1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ አዲስ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2014

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክትን አስተዋወቀ፡፡ ዓመታትን በፈጀው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የተመዝጋቢዎች እና ቤት ፍላጎትን መመለስ ያልቻለው ከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ ሌሎች አማራጮችንም እየተመለከተ ስለመሆኑ እያሳወቀ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4BNLn
Äthiopien Addis Abeba | Neues Hausprojekt
ምስል Seyoum Getu/DW

ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በመዲናዋ የተጀመረው አዲስ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የመሳያ ምዕራፍ በሶስት ወራት እንደሚጠናቀቅና ውጤታማነቱ እየታየ እንደሚቀጥልም ተነግሯል፡፡ የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት እንዳሳወቀው በሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት በመንግሥት፣ በግለሰቦችና በባለሃብቶች 7.2 ሚሊዮን ቤቶች በከተማና በገጠር እንደሚሠሩ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉና እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት የሚያቃልሉ ያሏቸውን የቤት፣ የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ፣ የከተማ ግብርና እና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች ይፋ ሲያደርጉ ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን አሁናዊ ገጽታ እና ችግሮች ከማቃለል አንጻር ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡ ዛሬ እንደ አዲስ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች አንደኛው በአጭር ጊዜ ተሰርቶ ይጠናቀቃል የተባሉ የመኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ ነው፡፡

Äthiopien Addis Abeba | Neues Hausprojekt
ምስል Seyoum Getu/DW

በ3 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ለዝቅተኛ ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ የሚሆን፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ከከተማው እድገት ጋር የህዝቡን ኑሮ አብሮ የሚቀይር የተባለው የተገጣጠመ 4 የጋራ መኖርያ ህንፃዎች፤ 200 ቤቶች የሚይዝ የG+9 ቤቶች ግንባታው በተጀመረበት በዛሬው ዕለት፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ሊያገኙ እንደማይችሉም ከንቲባዋ በንግግራቸው ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

አዲሱን የጋራ መኖሪያ ህንጻ በሙከሪያ ፕሮጀክቱ የሚሰራው ኦቪድ የተባለው ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ፀጋዬ በፕሮጀክቱ ትውውቅ ወቅት በሰጡት ማብራሪያም ቀለል ያለ የቤት ግንባታ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ያሉት ፕሮጀክቱ ቢያንስ 20 በመቶ ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳም አመልክተዋል፡፡

ከቤቶች ግንባታው በተጨማሪ የከተማዋ ነዋሪን ኑሮ ለማቃለል ይረዳል የተባሉ የምገባ ማዕከላት እና የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታም ከ2-3 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ከተማ አስተዳደሩ አመልክቷል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ