1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአሜሪካ የትግራይ ማኅበረሰብ አባላት፣ስለክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ የሰጡት አስተያየት

ታሪኩ ኃይሉ
ዓርብ፣ ሰኔ 26 2018

ከሲያትል ያነጋገርነው እና የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ በውይይት መፍትሔ ይገኝለታል የሚል እምነት የለውም። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፣ፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ነው ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ።

https://p.dw.com/p/5GX5c
የመቀሌ ከተማ
የመቀሌ ከተማ ምስል፦ Liu Fangqiang/Xinhua/picture alliance

በአሜሪካ የትግራይ ማኅበረሰብ አባላት፣ስለክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ የሰጡት አስተያየት

በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ አስከፊ ደረጃ ማምራቱ አሳስቦናል ሲሉ፣ በዩናይትድስቴትስ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ገለጹ። የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ያነጋገራቸው ዲያስፖራ የክልሉ ተወላጆች፣ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ይበጃል ያሉትን የመፍትሔ እርምጃዎችም ጠቁመዋል። 
በትግራይ በጀት እና ነዳጅን ጨምሮ መሰረታዊ ነገሮች በመቋረጣቸው የተነሳ፣ሕዝቡ በከፍተኛ ከበባ እና ሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኝ፣በዲያስፖራ የተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚሳተፉት እና በደቡብ ካሮላይና ነዋሪ የሆኑት አቶ አባይ ግደይ ይናገራሉ።

ሕዝቡ ከበባ ውስጥ መግባቱ

"ችግሩ ፡በትግራይ ሕዝብ ላይ ሰቆቃ አለ፣ከበባ አለ፣ተዘግቷል ሁሉም ነገር፤ባጀት የለ ነዳጅ የለ ግንኙነት የለ ሁሉም ነገር ተቆራርጧል።አዲስ አበባ በሄዱት የትግራይ ተወላጆች አማካይነት ደግሞ በመሬት ላይ የሉም።ከትግራይ የተለያያ ጊዜ ወስዶ ለማግባባትም ተሞክሮ አሱ ሳይሆን ቀርቶ ለይቶለታል።ስለዚህ በትግራይ ያለውን ኅይል ለማንበርከክ እንደገና ወረራም ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ የለም፣ሃገሩን ይበታትን ይሆን እንጂ።''

ስለሆነም፣አቶ አባይ እንደሚሉት መረዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች አካላት የክልሉን ኅይሎች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለማወያየት የሚያስችል  መድረክ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።

"መፍትሔ የሚሆነው፣የትግራይ ኅይሎች መፍትሔ እያቀረቡ ነው።አኦቦሳንጆም የተሰጣቸው መልስ፣የፖለቲካ ውይይቱ ይጀመር የሚል ነው፡መፍትሔው ውይይት እና ውይይት ብቻ ነው።''

ውይይት መፍትሔ አያመጣም 

ከሲያትል ያነጋገርነው እና የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ ግን ከዚህ የተለየ ዐሳብ ነው ያለው፤የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳስበው ጋዜጠኛ አብርሃ፣በውይይት መፍትሔ ይገኝለታል የሚል እምነት የለውም።

''ህወሓት የሚባለው ድርጅት ወይም ታጣቂ ቡድን ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ አፈሳ በሌሊት እና በቀን እየታፈሱ፣ወጣቶች አፈሳውን የፈሩ ደግሞ በ10ሺህ ዎች የሚቆጠሩ ከዚያም በላይ በስደት ተበትነው፣ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው እየሸሹ ይገኛሉ።''

ሽሬ በሚገኝ  መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሴት ተፈናቃዮች
ሽሬ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሴት ተፈናቃዮች ምስል፦ Marco Simoncelli

ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፣ፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት ባይ ነው ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ።

''የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ነጻ የማውጣት ካለው ከእዛ አካባቢ አንድ የሰላም ጦር የሚባል አለ፣ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚተባበር ማለትነው፤ብዙ ተዋጊ ኅይሎች አሉት።አንድ ላይ ሆነው ነጻ ካላወጡት በስተቀር ይሄ በድርድር፣በሽምግልና እጅ ይሰጣሉ ማለት ዘበት ነው፣ሰላም ያወርዳሉ ማለት ዘበት ነው።''

የሕጋዊ መንግሥት ጥሪ

በፊላዴልፊያ ነዋሪ የሆኑት አቶ ግደይ ተስፋይ፣አክሱማውያን የተሰኘ የሚዲያ ኔትዎርክ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣አሁን በትግራይ ሕጋዊ የሆነ መንግስት አለ ማለት እንደማይችል ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

''የትግራይ ችግሩ አሁን መንግሥት አለመኖሩ ነው።አብዛኛው  ሊቅ ደግሞ መንግሥት ይኑረን እያለ ነው።አሁን ሁሉም ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ጥሪ ምንድን ነው፣መንግሥት ይኑረን አቃፊ መንግሥት ይኑረን፣ሰላማዊ በሆነ ከፌደራል ጋር እንነጋገር ነው እየተባለ ያለው።''

ሁሉንም የትግራይ ተወላጆች በእኩልነት የሚመለከት አመራር በክልሉ መመስረትን፣አቶ ግደይ በመፍሔነት ሀሳብ አቅርበዋል።

''አቅም ያለው የፖለቲካ መሪ ሕዝቡ በራሱ መርጦ ከቀበሌ ጀምሮ ወረዳዎችን ወክሎ ምክር ቤት መመስረት አለበት።ይህ ምክር ቤት ደግሞ የራሱ ፕሬዚዳንት ይመርጣል።ፕሬዚዳንቱ ደግሞ የራሱን ካቢኔ ያቋቋማል።ይህ ፈጻሚ አካል ከፌደራል ጋር እየተነጋገረ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እያደረገ ሰላማዊ የሆነ ትግል እናድርግ፣የትግራይን አንድነት በዚህ መልኩ እንጠግነው።''ብለዋል። 

ታሪኩ ኃይሉ 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ