1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ምላሻቸው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተፈጥሮ ለሚከሰቱት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው ተገለጠ። በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ግዢ ተፈጽሞ እስከ ቀጣይ ታኅሣስ ወር መጀመሪያ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/41vhX
Südostäthiopien | Dürre in Borena
ምስል Seyoum Getu/DW

400 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ግዢ ተፈጽሟል

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተፈጥሮ ለሚከሰቱት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው ተገለጠ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ግዢ ተፈጽሞ እስከ ቀጣይ ታኅሣስ ወር መጀመሪያ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ብሏል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ እንዳሉት፤ ግዢው ከተፈጸመ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል በተጨማሪ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ለመግዛትም ሂደቱ ተጀምሯል። 

ሰሞኑን አነጋጋሪ ሆኖ የቆየው የቦረናው ዞን አስከፊ የድርቅ ክስተት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንስሳትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ በመሆኑ ኑሮያቸውን በዚሁ የሚመሩ ዜጎችንም ለችግር ስለመዳረጉ ነው፡፡ የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለዶይቼ ቬለ ለዚሁ ችግር ምላሽ ለመስጠት የመጀመሪያ ምዕራፍ ድጋፍ ወደ ስፍራው ተልኳል ነው ያሉት። 

Südostäthiopien | Dürre in Borena
ምስል Seyoum Getu/DW

በአከባቢው የሚያስፈልገውን የድጋፍ ደረጃ ለመለየት ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ተልከው መረጃ እያሰባሰቡ ነው ያሉት አቶ ደበበ፤ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዳሰነች ወረዳም በጎርፍ ምክኒያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ኮሚሽኑ ከ5 ሺህ 400 በላይ እህል ወደ ስፍራው መላኩን ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ሰውሰራሽ አደጋ (ጦርነት) ከዚህ በፊት ዝግጅት ለሚደረግበት የተፈጥሮ አደጋን ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አክብዶታልም ተብሏል፡፡ ይሁንና በጦርነቱ ምክኒያት ለሚፈናቀሉትም የተለያዩ ማዕከላት ተሰናድተው ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ኃላፊው አክለው ተናግረዋል፡፡

በሚከሰቱት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ድጋፍን ለሚሹ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት በመቶ ሺዎች ሜትሪክ ቶን የሚቆጠር እህል ታዞ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ የተቀናጀ ሥራ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጠዋል።

ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ