1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተጠፋፉ ቤተዘመዶችን የማገናኘት ስራ በአፍሪቃና በጋምቢያ በህንድ ሰራሽ መድሃኒት የሞቱ ህፃናት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5 2015

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ35 በላይ በታጠቁ ሀይሎች መካከል ግጭቶች አሉ። እነዚህን ግጭቶች ለመሸሽ በሚደረገው ጉዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመድ አዝማድ ከቤተስቦቻቸው ጋር ተጠፋፍተዋል።በሌላ በኩል በህንድ ሰራሽ የሳል መድሃኒት የ66 ህጻናት ህይወት አልፏል።ለእነዚሀ ሕጻናት ጋምቢያውያን ፍትህ እየጠየቁ ነው።

https://p.dw.com/p/4IERd
Gambia Andacht für mit indischem Hustensaft vergiftete Kinder
ምስል Omar Wally/DW

ትኩረት በአፍሪቃ 15.10.2022

 
 የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅትዝግጅታችን በአፍሪካ  በተለያዩ ምክንያቶች የተጠፋፉ  ቤተሰቦችን የማገናኜት ስራ እንዲሁም በጋምቢያ በአንድ የህንድ ሰራሽ መዳሃኒት ሳቢያ የሞቱ 66 ህፃናትን የተመለከቱ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮችን አካቷል።
በአፍሪካ  በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በጎርጎሪያኑ 2001 ብቻ 64,000 ያህል ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መጠፋፋታቸውን የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ መረጃ ያሳያል። ከነዚህም ውስጥ ግማሾቹ ህጻናት ናቸው።
የደቡብ ሱዳኑ አብዶ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ነው። አብዶ ለዓመታት ያህል ያለ ቤተሰብ  ሕፃን ሆኖ ራሱን ለመምራት ተገዷል።አብዱ ገና በ13 አመቱ ነበር  ከሀገሪቱ በስተ ምዕራብ ወደ ሚገኝ ቶምቡራ ወደ ተባለ ቦታ የተሰደደው።
በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እርዳታ በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም ነበር  የ22 አመት ወጣት ሆኖ ከእናቱ ጋር የተገናኘው ።
በጎርጎሪያኑ 2013 የጀመረው የደቡብ ሱዳን ጦርነት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት፣ የአስገድዶ መድፈር  ጾታዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ህጻናትን ለውትድርና መመልመልን የመሳሰሉ ጉዳቶች አድርሷል። አብዶን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ደግሞ ለያይቷል። አብዶ በ2017 ዓ/ም በ22 ዓመቱ ነበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻታት መርጃ ድርጅት አማካኝነት ከቤተሰቡ ጋር የተቀላቀለው።
እናቱ ወይዘሮ ኤሌና ለድርጅቱ በልጃቸው መጥፋት የደረሰባቸውን የስሜት ስብራት ሲገልፁ «ሞቶ ስላልቀበርኩት እሱን መርሳት ከባድ ነበር።በህይወት ለመቆየት ብቻ ነበር ምግብ የምበላው ። ነገር ግን ፈጽሞ ደስተኛ አልነበርኩም።» ሲሉ ገልፀዋል። 
በዚህ ሁኔታ በጎርጎሪያኑ 2013 እስከ 2018 ፣ ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ፣ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት እና አጋሮቻቸው በደቡብ ሱዳን ከ6,000 በላይ ህጻናትን በተሳካ ሁኔታ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አገናኝተዋል።ነገር ግን በ 2018 ዓ/ም 15,000 ህጻናት አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል ። በ 2022 ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ  የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በመላው አፍሪካ ከ25,000 በላይ ታዳጊዎች ጠፍተዋል።
በድርጅቱ በመላው አፍሪካ ከተመዘገቡት 64,000 የጠፉ ሰዎች  ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው።የዓለም አቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ  ባልደረባ ሴሊን ዱትሬሉኝ ለDW እንደገለጹት ቁጥሩ ከዚህም ሊሻቅብ ይችላል።
«ወደ እኛ የሚቀርቡ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ይህ  የበረዶ ግግር ጫፍ ያህል ብቻ ነው። ምክንያቱም የተወሰኑ ብቻ ናቸው ወደ እኛ እየቀረቡ ያሉት። እውነታው በ2022  እጅግ የላቀ መሆኑን እናውቃለን ።ማለቴ በ2001 ዓ/ም መጨረሻ ብቻ  በአፍሪካ 64,000 የጠፉ ሰዎች ጉዳይ ነበር።ከዚያ በኋላም  እንደገና ብዙ ቁጥር ያላቸው ልጆች ነበሩ። ሰዎች ሊለያዩ የሚችሉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ።ከግጭት፣ ከስደት እና ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ሊገናኝ ይችላል።».
በተለይ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግንኙነት ካቋረጡ በኋላ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው የሚሉት ሰሊን ፤ በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ግጭት በትግራይ ክልል በግንቦት 2021ዓ/ም  ከ5,000 በላይ ህጻናትን ከወላጆቻቸው ለያይቷል ሲል የህፃናት አድን ድርጅት  መረጃ ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ35 በላይ በታጠቁ ሀይሎች መካከል  ግጭቶች አሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ደህንነት ፍለጋ በየአመቱ ድንበር አቋርጠው በሳሃራ በረሃ እና በሜዲትራኒያን ባህር ይጓዛሉ። እነዚህ ጉዞዎችም መጠፋፋትን  ጨምሮ በርካታ አደጋዎችን ያስከትላሉ።
ከደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ 80% ያህሉ የጠፉ ሰዎች ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ ከ11 የአፍሪቃ ሀገራት  የመጡ ናቸው። ማለትም ከካሜሩን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጊኒ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ እና ከሱዳን የመጡ ናቸው።
በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዚህ አመት በሀምሌ ወር ብቻ 800 ህጻናት በታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ጦርነት ሸሽተው ወላጆቻቸውን አጥተዋል።
በጎማ የህጻናት አድን ድርጅት የፕሮግራም  ዳይሬክተር የሆኑት አርጂካ ባርክ በቀውስ ወቅት  ህጻናት ለተለያዩ ችግሮች በጣም የተጋለጡ ናቸው ።ይላሉ።
«ልጆች ከቦታቦታ ከሚዘዋወሩት  በጣም ተጋላጭ ከሆኑት ወይም ከስደተኞች መካከል በተለዬ ሁኔታ ይጎዳሉ።ልጆች ከጠቅላላው ከሚፈናቀሉት ግማሽ ያህሉን የሚወክሉ ሲሆኑ ፤ ለጥቃት፣ ለሕገወጥ ዝውውር፣ ለወሲብ ጥቃት እና ጾታን መሠረት ላደረጉ  ጥቃቶች፣ ለአፈና፣ የታጠቁ ቡድኖች ውስጥ በግዳጅ የመሳተፍ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ  ሕገ-ወጥ ለእስር እና ብዝበዛ በጣም የተጋለጡ ናቸው። ስለዚህ ዝርዝሩ ረጅም ነው።»
በናይጀሪያም ወደ 14,000 የሚጠጉ ህጻናትን ጨምሮ ከ25,000 በላይ ሰዎች ጠፍተዋል።  ይህም በአፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ነው።
ናይጄሪያ የጠፉ ሰዎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና በማገናኘት ረገድ ባለፈው አመት የተወሰነ ስኬት መገኘቱን ተገልጿል። 
በአፍሪቃ ብዙ ድርጅቶች የተበታተኑ  ቤተሰቦችን የማፈላለግ አገልግሎት ይሰጣሉ። ዓለምአቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ  በ26 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እየሰራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ኮንጎ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኤርትራ እና ሩዋንዳ ውስጥ ይሰራል።
የህፃናት አድን ድርጅት ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት መርሀ ግብሮች  አሉት። የድርጅቶቹ ባልደረቦች እንደሚሉት ውጤቱ ሁል ጊዜ እንደገና ማገናኘት ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜም በዘመዶቻቸው ላይ የተከሰተውን ነገር ግልጽ ማድረግ ይሆናል።
ዓለም አቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ በ2020 አመታዊ ዘገባው  በአፍሪካ ብቻ 740,064 የስልክ ጥሪዎችን በቤተሰብ መካከል መደረጉን እና 874 ሰዎችን 788 ህጻናትን ጨምሮ - ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረጉን ገልጿል።
የአለምአቀፍ የጠፉ ሰዎች አገናኝ ኮሚሽን (ICMP) /The International Commission on Missing Persons/ ወይም እንደ ሳልቬሽን አርሚ/ Salvation Army /ያሉ የቤተክርስቲያን ቡድኖች እንዲሁ የጠፉ ሰዎችን ለማግኘት የመገናኛ መንገዶች ናቸው። እንደ ትሬስ ፌስ Trace the Face  ያሉ የበይነመረብ  አገልግሎቶች ደግሞ ወደ አውሮፓ ሲሻገሩ በባህር መንገድ ላይ በጠፉት ላይ ያተኩራሉ።
ነገር ግን ፍለጋው ቀላል አይደለም የት መጀመር አለበት? የሚለው ጥያቄ ቀድሞ የሚነሳ ነው።የአቀፉ የቀይመስቀል ኮሚቴ  ባልደረባ ሴሊን ዱትሬሉኝ የፍለጋውን አስቸጋሪነት ሲገልፁ «በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ወይም በአህጉሪቱ ውስጥ መፈለግ አለብህ።.ሰዎች ሊታሰሩ ይችላሉ።በዚያ የተነሳ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት አይችሉም።»ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር የማስፈጸሚያ  የቁሳቁሶች እጥረት፣ የበይነመረብ ግንኙነት ችግር , እንዲሁም ሰዎቹን በአካል ለመፈለግ የመሰረተ ልማት ወይም በግጭት ምክንያት ወደ አካባቢው ለመድረስ  አስቸጋሪ  መሆኑን ተናግረዋል።ችግሩን ለማቃለል ዶትሬሉኝ ከባለስልጣናት ድጋፍ  ማግኘትንም ተስፋ ያደርጋሉ።የተጠፋፉ ቤተሰቦችም የት  እንደሚፈልጉ ማወቅ ያስፈልጋል ይላሉ።   
 «አንዱ አስፈላጊ ነገር በመጀመሪያ ቤተሰቦች ዘመድ ለማግኘት ማንን መጠየቅ እና የት መፈለግ እንዳለባቸው ማወቅ ነው።እኔ እንደማስበው አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት   የመመዝገቢያ ስርዓት የላቸውም።የጠፉ ቤተሰቦች በትክክል እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው አያውቁም። ስለዚህ ፈላጊ ቤተሰቦች የመጀመሪያው ነገር  የጠፉትን ዘመዶቻቸውን ለባለስልጣናት ማሳወቅ የሚችሉበት አገናኝ መንገድ ሊኖራቸው ያስፈልጋል። የተጠፋፉ ሰዎች  ቤተሰባቸውን የሚገኙበትን መንገድ ለመፍጠር  ማለት ነው። እኛ ፣ እንዲሁም ቀይ መስቀል ለማድረግ የምንሞክረው የመጀመሪያው ነገር ይህ ነው። ምክንያቱም ሳይገናኙ በቆዩ ቁጥር  ተለያይቶ የመቅረት እድሉ ይጨምራል።» 
የህፃናት አድን ድርጅት ባልደረባው  ባርክ በበኩላቸው ችግሩ ዓለም አቀፍ ጥረትን ይጠይቃል ይላሉ። 
«ስለዚህ የፍላጎት ደረጃን ከግምት ውስጥ በማስገባት ድርጊቱ ዓለም አቀፋዊ መሆን እና በተዋናዮች መካከል በደንብ የተቀናጀ መሆን አለበት።.በሂደቱ መጨረሻ  እንዳለመታደል ሆኖ አብዛኛዎቹ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። በተደራሽነት ችግር በርካታ ወራት እና አንዳንዴም አመታት ሊወስድ ይችላል። ቤተሰቦች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይቀጥሉ እና እነሱን ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል።»
ይህ ከሆነ  እያንዳንዱ ትንሽ መልእክት እና መረጃ በአፍሪካ የተጠፋፉ  ቤተሰቦችን በፍጥነት እንዲገናኙ ይረዳል ሲሉም አክለዋል።
 በጋምቢያ ከህንድ ሰራሽ የሳል ሽሮፕ ጋር በተያያዘ በከባድ የኩላሊት ጉዳት 66 ህጻናት መሞታቸውን የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት ከሰሞኑ አስታውቀዋል። 
 ይህንን ተከትሎ  የሞቱት ህጻናት ፍትህ እንዲያገኙ እና ባለስልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ  ጋምቢያውያን እየጠየቁ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅትም በህንድ ውስጥ ለተመረቱ በርካታ የሳል እና የጉንፋን መድሃኒቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የሕንድ የመድኃኒት ቁጥጥር ድርጅት እና የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት በጋምቢያ  66 ህፃናትን ለሞት አብቅቷል የተባለውን መድሃኒት  ባመረተው « ሚዲየን» በተባለ የመድሀኒት አምራች ኩባንያ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። 
በሳምንቱ መጨረሻም ይህንኑ የሳል እና የጉንፋን መድሃኒት ከወሰዱ በኋላ ወደ ሆስፒታል የገቡ ተጨማሪ ሶስት ህጻናት በከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት ህይወታቸው አልፏል። የጋምቢያ ባለስልጣናት እንዳሉት 81 ተጨማሪ ህጻናትም በሆስፒታል ይገኛሉ።
በዚህ መድሃኒት ሳቢያ ሙሳ የተባለውን የሁለት አመት ልጁን  ያጣው አላሳን ካማሶበጉዳዩ የሀገሪቱን መንግስትን ይተቻል። 
«በጋምቢያ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር መከሰት ያለበት አይመስለኝም።. የመጀመሪያው ልጅ ከሞተ በኋላ መንግስት አንድ እርምጃ መውሰድ እና መንስኤዎቹን ማወቅ ነበረበት። ያ ባለመሆኑ ነገሩ ከፋ እና ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። መንግሥት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶችን ይቆጣጠር።ሰዎች መሞት የለባቸውም።  የስራ ፈቃድ የሰጠውን መድሃኒት ቤትም ይመርምር። የሰው ህይወት ውድ ነው። ማንም የሰውን ህይወት ሊገዛ አይችልም።»በማለት በቁጭት ገልጿል።
ብዙ ጋምቢያውያን ከዋና ከተማዋ ባንጁል ወጣ ብላ በምትገኘው ሴሬኩንዳ በሚገኝ አደባባይ በሳምንቱ መጨረሻ ህፃናቱን ለማሰብ  እና አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉት ለመፀለይ እንዲሁም ጥፋተኞቹ ለህግ እንዲቀርቡ ለመጠየቅ  ተሰብስበው ነበር።
የመብት ተሟጋቹ ማዲ ጆባርቴህ እንዳሉት ህጻናት የሞቱት በቸልተኝነት ነው።
«በቸልተኝነት እና በመንግስት ጥፋት ለሞቱት 66 ህጻናት የተግባር ጥሪ ለማድረግ የሻማ ማብራት እና የፀሎት ሥነ-ስርዓት እያደረግን ነው። የጤና ስርዓቱ በትክክል መስራቱን ለማረጋገጥ እና እነዚህን ልጆች የገደላቸው አይነት መጥፎ መድሀኒት እንዳይፈቀድ  እንዲሁም  ጥፋቱ የት እንደሆነ ሀላፊነት የሚወስደው ማን እና ምን እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።»
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አራቱ የሳል እና የጉንፋን መድሃኒቶቹ ለልጆቹ ሞት መንስኤ የሆኑት«ዲኤታይሊን ግላይኮል» መመረዝ ሳቢያ ከፍተኛ የኩላሊት ጉዳት በማድረሳቸው ነው።
በዚህ ምክንያት የጋምቢያ ባለስልጣናት ከ16,000 በላይ በህንዱ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የተመረቱ  መድሃኒቶችን መሰብሰብ ችለዋል። 
 የሕንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ለDW እንደተናገሩት አራቱ ሽሮፖች ቻንዲጋር በሚገኘው የክልል የመድኃኒት መመርመሪያ ቤተሙከራ ለምርመራ ተልከው ውጤቱ እየተጠበቀ ነው። 
በሌላ በኩል አንዳንድ ጋምቢያውያን ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው የልጆቹን ሞት አቅልለውታል ሲሉ ተችተዋል። ትችቱ ፤ባሮው በሀገራቸው በብሔራዊ ቴሌቪዥን የልጆቹ ሞት ካለፈው ዓመት በሀገሪቱ ከነበረው የጨቅላ ህጻናት ሞት ያን ያህል የተለየ አይደለም ብለዋል።» በሚል  ነው,። ይሁን እንጂ ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ስለበሽታው ሁኔታ ለማብራራት እንጅ ለሕይወት መጥፋት ግድ የለሽ መሆናቸው አይደለም። በሚል መሥሪያ ቤታቸው በፍጥነት ነገሩን ለማስተካከል ሞክሯል።ፕሬዚዳንቱም በይፋ መግለጫ ሰጥተዋል።
ያም ሆኖ አንዳንድ ጋምቢያውያን ፕሬዚዳንቱን አሁንም እየወቀሱ ነው። ቻይልድ  አሊያንስ የተባለው  በህፃናት  ደህንነት ጥበቃ  ላይ የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የፕሬዚዳንት ባሮውን አስተያየት “አሳዛኝ” እና “ኃላፊነት የጎደለው” ሲል ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ነዋሪዎች በወቅቱ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው የመንግስት ባለስልጣናት እና መድሃኒቱን በሚያስገቡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልባቸው ጠይቀዋል።የተቃዋሚ ፖለቲከኛዋ  ነኔህ ፍሬድ ጎሜዝ ጥፋተኞች ለፍርድ እንስኪቀርቡ  አይናቸውን ከጉዳዩ እንደማያነሱ ተናግረዋል።
«ጋምቢያውያን የተሰበሰቡት ለነዚህ ለሚያሳዝኑ ልጆች ለችግር ለተጋለጡ ወላጆች እና  ድምጽ አልቫ ለሆኑ ቤተሰቦች ለማዘን ነው።በእርግጥ ነው በሆነ ሰው የብቃት ማነስ ምክንያት፤ በሆነ ሰው እንክብካቤ ጉድለት ነው እነዚህ የሚያሳዝኑ ልጆች  የተገሉት።እኔ «ተገደሉ» የሚለውን  ቃል ነው የምጠቀመው። እና በእርግጥም፣ የሆነ አካል እየተመለከታቸው  መሆኑን ለባለስልጣናቱ ለመንገር እና ስጋታችንን ለማንሳት ጭምር ነው። በድርጊታቸው ሁላችንም አይናችንን አንከድንም።»
ልጃቸውን በሞት ያጡት ካማሶም  ይህ ቀውስ  እና ሀገራዊ አደጋ ዳግም እንዳይከሰት ፍትህ እና ከፍተኛ እርምጃ ይፈልጋል።
 የመድሃኒት አምራች ኩባንያው ስለ መድሃኒቶቹ ችግር ሲያጋጥመው የመጀመሪያው አይደለም። ኩባንያው በህንድ ውስጥ በሚገኙ ሰባት ግዛቶች ደካማ ጥራት ያላቸውን መድሃኒቶች በማምረት ከዚህ ቀደም ተከሷል። በ 2020 ዓ/ም  ጃሙ እና ካሽሚር በተባሉ ሁለት የህንድ ግዛቶች-ከፍተኛ መጠን ያለው «ዲኤታይሊን ግላይኮል» ያለው ሽሮፕ ከወሰዱ በኋላ 17 ህጻናት ህይወታቸው አልፏል። 
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ

Gambia Andacht für mit indischem Hustensaft vergiftete Kinder
ምስል Omar Wally/DW
Gambia Banjul Todesfälle durch Einnahme von verunreinigten Hustensäften aus Indien
ምስል MILAN BERCKMANS/AFP
Gambia Andacht für mit indischem Hustensaft vergiftete Kinder
ምስል Omar Wally/DW
Gambia Hustensaft | Logo Maiden Pharmaceuticals
ምስል ANUSHREE FADNAVIS/REUTERS
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Bildergalerie | DR Congo | Ausbruch des Nyiragongo und Evakuierung von Goma
ምስል Hugh Kinsella Cunningham/Save the Children/Reuters
EMBARGOED APRIL 12 Data visualization - Migation within Africa - UNHCR displaced people