1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተከሰሱት የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 27 2013

የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ስር የተደነገጉትን በመተላለፍ በክሱ በተደነገገው አግባብ የፖለቲካ ርዕዮትን ለማሳካት በሚል የተመረጡ ሰዎችን በመግደል ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ ካሰሩት ተልእኮ በመቀበል አርቲስቱን መግደሉ በማስረጃ ተረጋግጧል ብሏል ችሎቱ፡፡

https://p.dw.com/p/3yTbN
Äthiopien Hachalu Hundessa
ምስል Reuters/T. Negeri

አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ገድለዋል በተባሉት ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም እውቁ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ተጠርጥረው ከአንድ ዓመት ባለፈ የክስ ሂደት ውስጥ በነበሩት ሶስት ተከሳሾች ላይ ዛሬ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የሽብር ተልእኮን ኦነግ ሸኔ እና ወያኔ ከተባሉት ቡድኖች ተቀብሎ አርቲስቱን በቀጥታ በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ-ሽብርና ህገመንግስት ጉዳዮች ችሎት የእድሜ ልክ እስራት ወስኖበታል፡፡

በግድያው ተባባሪነት እና ገድሎ በመዝረፍ ተስማምቶ ወንጀሉ ላይ ተሳትፏል የተባለው ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ፤ ሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በስድስት ወር ቀላል እስራት እንዲሰናበት ተብሏል፡፡

የከሳሽ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተወካዮች፣ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ሂደት ጥፋተኛ የተባሉት ሶስት ተከሳሾች ከተከላካይ ጠበቃቸው፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች እና ጋዜጠኞች በችሎቱ ታድመዋል፡፡ የሁለተኛ ፀረ-ሽብር እና ህገመንግስታዊ ጉዳይ ችሎቱን የያዙት ሶስት ዳኞችም ከመድረኩ ተቀምጠው የቅጣት ውሳኔው ለግራ-ቀኝ ተከራካሪዎች እና ለታዳሚያኑ ሲነበብ፤ ችሎቱ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የተሰጠውን የውሳኔ ሃሳብ አስታውሷል በመግቢያው ላይ፡፡

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ስር የተደነገጉትን በመተላለፍ በክሱ በተደነገገው አግባብ የፖለቲካ ርዕዮትን ለማሳካት በሚል የተመረጡ ሰዎችን በመግደል ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ ካሰሩት ተልእኮ በመቀበል አርቲስቱን መግደሉ በማስረጃ ተረጋግጧል ብሏል ችሎቱ፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በወንጀል ህግ አንቀጽ 540 እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በወንጀል ህጉ 443/1ሀ በመተላለፋቸው የቅጣት ውሳኔው መሰጠቱንም እንዲሁ፡፡

በተከሳሾች ላይ የተሰጠውን የጥፋተኝነት ውሳኔን ተከትሎ ቅጣት ለመጣል ግራ ቀኝ አስተያየት ማድመጡን ያስታወሰው ችሎቱ፤ ተከሳሾች ጨለማን ተገን አድርገው ድርጊቱን መፈፀማቸው አደገኝነታቸውን የሚያሳይ በመሆኑ በወንጀል ህግ 84 መሰረት ከባድ ቅጣት እንዲወሰን አቃቤ ህግ መጠየቁን አስታውሷል፡፡ አቃቤ ህግ ለዚህም ያቀረበው ማስረጃ 1ኛ ተከሳሽ በጥቅም ተደልሎ 1500 ብር መቀበሉን እና ወደ ፊትም ቃል የተገባለት መሆኑ፣ 2ኛ ተከሳሽም ገንዘብ ለማግኘት በግድያው መስማማቱ በክስ ሂደት መረጋገጡን ነው፡፡

አቃቤ ህግ አክሎም ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ 1ኛ ተከሳሽ ምንም እንኳ ፍርድ ያልተሰጠበት ቢሆንም በባጃጅ ስርቆት መከሰሱን፣ ቃሉንም ሲሰጥ የራሱ መሳሪያ እያለው በህገወጥ የተያዘው በ2ኛ ተከሳሽ መሳሪያ ግድያውን መፈጸሙ፣ ድርጊቱም ድንገት ሳይሆን ታስቦበት የተፈጸመ እና ተከሳሹ በማህበረሰቡ ዘንድ በመልካም ጠባይ የማይታወቅ መሆኑ በክሱ ሂደት በመረጋገጡ ከ2ኛው ተከሳሽ ጋር የቅጣት ማቅለያ እንዳይያዝላቸው ጠይቋል፡፡ በተፈጸመውም ወንጀል በህዝብ እና አገር ላይ በተቀሰቀሰው ሁከት ጉዳት በመድረሱ 1ኛ ተከሳሽ በሞት ፍርድ እንዲቀጣ፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በቅጣት መመሪያ መሰረት እንዲወሰንባቸው ነው አቃቤ ህግ የጠየቀው፡፡

ተከሳሾችም ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት መልካም ስነምግባር ያላቸው፣ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው እና ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ በመሆናቸው ወንጀሉ የሚያስከትለውን ውጤት በእውቀት ማነስ ምክኒያት ባለማገናዘብ የተፈጸመ በመሆኑ ቅጣቱ ቀሎ እንዲወሰን ጠይቀዋል፡፡

ግራ-ቀኝ አስተያየቶችን ተመልክቶ ውሳኔ መስጠቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ ወንጀሉን የፈጸመው በሶስተኛ አካል ተገፍቶ በመሆኑ በጣም ከባድ የማያረገው በመሆኑ የሞት ብያኔ ጥያቄን ውድቅ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡ በመሆኑም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/12 አንቀጽ 3 መሰረት ውሳኔ የተላለፈበት አንደኛ ተከሳሽ በችሎቱ ፍቅደ ስልጣን መሰረት በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እነዲቀጣ ተወስኗል፡፡

ከአምስት እስከ 20 ዓመት በሚያስቀጣው የ1996ቱ ወንጀል ህግ አንቀጽ 540 የተከሰሰው ሁለተኛ ተከሳሽ ሟችን ገድሎ ለመዝረፍ በማሰብ ወንጀሉን በመፈጸሙ፤ እንደ አንደኛው ተከሳሽ ሁሉ ሶስት የአቃቤ ህግ የቅጣት ማክበኛ ተይዞበት የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል፡፡

ወንጀሉ ሲፈጸም አይቶ ለፍትህ አካል ባለማሳወቅ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 443/1ሀ ጥፋተኛ የተባለው 3ኛ ተከሳሽ የስድስት ወር ቀላል እስራት ተወስኖበታል፡፡

የቅጣት ውሳኔው ተከሳሾቹ ከተያዙበት ሃምሌ 1 እና 3 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታሰብ ነው ያለው ፍርድ ቤቱ 3ኛ ተከሳሾች በሌላ ወንጀል የማይፈለግ ከሆነ ቅጣቱን በመጨረሱ እንዲሰናበት በማዘዝ ፍርዱን ለይግባኝ ክፍት አድርጎ መዝገቡን ዘግቷል።

ስዩም ጌቱ 

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ