን ከተማ የግላቸውን የቢዝነስ አማካሪ አገልግሎት ቢሮ ከፍተው ኢትዮጵያ ውስጥ ንዋያቸውን ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የዓለማቀፍ እና የጀርመን ባለሃብቶች ሙያዊ መረጃ እንዲሁም የምክር አገልግሎት የሚሰጡት ዶክተር ቅድስት ኃይሉም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግና የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እንዲህ ዓይነቶቹ መሰረታዊ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት::
የጀርመን የልማት ተራድዖ መረጃ እንዳመለከተው መንግሥት የነደፈውን አዲስ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ተከትሎ ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት ውስጥ 65 ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ተመዝግበዋል ፡፡ይሁን እንጂ የፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም በመስኩ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል አለመኖርና እንደ ኬሚካሎች ባሉ ጥሬ ዕቃዎች እጥረት የተነሳ ከ 40-45 በመቶ የተወሰነና ዘገምተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም:: በተለይም በኢትዮጵያ ለምርት ግብአቱ ከሚያስፈልጉት ቁሳቁሶች ውስጥ 40 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የተቀሩት 60 ከመቶ የሚሆኑትን ግን ከውጭ የማስመጣቱ ጉዳይም ሌላው ለዕድገቱ ማነቆ ሆኖ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው፡፡ይህም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የምርት ሂደቱ ከ 45 እስከ 60 ቀናት ረዘም ያለ ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል፡፡ሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከገጠሙት ተድጋሮቶች መካከልም በተለይም ለግብይት ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራሮች አለመጠናከር እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የጨርቃጨርቅና ቆዳ ውጤት ምርቶቹን የሚገበዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢንዱስትሪዎቹ ለተፈጥሮ ሃብት ለአካባቢ ብክለት ለመሰረተ ልማትና ለማኅበራዊ ጉዳዮች የሚሰጡትን ትኩረት ግምት ውስጥ ማስገባታቸው የሚጠቀሱ ናቸው ::  በኢትዮጵያ የዘርፉን ኢንዱስትሪ ለማጠናከርና ተግዳሮቶቹን ለመቅረፍ በመከረው የፍራንክፈርቱ ወርክሾፕ የተሳተፉት በጀርመን ከ 30 ዓመታት በላይ ነዋሪ የሆኑትና በንግድ ሙያ የተሰማሩት አቶ አስናቀ የማነብርሃን እንዲህ ዓይነቱ የመረጃ ልውውጥ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት::

Äthiopien Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa
Äthiopien Industriepark Hawassa
ምስል Imago/Xinhua/M. Tewelde
Äthiopien Textilindustrie Fabrik H&M Produktion
ምስል Jeroen van Loon

የጀርመኑ ዓለማቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት በምህፃሩ GIZ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ክልሎች በመንግስት ወጪ በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የዘረጋቸው ፓይለት ፕሮጀክቶች ስኬት ማስመዝገባቸው ነው የተነገረው:: ለአብነትም  ከዋና ከተማዋ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 270 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በሀዋሳ ከተማ 300,000 ነዋሪዎችን በዚህ የኢኮኖሚ ዘርፍ  ለማሳተፍ የተያዘው ዕቅድም ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፡፡ አሥራ ስምንት ዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በአካባቢው የገበያ ሱቆችን ያቋቋሙ ሲሆን ለ 20,000 ያህል የአካባቢው ነዋሪዎችም የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል ፡፡ ዓለማቀፍ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ እና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ዓብይ ምክንያት የሆናቸው እንደ ቻይና ባሉ የኤስያ አገራት በዘርፉ ልምድና ስልጠና ላላቸው ሰራተኞች የሚከፈለው ክፍያ ከአፍሪቃውያ ጋር ሲነጻጸር እየናረ መሄድ፥ እንደ ጥጥ ያሉ ለምርት ግብዓት የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች በአገሪቱ በብዛት መገኘት፥ ለውሃና ለኃይል ፍጆታ አቅርቦት ወጪ የሚከፈለው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑና ከፍተኛ አምራች የሰው ኃይል በአገሪቱ መኖሩ ፣ ምርቶቹን ወደ አውሮፓ ገበያ ለማጓጓዝ አጭር የትራንስፖርት መስመር አማራጭ መጠቀማቸው እና በኢትዮጵያ የፖለቲካው ሁኔታ አንጻራዊ መረጋጋት ማሳየቱ መሆኑ በንዑስ ክፍለ ኢኮኖሚው ዘርፍ ቴክኖሎጂያቸውን እና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ነው ጥናቶች ያረጋገጡት:: በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት የኢኮኖሚ እና የመሰረተልማት ጉዳዮች ቆንስል ወይዘሮ ኡባህ መሃመድ ሁሴን በበኩላቸው የጀርመን ኢንዱስትሪ ተወካዮች እና የንግድ ጥናትና ምርምር ኤክስፐርቶቹ በመድረኩ ላይ ላነሷቸው ቅሬታዎች መንግሥት ልዩ ትኩት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ነው የገለፁት::
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንታቸውን ካስፋፉ ዓለማቀፍ ከባንያዎች መካከል የጀርመኑ ቺቦ ድርጅት ተጠቃሽ ነው:: ዋና መሰረቱን በጀርመኗ የወደብ ከተማ ሃምቡርግ ያደረገው ቺቦ ኩባንያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተቆልቶ የታሸገ ቡና ለተለያዩ አገራት ሸማቾች በመሸጥና ጥራት ያለውን የኦርጋኒክ /መደበኛ/ ጥጥ ለዓለም ገበያ በማቅረብ በዓለም የ3 ኛ ደረጃን ይዟል::ሌላው የጀርመን የጨርቃጨርቅ ኩባንያ ኪክም የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ የጎላ ሚና በማበርከት ላይ ይገኛል:: በኢትዮጵያ የሚገኘው የአይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪም በርካታ የቺቦ ንግድ ምልክት ያለባቸውን ምርቶች ያመርታል:: ኩባንያው ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ፣ በሩዋንዳ ፣ በኬንያ እና በግብፅ የተመረቱ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ የጥጥ ካኔተራዎችን ፣ ጂንሶችን እና ልዩልዩ ጃኬቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረቡም በድርጅቱ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል:: ድርጅቱ የምርት ጥራቱን ለመጠበቅ ከ 2000 ሺህ ለሚልቁ በእነዚሁ አገራት ለሚገኙ ሰራተኞቹ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱም ታውቋል:: ከዚህ ሌላ በአውሮጳም ሆነ በመላው ጀርመን ታዋቂ የንግድ ስም ያላቸው ኤች.ኤንድ.ኤም ፣ ቴስኮ፣ ቤልክ፣ ዎልማርት እና ጋፕን የመሳሰሉ የጨርቃጨርቅ እና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪዎችም በኢትዮጵያ እንቅስቃሴ መጀመራቸው በወርክሾፑ ላይ ተገልጿል:: በቀጣይም የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር በተለይም አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በዕድገት ኋላ ቀር ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገራት ያመቻቹትን የቀረጥና ኮታ ነጻ የገበያ ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ሰፊ ዕድል ሊኖር ይችላል የሚል ዕምነት እንዳላቸው የውይይቱ ተካፋዮች ገልፀዋል:: አቶ እሸቱ ለገሰ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት የኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ቅንስልም በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ድርጅቶች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንደሚመቻች ነው ያረጋገጡት::
ለበርካታ ዓመታት እንደ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ቆዳና የቆዳ ልማት ውጤቶች 59 በመቶ ያህሉን የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርቶች በመግዛት ከአውሮጳ አገራት ቀዳሚ ስፍራ ያላት ጀርመን ፤ ለአገሪቱ የወጭ ንግድ ገቢ ጉልህ አስተዋፅዖ ስታበረክት ቆይታለች:: በቅርቡም ከኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በአገሪቱ በጨርቃጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ምርቶች ለተሰማሩ አምራች ድርጅቶች ገበያ ለማፈላለግ የሚያስችል ስምምነት ዓለማቀፍ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት የረጅም ዓመታት ልምድ ካካበተው የጀርመኑ ሜሰ ፍራንክፉርት ካምፓኒ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል:: ዘርፉ በርካታ የስራ ዕድሎችን ለአገሪቱ ዜጎች የሚፈጥር እንዲሆን ኢንዱስትሪውን በዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂ ማዘመን ፣ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት የመገንባትና የምርምርና ሥርፀትን ስራ ማስፋፋት ፣ለባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መስጠት ፣ ገበያ ማፈላለግ ፣ ሎጂስቲኩን ማጠናከር በተጓዳኝም ጥራት እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ምርት ለገበያ የማቅረብ ዕቅዶች መከናወን እንዳለባቸውም ነው የፍራንክፈርቱ ወርክሾፕ ምክረ ሃሳቡን ያቀረበው::

Äthiopien Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

እንዳልካቸው ፈቃደ