1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ጀማሪ ኩባንያ የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

ሐሙስ፣ ግንቦት 12 2013

የኢትዮጵያ ገበሬዎች ግብዓቶች የሚያገኙበትን፣ ማሽኖች የሚከራዩበትን እና ምክር የሚቀበሉበትን መንገድ ለማቃለል የተቋቋመው ለእርሻ የተባለ ጀማሪ ኩባንያ ከምሥረታው ጀምሮ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለእርሻን የመሳሰሉ ኩባንያዎችን የሚበይን እና የሚገጥሟቸውን ችግሮች ይፈታል የተባለ የአዋጅ ረቂቅ አዘጋጅቷል

https://p.dw.com/p/3tctZ
Äthiopien | Startup | Lersha
ምስል Abrhame Endrias/Lersha

ከኤኮኖሚው ዓለም፦በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ጀማሪ ኩባንያ የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

ከ39 ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ስልጠና በተሰጣቸው የግብርና ምሩቅ ወጣት ባለሙያዎች በኩል ለእርሻ የተባለው ጀማሪ ኩባንያ ከሚያቀርበው አገልግሎት ለመቋደስ ተመዝግበዋል። በዚህም የኩባንያው መሥራች እና ማኔጄንግ ዳይሬክተር አብርሐም "ስኬታማ" ብሎ የሚገልጻቸው 160 ክፍያዎች ተፈጽመዋል። በቅንጡ ስልኮች ላይ በሚጫኑ መተግበሪያዎች እና በጥሪ ማዕከሎች አማካኝነት አነስተኛ የእርሻ ማሳ ላላቸው ገበሬዎች የሚቀርበው ግልጋሎት በፍጥነት ባይለመድም አብርሐም ሰኔ ግም ሲል እያደገ እንደሚሔድ ይጠብቃል።

"አይደለም በገጠር ለአርሶ አደር የሚሰጥ እንዲህ አይነት የዲጂታል አገልግሎት ከተማውም ላይ ለመልመድ ረዥም ጊዜ ይፈልጋል" የሚለው የለእርሻ መሥራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አብርሐም እንድርያስ "አሁን የመላመድ መጠኑ በጣም ከፍተኛ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግረናል። ሁለተኛ የኢትዮጵያ የግብርና ወቅት የሚጀምረው ከግንቦት እና ከሰኔ በኋላ ስለሆነ ከፍ የሚለው በዚያ ወቅት ነው። ብዙ ባለድርሻዎች ከእኛ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ያሳዩበት ስለሆነ ተስፋ ሰጪ ነው ግን ዕድገቱ ዘገምተኛ ነው" በማለት ያስረዳል።

በወጣቱ የሥራ ፈጣሪ የተመሰረተው እና ከአመት ከስድስት ወር ገደማ በፊት በይፋ ሕጋዊ ሆኖ የተመዘገበው ኩባንያ አነስተኛ ማሳ ያላቸው የኢትዮጵያ ገበሬዎች የእርሻ ግብዓቶች የሚያገኙበትን፣ ግብርናቸውን የሚያቀላጥፉባቸው ትራክተር እና ኮምባይነር የመሳሰሉ ማሽኖች የሚከራዩበትን እና ምክር የሚቀበሉበትን መንገድ ለማቃለል የተቋቋመ ነው።

"የለእርሻ ዋና ዓላማ የገበሬን ሥራ ዲጂታላይዝ ማድረግ ወይም አርሶ አደሩ ዲጂታላይዜሽን እንዲለምድ አይደለም" የሚለው አብርሐም "የገበሬ ዋና ችግር የግብርና ዋና ግብዓት በጊዜው አለመቅረቡ፤ የእርሻ ማሽነሪዎች በጊዜው አለማግኘቱ እና ለምክር አገልግሎት በጣም የራቀ መሆኑ ናቸው። እነዚህን አገልግሎቶች ወደ አርሶ አደር ለማድረስ ሞባይል መተግበሪያ እና የጥሪ ማዕከልን እንጠቀማለን። የሞባይል መተግበሪያው እና የጥሪ ማዕከሉ  አማርኛ፣ ኦሮሚኛ እና እንግሊዘኛን የቋንቋ አማራጭ የሚሰጡ ናቸው" ሲል ያስረዳል።

ይሁንና እንደ አብርሐም ማብራሪያ ገበሬዎች ለአገልግሎቱ የተዘጋጀውን መተግበሪያ ወደ የእጅ ስልኮቻቸው በመጫን ራሳቸው መጠቀም አይጠበቅባቸውም። "በየአካባቢው በግብርና ተመርቀው ሥራ አጥተው የነበሩ ልጆችን በማሰልጠን ጥሩ ስም ስላጣን ለጊዜው `ለእርሻ ኤጀንት` ብለን እንጠራቸዋለን፤ እነሱ ናቸው እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉት" በማለት ኩባንያው የተከተለውን አሰራር መሥራቹ ይገልጸዋል።

Äthiopien | Startup | Lersha
የለእርሻ መሥራች አብርሐም እንድርያስምስል Abrhame Endrias/Lersha

ለኩባንያው ከምሥረታው ጀምሮ የነበረው የሥራ ሒደት ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም።  “አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ማሽነሪዎችን በመግዛት፣ ብዙ የግብዓት ሱቆችን በመክፈት ሥራውን ከማስፋፋት ይልቅ ዓለም የደረሰበት ዲጂታል አግሪካልቸርን እንሞክር ብለን ስንገባ ገጠር አካባቢ ካለው የትምህርት ተደራሽነት፣ የኢንተርኔት ኮኔክሽን አለመኖር፣ ገበሬው የሚይዘው የስልክ አይነት ትልቅ ችግር ነበር።  ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን የሚያስፋፉ የሕግ ማዕቀፎች ብዙም አልነበሩም" የሚለው አብርሐም ከሶስት አመታት በፊት ጥናት በማድረግ ላይ ሳሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎች እና ድጋፎች ቢያግዟቸውም "ውስጥ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ" ሲል ይናገራል።

ኢትዮጵያ እንደ አብርሐም ላሉ ሥራ ፈጣሪዎች እና ለእርሻን ለመሳሰሉ ጀማሪ ኩባንያዎች የሚመች ጥረታቸውንም የሚያበረታታ የሥራ ከባቢ ያለባት አገር አይደለችም። ከሶስት አመታት በፊት ዓለም አቀፉ የኢንተርፕነርሺፕ እና ልማት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው እና ለሥራ ፈጣሪዎች አመቺነትን በመዘነበት ሰነድ ኢትዮጵያን ከ137 አገሮች በ110ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ለጀማሪ ኩባንያዎች የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ ምን ይዟል?

የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በመተባበር ጀማሪ ኩባንያዎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ይቀርፋል ተብሎ የሚጠበቅ የአዋጅ ረቂቅ አዘጋጅተዋል።  

"እስካሁን በሔድንበት አካሔድ ጀማሪ የንግድ ሥራዎች አደጉ ወይም ፈርጠም ካሉ ኩባንያዎች የተለየ ድጋፍ የሚደረግበት ወይም መንግሥት እነሱን በተለየ መልኩ የሚያስተናግድበት መንገድ የለውም ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም የጀመረ፤ ግማሽ ላይም ያለ፤ ብዙ ርቆም የሔደ የሚጋፈጧቸው ሥጋቶች አንድ አይነት ናቸው" ሲሉ በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የአዳዲስ የሥራ ዕድሎችና ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአዋጅ ረቂቁን ማዘጋጀት ያስፈለገው "በተለየ መልኩ አዳዲስ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ንግዶችን መንግሥት መደገፍ አለበት ከሚል አላማ ነው። ጀማሪ ኩባንያዎች እንላለን እንጂ በውስጡ ደግሞ ኢኖቬቲቭ የምንላቸው አምስት አመት እና ከዚያም በላይ ቆይተው በከፍተኛ ፍጥነት ሊያድጉ የሚችሉ ንግዶች ይኖራሉ። አምስት አመትም አልፏቸው በፍጥነት ማደግ የሚችሉ ወይም እያደጉ ያሉ ማርሽ ቀያሪ ወይም አምድ ቀያሪ በእንግሊዝኛው (disruptive) የምንላቸው ቢዝነሶች ይኖራሉ። ፊት የነበረው የጥቃቅን እና አነስተኛ ስትራቴጂ ከአምስት አመት በላይ ቆይተው በፍጥነት ማደግ ለሚችሉ የተለየ ድጋፍ የሚያደርግበት ምንም አይነት መንገድ አልነበረውም" ይላሉ።

ጀማሪ ኩባንያዎች እነማን ናቸው?

የአዋጅ ረቂቁ በእንግሊዘኛው ስታርትአፕስ ተብለው የሚታወቁ ጀማሪ ኩባንያዎችን የአገሪቱን ሕግጋት በመንተራስ ይበይናል። አቶ ዳዊት "ከተቋቋመ ከአምስት አመት በታች መሆን አለበት። የኢትዮጵያን የፋይናንስ እና የንግድ ሕግ ላለመጣስ የራሱ የሆነ እስከ 51 በመቶ ካፒታል የግል ድርሻ ይዞ የሚንቀሳቀስ መሆን አለበት። አሁን ካለው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች ብያኔ ስንጨምርበት ደግሞ የኢኖቬሽን አስፔክቱ አለ። አዲስ አገልግሎት ይዞ መምጣት የሚችል ወይም ባለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ተጨማሪ እሴት ይዞ መምጣት የሚችል ወይም ያለውን አካሔድ ሰብሮ መምጣት የሚችል መሆን አለበት" በማለት የአዋጅ ረቂቁ ያስቀመጠውን ብያኔ ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።

ይኸ የአዋጅ ረቂቅ ሲጸድቅ ብሔራዊ የጀማሪ ኩባንያዎች ምክር ቤትን (National Start-up Council) ያቋቁሟል። ምክር ቤቱ ከስድስት ያላነሱ ከዘጠኝ ያልበለጡ አባላት የሚኖሩት ሲሆን በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ምኒስትሩ ሊቀ-መንበርነት ይመራል። አባላቱ በምኒስትሩ ተመርጠው በጠቅላይ ምኒስትሩ የሚሾሙ ናቸው።

"ይኸ አዋጅ በውስጡ የግብር ጉዳይ አለው። ሌላው የምዝገባ ጉዳይ፤ የተሰጥዖ ጉዳይ አለው። እነዚህን ነገሮች ሁሉ አጠናቅሮ ለመሔድ ለአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ብቻ የሚሰጥ ሥራ አይደለም። ሰፊ ነው። የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መሳተፍ አለባቸው። ይኸን ሁሉ ለማቀናጀት ሁነኛው መንገድ በምክር ቤት መልክ መሆን አለበት" ሲሉ የምክር ቤቱን አስፈላጊነት ለዶይቼ ቬለ አቶ ዳዊት ተናግረዋል። "ይኸ ምክር ቤት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን መሪዎች ያካተተ ይሆናል" ያሉት አቶ ዳዊት የለት ተለት ሥራዎችን የሚያከናውን የሚወጡ ስትራቴጂዎችን፣ ምልመላዎችን፣ "ማን ማበረታቻ ይሰጠው? ማን ይቅርበት?" የሚሉ ጉዳዮችን የሚከታተል ቴክኒካዊ ኮሚቴ በምክር ቤቱ ሥር እንደሚቋቋም አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ እንደሰፈረው "ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም አዳዲስ ሥራ ፈጠራ የሚመች ከባቢ በመፍጠር ኤኮኖሚያዊ ዕድገትን የማፋጠን" ገዘፍ ያለ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ጀማሪ ኩባንያዎች በሕግ ተመዝግበው ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚፈትናቸው የገንዘብ ጉዳይ አብርሐም እንድርያስ ለመሠረተው እና አሁን በኃላፊነት የሚመራው ለእርሻ የተባለ ኩባንያም አልቀረለትም። "ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ አገልግሎት መስጫ እንደዚህ አይነት አዳዲስ ጅማሮዎች ገበያ አግኝተው እስኪያድጉ ድረስ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ-ንዋይ ይፈልጋሉ" የሚለው አብርሐም ለእርሻ ኩባንያ "አሁን ከ85 በመቶ በላይ መዋዕለ-ንዋዩ ኢኩዊቲ ኢንቨስትመንት ወይም የራሳችንን ገንዘብ ነው እየተጠቀምን ነው" ብሏል።

ኩባንያው ግብርና ሚኒስቴር እና የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኮርፖሬሽን (GIZ) ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር በአጋርነት ይሰራል። "አጋሮቻችን በቀጥታ ለእኛ ገንዘብ ባይሰጡንም ወጪ ልናወጣባቸው ይችሉ የነበሩ እንደ ሥልጠና መስጠት፤ የመስክ ጉብኝቶች እና ልምድ ልውውጦች በማመቻቸት፤ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር የእኛን ኩባንያ በአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረጉልን ነው። አሁን ባለንበት ደረጃ ገበያ ላይ ተስፋፍቶ ወጪው ከገቢው ያልተመጣጠነ ኩባንያን በገንዘብ ለማገዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የንግድ ባንኮች ፍላጎት የላቸውም። ኢንቨስተር የሚባሉትም ከዳር ቆመው የኩባንያውን ዕድገት ማየት ይፈልጋሉ" ሲል የገንዘብ ጉዳይ አሁንም ፈታኝ መሆኑን ገልጿል።

Äthiopien | Startup | Lersha
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በለእርሻ ኩባንያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትምስል Abrhame Endrias/Lersha

አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ከጸደቅ እንዲህ አይነት ችግሮች መላ የሚያገኙበት ለጀማሪ ኩባንያዎች ዕገዛ የሚያደርግ የኢኖቬሽን ፈንድም ይቋቋማል። አቶ ዳዊት "ይኸ ፈንድ ምንጩ በአብዛኛው ከመንግሥት እንዲሆን እንጠብቃለን። ነገር ግን የተለያዩ [የፋይናንስ ምንጮችን] ይዞ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ የሚተዳደር እንዲሆን ነው የምንፈልገው። መንግሥት ከጡረታ ቁጠባም ሊሆን ይችላል ካለው የተለያዩ ምንጮች የሚያዋጣበት፣ ከተለያዩ የልማት አጋሮች ለሥራ ፈጣራ፣ ለኢኖቬሽን እየተባሉ የሚመጡ ብዙ የፋይናንስ ምንጮች ስላሉ ወደዚህ ማምጣት የምንችልበት፤ ከተቻለ የመዋዕለ-ንዋይ ክንፍ እንዲኖረውም ይታሰባል" ብለዋል።

ይኸ ከተለያዩ ምንጮች ሊሰበሰብ የታቀደ ገንዘብ ለጀማሪ ኩባንያዎች የሚሰጠው ምክር ቤቱ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ለሚያሟሉ የሥራ ዘርፎች ነው። ይኸን ፈንድ የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚያስተዳድር ሲሆን የጀማሪ ኩባንያዎች ምክር ቤት የመቆጣጠር ሥልጣን ይኖረዋል።

"የንግድ ባንኮችን በትንሹም እንኳን ግዴታ ውስጥ የሚከት ቢሆን ጥሩ ነበረ። ምን አልባት ከሚያበድሩት ገንዘብ ውስጥ አንድም ሁለት በመቶ ለጀማሪ ኩባንያዎች እንዲያውሉ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ ቢደረግ ብዙ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል" የሚለው አብርሐም "ሕግ መውጣቱ ከማዕቀፍም አንፃር ሌሎችም በሕጋዊነት እንዲያግዙ ለማድረግ በጣም ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል" በማለት ተናግሯል።

የአዋጅ ረቂቁ እንደሚለው ጀማሪ ኩባንያዎች እና ኢኖቬቲቭ የተባሉ የንግድ ሥራዎች የውጭ ምንዛሪ የባንክ አካውንት እንዲኖራቸው ይፈቀድላቸዋል። የግብር ፋታም ያገኛሉ። ይኸ የሚሆነው ግን አሁን በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲጸድቅ ነው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ