1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የኮሮና ምርመራ ዘመቻ ተጀመረ 

ዓርብ፣ ነሐሴ 1 2012

አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በአገር አቀፍ ከተቀመጠው 200 ሺህ ምርመራ መካከል አንድ አራተኛው በአማራ ክልል እንደሚከናወን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ። ዛሬ በተጀመረው በዚህ ዘመቻ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶችን ለመድረስ ታቅዶአል፡፡ 

https://p.dw.com/p/3gbZQ
Äthiopien Addis Abeba | Hilfsgüter der WHO
ምስል Getty Images/AFP/S. Habtab

50 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር ዝግጅት ተጠናቋል

 

በቢሮው የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳሬክተር አቶ ተክለኃይማኖት ገብረሕይወት ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ዛሬ በተጀመረው አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ዘመቻ በአማራ ክልል 42 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር የሚጠበቅ ቢሆንም ክልሉ የተሸለ ሥራ ይሰራል ተብሎ በመታመኑ እስከ 50 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ 
 ከዚህ በፊት የተደረገውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መነሻበማድረግ በአማራ ክልል 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ተክለኃይማኖት፣ ካቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመ ሁሉም ቤቶች ጋር ይደረሳል፡፡ ያ ካልሆነ ግን በትንሹ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቤቶችን ለመድረስ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡ 
ለየዞኖች 3 የመለያ መስፈርቶች እንደተቀመጡና በዛ መስፈርት መሰረት ምርመራው እንደሚካሄድም ያብራሩት አቶ ተክለኃይማኖት ህዝብ ብዛት ያላቸው ዞኖች 80 ከመቶ፣ የተጓዳኝ ህመም በብዛት ያለባቸው ዞኖች 10 ከመቶና የኮሮና ቫይረስ በብዛት ስርጭት የታየባቸው ዞኖች 10 ከመቶውን ይያዛሉ ብለዋል፡፡ 
በዘመቻው በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገመተው አጠቃላይ10ሺህ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ውስጥ 2ሺህ100 ከአማራ ክልል እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ህክምናውን ለመስጠት በክልሉ ባሉ የህክምና ማዕከላት 1ሺህ 200 አልጋዎች ብቻ መኖራቸውን አመልክተው ይህ አንዱ ስጋት እንደሆነም ተናግረዋል፣ ዋናው ጉዳይ ግን ምርመራውን ማድረግና ያለውን ስርጭት ማወቅ ነው ብለዋል፡፡ 
 ከዛሬ ነሐሴ1/2012 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 15/2012 ዓ ም በሚቀጥለው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በአገር አቀፍ ደረጃ 200 ሺህ ሰዎች እንደሚመረመሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አመልክተዋል፡፡ 
 በአማራ ክልል እስከ ትናንት ድረስ ባለው መረጃ 33ሺህ 166 ተመርምረው 642 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 478 አገግመዋል፣ 6 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ህወታቸው ማለፉን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዋለ በላይነህ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 


ዓለምነው መኮንን


አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ