1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት» ለመፍጠር ቅድሚያ እንዲሰጥ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ 

ሰኞ፣ መስከረም 24 2014

"ለአመታት የሀገርን ኅልውና፣ የሕዝባችንን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደዚሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ሰንኮፎች በብሔራዊ መግባባት ሊፈቱ ይገባል" ያሉት ፕሬዝዳንቷ "ሆደ ሰፊነት፣ መተማመን፣ መመካከር፣ ኅብረት እና አንድነት፣ የውይይት እና የክርክር ባህሎችን ማዳበር" እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/41Eec
Sahle-Work Zewde
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ «ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር እና ማዳበር ተቀዳሚ» ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሔዱት የጋራ ጉባኤ ላይ አሳሰቡ። «ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በእጅጉ ተፈትናለች» ያሉት ሣህለ ወርቅ «ሉዓላዊነቷን፣ አንድነቷን፣ አብሮ መኖራችንን ለማናጋት ተሞክሯል» ብለዋል። 

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ንግግር ከማድረጋቸው በፊት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ኢትዮጵያን እንዲመሩ ተሾመዋል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ ውጤት መሠረት ብልጽግና ፓርቲ ዐቢይን ለጠቅላይ ምኒስትርነት አቅርቦ ሹመታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። 

ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ታገሰ ጫፎ አፈ-ጉባኤ፣ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሆነው ተመርጠዋል። ለኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክርት ቤት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር አፈ-ጉባኤ፤ የአፋር ክልል ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ዛራ ሁመድ አሊ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሆነዋል።   

Äthiopien | Vereidigung Abiy Ahmed
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ኢትዮጵያን እንዲመሩ ተሾመዋልምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ሥራ ላይ የሚቆዩት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች «የሕዝብ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው፣ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው፣ የሚፋጩባቸው» መሆን እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል። 

በሁለቱ የምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ለ30 ደቂቃ ገደማ የረዘመ ንግግር ያደረጉት ሣህለ ወርቅ «እኛ የአንድ አገር ልጆች ተቻችለን እና ተደማምጠን፤ ጥላቻን ተጠይፈን ቁጭ ብለን ተወያይተን የሐሳብ ልዩነትን ተቀብለን፤ ተከራክረን አማራጭ ሐሳቦች እንዲቀርቡ ፈቅደን የማይመጥነንም ቢሆን ለመስማት ዝግጁ ሆነን ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር እና ማዳበር ተቀዳሚ ተግባራችን እንድናደርገው አደራ እላለሁ» ብለዋል። 

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ በንግግራቸው በትግራይ ክልል ይገኝ በነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመውን ጥቃት አንስተዋል። «ባለፈው አመት ለአመታት ዳር ድንበሩን ሲጠብቅ የኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ጥቃት እንደዚሁም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች፣ ሕዝብ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ሲፈጸሙ የተስተዋሉ ጥቃቶች እና የሽብር ተግባራት ከሕግ እና መርኅ፤ ከሞራል እሴቶቻችን እና ባህሎቻችን ያፈነገጡ ነበሩ» ሲሉም ኮንነዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረት የሚያደርግባቸውን የተለያዩ ጉዳዮች በዘረዘሩበት ንግግራቸው በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተንሰራፋውን እና ብርቱ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለውን ውጊያ ለማቆም የታቀደ ነገር ስለመኖሩ ያሉት ነገር ግን የለም። 

«በአመጽ እና በጠብመንጃ ትግል አልያም ንጹሐንን በማሸበር የሚገኝ ሥልጣን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የማይፈጠር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል» ያሉት ሣህለ ወርቅ በዚሁ ንግግራቸው ፖለቲከኞች እና ፓርቲዎቻቸው «በሕጋዊ ምርጫ ብቻ በመሳተፍ ሕዝባችሁንና አገራችሁን የምታገለግሉበትን ሰላማዊ የፉክክር መድረክ ብቻ እንድትመርጡ» የሚል ማሳሰቢያም ሰጥተዋል።  ሣህለ ወርቅ በዚሁ ንግግራቸው ስለ ብሔራዊ መግባባት ደጋግመው በአጽንዖት ተናግረዋል።

«ለአመታት የሀገርን ኅልውና፣ የሕዝባችንን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደዚሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ሰንኮፎች በብሔራዊ መግባባት ሊፈቱ ይገባል» ያሉት ፕሬዝዳንቷ «ሆደ ሰፊነት፣ መተማመን፣ መመካከር፣ ኅብረት እና አንድነት፣ የውይይት እና የክርክር ባህሎችን ማዳበር» እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

«ነጠላ ሁኔታ ሳይሆን ረጅም ጊዜ የሚሻ የለውጥ ሒደት» ላሉት ብሔራዊ መግባባት ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። ሣህለ ወርቅ ከዚህም ሌላ «ፍትኅ እና ተጠያቂነትን ማስፈን፤ የተጎዱን መካስ ማኅበራዊ ፍትኅን ማስፈን ይገባል» ሲሉ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።