1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዉሮጳ መድረኮች የደመቁት የባህርዳር የሰርከስ ጥበበኞች

ዓርብ፣ መጋቢት 23 2014

የሰርከስ ባህርዳር በአዉሮጳ ትርኢቱን እያሳየ ነዉ። ሰርከስ ባህርዳር በተለይ በጀርመን የጥበብ ትርኢቱን ማሳየት ከጀመረ ሦስት ወራቶችን አስቆጥሮአል። የሰርከስ አባላቱን እየመራች ወደ አዉሮጳ የመጣችዉ የማዕከሉ ዋና መስራች እና የአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዉዴ ዘለቀ፤ ቡድኑ ትርኢት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እያስተዋወቀም ነዉ።

https://p.dw.com/p/49Ijc
Äthiopien Circus Bahir Dar
ምስል JABULA AFRICA

«ኢትዮጵያ የሰርከስ ባለሞያዎች ሊደገፉ ይገባል»

የሰርከስ ባህርዳር በአዉሮጳ በተለያዩ ሀገሮች ትርኢቱን እያሳየ ነዉ። ሰርከስ ባህርዳር በተለይ በጀርመን የጥበብ ትርኢቱን ማሳየት ከጀመረ ሦስት ወራቶችን አስቆጥሮአል። ዘጠኝ የሰርከስ አባላቱን እየመራች ወደ አዉሮጳ የመጣችዉ የማዕከሉ ዋና መስራች እና የአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዉዴ ዘለቀ፤ ቡድኑ ትርኢት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ባህል አኗኗር ብሎም ኢትዮጵያን በበጎ ጎን እያስተዋወቀ ነዉ። በተለያዩ የአዉሮጳ ከተሞች የሰርከስ ትርኢትን የሚያሳየዉ እና 10 የቡድን አባላትን የያዘዉ የባህርዳር የሰርከስ ማኅበር ከተመሰረተ ከ 29 ዓመት እንደሆነዉ አርቲስቲክ ዳይሬክተር ዉዴ ዘለቀ ተነግራናለች። ቡድኑ ባለፈዉ ታህሳስ ወር የዶቼ ቬለ የራድዮ ጣብያ በሚገኝበት በቦን ከተማ፤ ለፈረንጆቹ የገና ዋዜማ ጀምሮ ትርኢቱን እያሳየ ቆይቶአል። በአሁኑ ሰዓት የሰርከስ ቡድኑ የተለያዩ የጀርመን ከተሞችን ዞሮ ወደ ፈረንሳይ እና ኦስትርያ፤ ስዊዘርላንድ ብሎም ሆላንድ ሃገራት ዝግጅቱን ለማቅረብ መረሃ-ግብሩን አጠናቋል። በአዉሮጳ ከፍተኛ የኮሮና ተህዋሲ ስርጭት በመከሰቱ እና የዝዉዉር እገዳ በመጣሉ፤  ቡድኑ አብዛኛዉን ጊዜ በልምምድ እና በትምህርት ላይ መቆየቱንም አርቲስቲክ ዳይሬክተር ዉዴ ዘለቀ ተናግራለች። በኢትዮጵያ የመጀመርያዉ ሴት የሰርከስ አሰልጣኝ እንደሆነች የነገረችን የአማራ ክልል የሰርከስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዉዴ ዘለቀን በጀርመን ኖርዝ ራይን ግዛት ዱረን ከተማ ላይ አግኝተናታል።    

Äthiopien Circus Bahir Dar
ምስል JABULA AFRICA

የተለያዩ የሰርከስ አርቲስቶች ስፖርታዊ ጥበብን የተላበሱ ዝግጅቶችን እንዲያቀርቡ በተለዩ መድረክ ይዞ የሚቀርበዉ የጃቡላ አፍሪቃ የተባለዉ ፕሮግራም መሪ ጀርመናዊዉ ጆይ ሙራህ፤ ባህርዳር የሚገኘዉን የሰርከስ ትምህርት ቤትን እንደሚረዱ ተናግረዋል። 

«ባህርዳር የሚገኘዉን የሰርከስ ትምህርት ቤት እየረዳን ነዉ። በትምህርት ቤቱ ከሚገኘዉ የሰርከስ ቡድን ጋር ስንሰራም ወደ አስር ዓመት ሆኖናል። ባህርዳር ከሚገኘዉ ከዚህ የሰርከስ ትምህርት ቤት ወደዚህ ወደ ጀርመን እየጋበዝን በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ትርዒቶችን ስናሳይ ዓመታትን አሳልፈናል።» በጀርመን የጃቡላ አፍሪቃ መድረክ ተጠሪ ጆይ ሙራህ እንደተናገሩት በትርኢት ላይ ከኢትዮጵያዉያኑ የሰርከስ ባለሞያዎች ሌላ ከሌሎች አፍሪቃ ሃገራት ለምሳሌ ከኬንያ ከኮንጎ ከታንዛንያ የመጡ የጥበቡ ባለሞያዎች ተሳታፊ እንደሆኑም ተናግረዋል።

«ድርጅታችን ሾዉ ቢዝ ኢንተርቴንመንት ይባላል። ጃቡላ አፍሪቃ የሚል መጠረርያ የሰጠነዉ ደግሞ በድርጅቱ ስር ለህዝብ መድረክ ላይ የምናቀርበዉ ትርዒት ነዉ። የአፍሪቃ ደስታ እንደማለት ነዉ፤ ትርኢቱ አፍሪቃ ነክ ነዉ። መረሃግብሩን የምንመራዉም እኛ ነን።  በትርዒት ቡድኑ ዉስጥ ከኢትዮጵያ፤ ከዚምባቤ፤ ከኬንያ፤ ከታንዛንያ ፤ እና ከኮንጎ የመጡ  የሰርከስ ባለሞያዎች ይገኙበታል። የተለያዩ ትርኢቶችን እናቀርባለን፤ ባህርዳር የሚገኘዉን የሰርከስ ቡድንን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎችን እንረዳለን።» 

የአማራ ክልል ሰርከስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዉዴ ዘለቀ እንደምትለዉ በኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ አላደገም ይሁንና በሀገሪቱ በርካታ የዘርፉ ጥበበኞ አሉ ድጋፍንም ይፈልጋሉ። የባህርዳር የሰርከስ ቡድን ወደ ጀርመን መምጣት የቻለዉ ለቡድኑ ወጭዉን ሁሉ የሚሸፍን ግዙፍ የጀርመን የመድረክ አቀናባሪ ድርጅትን በማግኘቱ ነዉ።

Äthiopien Circus Bahir Dar
ምስል JABULA AFRICA

የባህርዳሩ የሰርከስ ቡድን በጀርመን ትርኢቱን ባቀረበባቸዉ መድረኮች ሁሉ ተወዳጅነትን አግኝቶአል። RTL በተሰኘ በታዋቂ የጀርመን ቴሌቭዝንም ልዩ ተሰጦአቸዉን የሚያሳዩ ሰዎች በሚቀርቡበት መድረክ ቀርቦ ታይቶአል። ወጣቱ የሰርከስ ቡድን ከትርዒቱ ባሻገር አንዳንድ የትምhreት ኮርሶችን እንደሚከታተል ተነግሮአል።  በጀርመን የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል የተጣለዉ ገደም እየላላ ነዉ። አዉሮጳ የሚገኘዉ የባህርዳር የሰርከስ ቡድንም የጥበብ ትርኢቱን ማሳየት ቀጥሎአል። ቡድኑ እንዲመነደግ በመመኘት ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመቻ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን ። 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ