1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፋር ድርቅና ጦርነት ያስከተለው የምግብ እጥረትና መዘዙ

ዓርብ፣ ሰኔ 3 2014

በአፋር ክልል በተደጋጋሚ በተስተዋለው ጦርነትና ድርቅ ሳቢያ በምግብ እጥረት ወደ ሆስፒታል ከገቡ ህጻናት ከ30 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ሆስፒታሉ አስታወቀ፡፡ ባለፉት ጢቂት ወራት በምግብ እጥረትና በሌሎች ህመሞች ወደ ዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታል የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ከሆስፒታሉ አቅም በላይ ሆንዋል ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/4CXhj
Äthiopien Konflikt im Norden
ምስል Seyoum Getu/DW

በምግብ እጥረት ቢያንስ 35 ህጻናት ሞተዋል

በአፋር ክልል በተደጋጋሚ በተስተዋለው ጦርነትና ድርቅ ሳቢያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ለምግብ እጥረት ተዳርገው ወደ ዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታል ከገቡ ህጻናት ከ30 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ሆስፒታሉ አስታወቀ፡፡ 
የሆስፒታሉ ሥራ አስከያጅ ዶ/ር ሁሴን አደም ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ባለፉት ጢቂት ወራት በምግብ እጥረትና በሌሎች ህመሞች ወደ ዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታል የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ከሆስፒታሉ አቅም በላ ናቸው፡፡ 

የሕክምና ግብረ ሰናይ ድርጅት የሆነው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF) መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ጢቂት ሳምንታት ቢያንስ 35 ህጻናት በኢትዮጵያው አፋር ክልል መሞታቸውን አመልክቷል፡፡ መረጃውን የአከባቢው ሆስፒታሎችን ዋቢ አድርጎ ያወጣው ድንበርየለሽ የሃኪሞች ቡድኑ ባለፉት 8 ሳምንታት ህይወታቸው ከለፈው ከ35ቱም ህጻናት ሁለት ሶስተኛው ህክምናውን ሊያገኙ ሆስፒታሉ በገቡ 48 ሰዓታት የሞቱ ናቸው፡፡ 
በአፋር ክልል ብቸኛው የሪፌራል ሆስፒታል በሆነው የዱብቲ ጀኔራል ሆስፒታል ባለፉት ጥቂት ወራት በታካሚዎች ብዛት ክፉኛ መጨናነቁን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሁሴን አደም፤ በክልሉ በምግብ እጥረት ተጎድተው የሚመጡ ሕፃናት ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመሩን እና ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ30 በላይ ህጻናት በምግብ እጦት ተጎድተው በመምጣታቸው ታክመው አለመዳናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ 

በአፋር ክልል እየጨመረ የመጣው የምግብ ቀውስ ስጋት እንዳጫረበት የገለጸው ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን (MSF); እንዳስታወቀው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መሠረታዊ የሚባሉ የጤና ማዕከላትን እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማያገኙበት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት። በርካታ ሕፃናት በከፋ የምግብ እጥረት ሕይወታቸውን አጥተዋልም ያለው MSF የዘንድሮው ችግር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር እንኳ በአራት እጥፍ የሚከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕፃናት ተስተውሏል። 
በአፋር ክልል ካሉ የጤና ማዕከላት አብዛኞቹ አገልግሎት ላይ እንዳልሆኑ ያመለከተው ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን መረጃ፤ በክልሉ በሥራ ላይ ያሉት 20 በመቶ ብቻ ናቸው ብሏል። በመሆኑም በክልሉ እየተከሰተ ያለው ቀውስ ከዚህም የከፋ ሊሆን ስለሚችል የረድኤት ተቋማት እንዲረባረቡ አሳስቧል። 
እስከ ቅርብ ጊዜ ከክልሉ ዞን 2 የሚሰደዱ ተፈናቃዮች በሰመራ አቅራቢያ ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ያለማቋረጥ እየገቡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑም ወቅት ስፍራው መሸከም ከሚችለው በላይ ከ30 ሺህ የላቁ ተፈናቃዮች መድረሳቸው ይነገራል። በተመሳሳይም በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ተፈናቃዮች የጤና፣ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ሁኔታ በቂ ባለመሆኑ ለተለያዩ ህመሞች እንደሚዳረጉም ተብራርቷል። የዱብቲ ጄኔራል ሆስፒታል ሥራ አስከያጅ ዶ/ር ሁሴን አደም የችግሩን አስከፊነት ወደ ሆስፒታላቸው ከሚመጡ ሰዎች ቁጥር አንጻር ነው የሚያሰሉት፡፡  
ስለአሁናዊ የክልሉ የእርዳታ አቅርቦት እና የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ለዛሬ ምላሽ አላገኘም፡፡ የክልሉ መንግስት ተደጋጋሚ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት ግን 1.3 ሚሊየን ህዝብ በተደጋጋሚ ጦርነት እና ድርቅ ምክኒያት የእለት እርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በሚሰጡትም መረጃ መሰረት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ዘንድሮ የከፋ የምግብ እጥረት ተከስቷል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተስፋፋው ጦርነት ከተጎዱት አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን ሳይጨምር በደቡብ ኦሮሚያ እና በሶማሊ ክልሎች ድርቅ ያስከተለው አደጋ 7.4 ሚሊየን ዜጎችን ለድጋፍ መዳረጉ ነው የሚነገረው፡፡ ይህ አሃዝ በአማራ ክልል ድጋፍ ከሚሹ 8.7 እና እና በትግራይ ከሚገኙ 5.2 ሚሊየን እርዳታ ፈላጊዎች ጋር የችግሩን መጠን አጉልቶ ያሳያል፡፡
ስዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ