1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ 154 ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ለመንግስት እንዲመለሱ ተወሰነ

ቅዳሜ፣ መስከረም 12 2011

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት አስራ አምስት ገደማ አመታት ታጥረው የተቀመጡ 154 ቦታዎች ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆኑ ትዕዛዝ አስተላለፈ። "ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ተመላሽ" እንዲሆኑ ውሳኔ የተላለፋባቸው ቦታዎች ከአራት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ስፋት እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/35Kqi
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው አስተዳደሩ ከዚህ ውሳኔ የደረሰው ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ከካቢኔያቸው ጋር በዛሬው ዕለት ካደረጉት ውይይት በኋላ ነው። ምክትል ከንቲባው ከውሳኔው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ "በአቋራጭ የሐብት ማካበቻ" ሆኖ ቆይቷል ሲሉ ተናግረዋል። የመረጃ እጦት፣ የመሬት ባለቤትን መለየት አለመቻል እና ሰነዶችን የማመሳከር ሥራ በከተማዋ በተካሔደው የመሬት ፍተሻ ስራ ወቅት ፈተና ከነበሩ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት አቶ ታከለ አስረድተዋል። 

የከተማይቱ ከንቲባ ፅህፈት ቤቱ እንዳለው በዛሬው ውሳኔ መሠረት በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙት የሼክ ሙሐመድ አል-አሙዲ ንብረት ከሆነው ሜድሮክ ግሩፕ የሸራተን ማስፋፊያን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ549 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው አስራ አንድ ቦታዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ይደረጋሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር እና ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ከፌድራል መንግሥት ተቋማት ብቻ ከሁለት ሚሊዮን 700 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው አስራ አንድ ቦታዎች ተመላሽ እንደሚሆኑ የከንቲባ ፅህፈት ቤቱ መረጃ ይጠቁማል። 

በፅህፈቱ ቤቱ መረጃ መሠረት ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች 19 ቦታዎች፣ ከዲፕሎማቲክ ተቋማት ደግሞ 18 ቦታዎች ተመላሽ እንዲሆኑ ውሳኔ ተላልፏል። እነዚህ ቦታዎች ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ግንባታ እንዲከናወንባቸው  የተሰጡ ናቸው ተብሏል።  "ከተማው ውስጥ ከቤቶች ልማት ጋር ተያይዞ ብዙ ጥያቄዎች አሉ" ያሉት ምክትል ከንቲባ ታከለ በአስተዳደሩ ውሳኔ ተመላሽ የሚደረጉት ቦታዎች "ወደዛ እንዲሻገሩ እየሰራን ነው" ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ውሳኔዎችን በተደጋጋሚ ሲያስተላልፍ ቢቆይም ተግባራዊ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በዛሬው ውሳኔ መሠረት ወደ ከተማዋ ተመላሽ ከሚሆኑ ቦታዎች መካከል ንብረትነቱ የሼክ ሙሐመድ አል-አሙዲ የሆነው ሁዳ ሪል ስቴት በመሐል አዲስ አበባ ፒያሳ አደባባይ አጠገብ አጥሮ ያስቀመጠው ቦታ እንደሚገኝበት ምክትል ከንቲባው ፍንጭ ሰጥተዋል። ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ሁዳ በቦታው 39 እና 48 ፎቅ ርዝመት ያላቸው መንትያ ሕንጻዎች ለመገንባት የተረከበው ከ20 አመታት በፊት አቶ አሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሳሉ ነበር። 

እሸቴ በቀለ 

ተስፋለም ወልደየስ