1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የየትኞቹ ኩባንያዎች አክሲዮኖች ለሽያጭ ይቀርባሉ?

ሐሙስ፣ ግንቦት 18 2014

"አራት አይነት የገበያ መደቦችን" ይኖሩታል የተባለውን የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለማቋቋም እስከ ሁለት አመት እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባለ ድርሻ በሆነበት ገበያ "ትላልቅ የስቶክ ገበያዎች" ፍላጎት እንዳሳዩም ተገልጿል። ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች የትኞቹ ይሳተፉ ይሆን?

https://p.dw.com/p/4Bs6r
Ethiopian Securities Exchange
ምስል Ethiopian Investment Holdings (EHI)

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ የየትኞቹ ኩባንያዎች አክሲዮኖች ለሽያጭ ይቀርባሉ?

የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለመመሥረት የተጀመረው ጥረት ባለፈው ሳምንት አንድ እርምጃ ወደ ፊት ፈቅ ብሏል። የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆንዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማሞ ምኅረቱ፣ እና የኤፍኤስዲ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ናፒየር የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለመመሥረት የመግባቢያ ሥምምት ግንቦት 10 ቀን 2014 ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የማክሮ ኤኮኖሚ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ ሥምምነቱ "ገበያውን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ቅድመ ሥራ የሚሰራ ፕሮጀክት ቡድን" ያቋቋመ መሆኑን በዕለቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ድርሻዎቻቸውን ለግብይት በማቅረብ "የረዥም ጊዜ ፋይናንስ" እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል የተባለው ተቋም ሲመሰረት ባለ ድርሻ ከሚሆኑት አንዱ የመንግሥት "ስትራቴጂያዊ የኢንቨስትመንት ተቋም" የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆንዲንግስ ነው። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ማሞ ምኅረቱ "የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሚያደርጋቸው ኢንቨስትመንቶች መካከል በኢትዮጵያ ሴኩቲሪ ኤክስቼንጅ ኢንቨስት ማድረግ ነው" ሲሉ ኩባንያው ባለድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካው ናስዳክን ጨምሮ "ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ትላልቅ የስቶክ ገበያዎች" በአዲስ አበባ በሚመሠረተው ተቋም ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳሳዩ አቶ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል። የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን ማቋቋም እና የቁጥጥር ሥርዓቱን የማበጀት ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ነው። በግብይቱ ለሚሳተፉ የመዋዕለ-ንዋይ ባንኮች እንዲሁም ገዢን ከሻጭ ለሚያገናኙ ተቋማት ፈቃድ የሚሰጠው እና የሚቆጣጠረው የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን ይሆናል።

Ethiopian Securities Exchange
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆንዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማሞ ምኅረቱ፣ እና እና የኤፍኤስዲ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ናፒየር የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን ለመመሥረት የመግባቢያ ሥምምት ግንቦት 10 ቀን 2014 ተፈራርመዋል።ምስል Ethiopian Investment Holdings (EHI)

መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ኤፍኤስዲ አፍሪካ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም በምታደርገው ጥረት የግብይቱን አዋጪነት ለመፈተሽ እና የገበያውን አቅም ለመገንባት የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የኩባንያው የኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር ኔልሰን ካራንጋ ለዶይቼ ቬለ በኢ-ሜይል ገልጸዋል። ኃላፊው እንዳሉት ኩባንያው የአገልግሎት አቅራቢዎችን የፈቃድ አሰጣጥ እና ለጋራ የኢንቨስትመንት ዕቅዶች የቁጥጥር ሥርዓት ማዕቀፎች በማበጀት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የእነማን አክሲዮን ለሽያጭ ይቀርባል?

የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን አቋቁሞ ሥራ ለማስጀመር እስከ ሁለት አመታት ሊፈጅ እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። ተቋሙ ሥራ ሲጀምር ቢያንስ 50 ኩባንያዎች ድርሻዎቻቸውን ለሽያጭ ሊያቀርቡ እንደሚችል ይጠበቃል። ከ22 አመታት ገደማ በፊት ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ተቋም ለመመስረት ጥረት ያደረጉት የፌይር ፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀ-መንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ በዋናነት የኢትዮጵያ ባንኮች እና የመድን ኩባንያዎች በግብይቱ የሚሳተፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይስማማሉ። "ኢትዮጵያ ውስጥ በአክሲዮን ገበያ ድርሻዎቻቸው እና ቦንድን የመሳሰሉ ሌሎች የፋይናንስ ሰነዶቻቸው ሊሸጥ የሚችሉ ኩባንያዎች 50 አካባቢ ነው የተባለው። ከእነሱ ውስጥ ወደ 40ዎቹ ባንክ እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ነው የምገምተው" ሲሉ አቶ አብዱልመናን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ግን ይኸ በግብይቱ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ቁጥር እስከ 70 ከፍ ሊል የሚችልበት ዕድል እንዳለ ይሞግታሉ። "እያደጉ የመጡ፣ ሁለተኛ ትውልድ ላይ የደረሱ፣ ጥሩ ሽያጭ ያላቸው፣ የአስተዳደር መዋቅራቸው እየተጠናከረ የመጣ ይኸ ገበያ በሚመጣበት ጊዜ በቀላሉ አክሲዮኖቻቸውን የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ላይ ማቅረብ የሚችሉ ከ10 እስከ 20 የቤተሰብ ኩባንያዎች አሉ የሚል እምነት አለኝ" ሲሉ አቶ ዘመዴነህ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም፣ መብራት ኃይል፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከመሳሰሉ በመንግሥት እጅ የሚገኙ ተቋማት መካከል አስር ገደማዎቹ በዚሁ ግብይት ለመሳተፍ ሊመዘገቡ እንደሚችሉ እምነታቸው ነው። በኢትዮጵያ ገበያ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ጥቂቶቹ ይኸንንው መንገድ ሊከተሉ እንደሚችሉ የፌይር ፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀ-መንበር ተናግረዋል። ቶታል፣ ዩኒሊቨር፣ ሔኒከን፣ ኮካ ኮላን የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ተቋማት በናይሮቢ፣ ሌጎስ እና ጁሐንስበርግ በእነዚያ አገሮች የሚሰሩ ኩባንያዎቻቸውን በአክሲዮን ገበያ እንደሚያስመዘግቡ የተናገሩት አቶ ዘመዴነህ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ መንገድ ሊከተሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል። እነዚህን ሁሉ ደምረው 50 አነስተኛ ግምት ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩት አቶ ዘመዴነህ "እስከ 70 የሚሆኑ በአክሲዮን ገበያ የሚዘጋጁ ወይ የተዘጋጁ ኩባንያዎች አሉ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

አሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚከናወነው የባንኮች እና የኢንሹራንሶች አክሲዮን ግብይት "በትክክለኛው ቦታ እንዲሸጥ፣ ትክክለኛ ዋጋውን ዋጋውን እንዲያገኝ" አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አቶ አብዱልመናን ተናግረዋል። ኩባንያዎች በፈቃደኝነት ወደ ግብይቱ እንደሚገቡ የገለጹት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "ሌላ ኩባንያ አክሲዮኑ በስቶክ ገበያ እንዲሸጥ የሚፈልግ ከሆነ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የነበረ ወይም በቤተሰብ የተያዘ ወደዚህ ግብይት መምጣት ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል። "በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ኩባንያዎች በቤተሰብ የተያዙ ናቸው" የሚሉት አቶ አብዱልመናን እንዲህ አይነት ተቋማት ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ወይም ለመሸጥ ወደ አክሲዮን ገበያ ሲያመሩ "ስለ ድርጅቱ ዝርዝር የሆነ መረጃ መስጠት አለባቸው። በዚያ መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው የአክሲዮን ዋጋ የሚወጣው። ያንን ዝርዝር መረጃ ማቅረብ ስለማይፈልጉ ብዙዎቹ ላይመጡ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

የትንንሾቹ ኩባንያዎች ቦታ የት ነው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የማክሮ ኤኮኖሚ አማካሪ አቶ መለሰ ምናለ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ "የኢኮኖሚያችን ዋና መሠረት" ያሏቸው "ትንንሽ ተቋማት ወይም ኩባንያዎች" ቸል እንደማይል ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ "በየደረጃው ላሉ እንደየአቅማቸው የሚገበያዩበት አራት አይነት የገበያ መደቦችን" እንደሚኖሩት አቶ መለሰ ገልጸዋል።

የካፒታል ገበያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ኩባንያዎች ተመዝግበው በግብይቱ እንዲሳተፉ ለመፍቀድ በርካታ መስፈርቶችን ያስቀምጣሉ። መስፈርቶቹ የኩባንያዎቹን አጠቃላይ የገበያ ዋጋ፣ የአክሲዮን ተመን፣ ለሽያጭ የሚያቀርቧቸውን አክሲዮኖች እና የባለድርሻዎች ብዛት የተመለከቱ ጭምር ናቸው። አቶ መለሰ የጠቀሷቸው የኢትዮጵያ "ትንንሽ ተቋማት" በእርግጥ ግብይቱን በበላይነት የሚመራው የካፒታል ገበያ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን የሚያስቀምጠውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት የመቻላቸው ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል።

Ethiopian Securities Exchange
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅን አቋቁሞ ሥራ ለማስጀመር እስከ ሁለት አመታት ሊፈጅ እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። ተቋሙ ሥራ ሲጀምር ቢያንስ 50 ኩባንያዎች ድርሻዎቻቸውን ለሽያጭ ሊያቀርቡ እንደሚችል ይጠበቃል።ምስል Ethiopian Investment Holdings (EHI)

አቶ አብዱልመናን መሐመድ "የአክሲዮን ገበያ ለትንንሽ ኩባንያዎች የሚሆን አይደለም። እንኳን በኢትዮጵያ በሌላው ዓለምም የእነሱ አክሲዮን አይሸጥም" ሲሉ ይሞግታሉ። "ትንንሽ" የሚባሉት ኩባንያዎች በግብይቱ ለመሳተፍ የሚቀመጡ መስፈርቶችን ለማሟላት እንደሚቸገሩ የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የባለወረቶችን ቀልብ በመግዛት ረገድም እንደማይሳካላቸው ገልጸዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀቱን ማጠናከር፣ የሕግ መዋቅሩን ማስተካከል፣ ኢንተርኔት እና የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊ መሠረተ-ልማቶችን ማሟላት እና የመረጃ አቅርቦት በየትኛውም ገበያ እንደ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ አይነት ግብይቶች ሲቋቋሙ ዋንኛ ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች እንደሆኑ የጥብቅና ባለሙያው አቶ መታሰቢያ ኃይሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ገበያውን የተመለከተ የመረጃ አቅርቦት ጉዳይ "ገበያው ከተቋቋመ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከመቋቋሙም በፊት ሊሰራ የሚገባ ነው። የወጣው አዋጅ ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮችን የያዘ ነው። ዝርዝር የመሆኑን ያህል እነዚያ ነገሮች ወደ ግሉ ዘርፍ ገብተው ምን አይነት ዝግጁነት ነው የሚያስፈልገው የሚለውን በሚመለከት ብዙ የተሰራ ነገር የለም" በማለት አቶ መታሰቢያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቋቁሟል። አንዱ ተግባር እና ዓላማው የገበያ መረጃ መግለጽ ነው። በሚቀጥሉት ቅርብ አመታት ይቋቋማል ተብሎ የሚገመት ከሆነ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው የቅድመ መስረታ መረጃ የሚባል ነገር አለ። የቅድመ መስረታ ሒደቱ በዚያ ውስጥ እንዲሳተፉ ለሚፈለጉ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃው ጎን ለጎን አብሮ መተላለፍ መቻል አለበት" ሲሉ አቶ መታሰቢያ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ለሽያጭ የሚቀርቡ ሰነዶች ዋጋ በመረጃ እንደሚወሰን የጠቆሙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ይኸ ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ይስማማሉ። "ቴክኖሎጂው፣ ሶፍትዌሩ ሊገዛ፣ ሕንጻው ሊገነባ ይችላል። ግብይቱን የሚያካሒዱ የተወሰኑ ባለሙያዎች ልናመጣ እንችላለን። እዚያ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች ግን በቂ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል። እውቀቱ የሌላቸው እንደሆነ ብዙ ሰዎች ሊከስሩ ይችላሉ" ሲሉ አቶ አብዱልመናን አስጠንቅቀዋል።

"የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ብቻውን የሚቋቋም አይደለም። ስኬታማ ለመሆን ዙሪያውን ብዙ መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ። እነዚህን ኩባንያዎች ወደ ገበያው የሚያመጣ የመዋዕለ-ንዋይ ባንክ ያስፈልጋል፤ ገዢ እና ሻጭን የሚያገናኝ የአክሲዮን ደላላ ያስፈልጋል" የሚሉት አቶ ዘመዴነህ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለ ግብይቱ ግንዛቤ መፍጠር እና ማስተማር አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሆኑ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ዘመዴነህ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ወደፊት በሚያቀርበው አገልግሎት እንደ ትርፍ ሁሉ" ኪሳራም እንዳለ ማስተማር ያስፈልጋል" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ