1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከነበሩ 32 የተፈናቃይ መጠለያዎች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ተዘጉ

ሰኞ፣ ጥር 9 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ በአማራ ክልል ከተቋቋሙ 32 የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች መካከል 31ዱ መዘጋታቸውን የክልሉ መንግሥት ገለጸ። የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የቀረው በደባርቅ ከተማ የተከፈተ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/45eZ2
Äthiopien Eyasu Mesfin
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ከነበሩ 32 የተፈናቃይ መጠለያዎች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ተዘጉ

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩ 32 የተፈናቃይ መጠለያዎች መካከል ከአንዱ በስተቀር ሁሉም መዘጋታቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታውቋል፡፡ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ተመላሽ ተፈናቃዮችን እያቀቋምኩ ነውም ብሏል፡፡
ከጥቅምት 2013 ዓም ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች በተፈጠረው ጦርነት በርካታ ንፁሐን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከ2 ሚሊዮን 300ሺህ በላይ የሚሆኑት ተፈናቅለው በመጠለያና በየዘመድ ቤት ለመቆየት ተገድደው ቆይተዋል፡፡
ጦርነቱ በአማራ ክልል መገባደዱን ተከትሎ በክልሉ ከነበሩ 32 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች መካከል 31ዱ መዘጋታቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
በደባርቅ የተፈናቃዮች መጠለያ 5000 ያህል ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ያመለከቱት አቶ እያሱ በተፈናቃዮች አካባቢ አስተማማኝ ሰላም ሲፈጠር እነርሱም የሚመለሱ እንደሚሆኑ አመልክተዋል፡
ተመላሾችን የእለት ምግብ ከማቅረብ ጀምሮ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ አንደሆነም አቶ እያሱ ገልፀዋል፡፡ 
አንዳንድ ተመላሾች በበኩላቸው “የእለት እርዳታ በተፈለገው ፍጥነት እየተሰጠን አይደለም፣ መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለ ስራም የለም” ይላሉ፡፡
በእርዳታ አሰጣጥ ሂደት አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስታወሱት አቶ እያሱ፣ ያም ሆኑ መንግስት ያልመሰልቸት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ንብረታቸው የተዘረፈባቸው ወገኖች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንና መንግስትም እርዳታ አቅም በፈቀደ መጠን  እያቀረበ እንደሆነ ሌሎች ተመላሽ ተፈናቃዮች መስክረዋል፡፡
አንዳንድ  ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ አሁንም ዳተኝነታቸውን እያሳዩ ነው ያሉት አቶ እያሱ፣ አሁንም ቢሆን የተጎዱ ወገኖችን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከ11 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የእለት ምግብ እርዳታ ይሻል፡፡

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ