1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ

እሑድ፣ ጥቅምት 18 2011

“የአማራ የማንነት ጥያቄዎች በሚያነሱ ወገኖች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ይቁም” በሚል በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ። ሰልፈኞቹ “ለጣና ሐይቅና ለላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት ትኩረት ይሰጣቸው” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/37HXL
Äthiopien Demo in Amhara Region
ምስል DW/A. Mekonnen

ሰልፈኞቹ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጠይቀዋል

ዛሬ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ወልዲያ፣ በደሴና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች “የራያ፣ የወልቃይትና የመተከል የአማራነት የማንነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ እንዲመለሱ” ጠይቀዋል። የአማራ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ባህርዳር ሰልፉ የወጡ የከተማይቱ ነዋሪዎች “የትግራይ ክልል መንግስት የአማራ ማንነት ጥያቄ ባነሱ ወገኖች ላይ የሚያደርገውን ማዋከብ ሊያቆም ይገባል” ብለዋል። “የሁለቱ ክልል መንግስታት በየጊዜው መግለጫ በማውጣት ከኃላፊነት ለመሸሽ የሚያደርጉት እሽቅድምድም የትም አያደርስም” ያሉት የባህር ዳር ሰልፈኞች “ይልቁንም በሰከነ መንገድ ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ” አሳስበዋል፡፡

DW ያነጋገራቸው አንድ የሰልፉ ተሳታፊ “ራያ አማራ ሆኖ ሳለ ወደ ትግራይ መጠቃለሉ ከበፊቱም ስህተት ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሰልፉ ከተያዙ መፈክሮች መካከል “ህገ መንግስቱ አማራን አያካትትም፣ በአማራ መቃብር ላይ የምትመሰረት ኢትዮጵያ አትኖርም፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮች ከስልጣን ይወገዱ” የሚሉ ይገኙበታል።

የሰልፈኞችን ጥያቄዎች ያደመጡት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ ዓለሙ ጥያቄያቸው ለሚመለከተው የመንግስት አካል እንደሚያቀርቡ ነግረዋቸዋል፡፡ የባህር ዳሩ ሰልፍ ያለ ምንም ችግር መጠናቀቁን የከተማይቱ ፖሊስ አሳታውቋል። ሰላማዊ ሰልፍ በተካሄደባቸው ሌሎች ከተሞችም ሰልፎቹ “በሰላም ተጀምረው፤ በሰላም መጠናቀቃቸውን” የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል።

Äthiopien Demo in Amhara Region
ምስል DW/A. Mekonnen

ዛሬ በሰልፎቹ ላይ በዋነኛነት የተነሳውን የራያ የማንነት ጥያቄን እና እርሱን ተከትሎ ሰሞኑን በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትላንትናው ዕለት መምከራቸው ተነግሯል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው ይፋ እንዳደረጉት በትላንትናው ስብሰባ “ማንኛውም አይነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲቀርብና እንዲስተናገድ ስምምነት ላይ ተደርሷል” ብለዋል።

በስብሰባው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤዎች፣ በቅርቡ የተሾሙት የሰላም ሚኒስትር እንደዚሁም የትግራይ እና የአማራ ክልል የበላይ አመራሮች ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ በሰልፈኞቹ በተጨማሪ ሲነሱ የነበሩትን የጣና ሀይቅን እና የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የአካባቢውን ነዋሪዎችም አነጋግረዋል።

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ