1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ አነስተኛ መሆን

ማክሰኞ፣ ጥር 24 2014

በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሁኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች መካከል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ ፈቃደኛ የሆኑት ከ10 በመቶ እንደማይበልጡ የአማራ ክልል አስታወቀ። በተመድ ስር ያሉ አንዳንድ ተቋማት ደግሞ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች እገዛ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆነ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/46JpI
Äthiopien Amhara Finance Bureau | Tilahun Mehari
ምስል DW/Alemnew Mekonnen

በአማራ ክልል ለመልሶ ማቋቋሙ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ምላሽ

በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሁኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች መካከል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ ፈቃደኛ የሆኑት ከ10 በመቶ እንደማይበልጡ የአማራ ክልል አስታወቀ። በተባበሩት መንግስታት ስር ያሉ አንዳንድ ተቋማት ደግሞ በጦርነቱ ለተጎዱ አንዳንድ አካባቢዎች እገዛ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆነ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ አመልክቷል፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሐሪ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በምስራቅ አማራ ህወሃት ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ በተለይ በቁሳዊ በኩል የደረሰውን ጉዳትለመመለስ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በዚህ በኩል በአማራ ክልል 266 መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ቢኖሩም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ሰበአዊ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሳተፉ ከተጠየቁት መካከል 28ቱ ብቻ ምላሽ መስጠታቸውን ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡ ተቋማቱ ለሚያካሂዷቸው ፕሮጅክቶች በአጠቃላይ 539 ሚሊዮን ብር መመደባቸውንና በንፁህ መጠጥ ውሀ፣ በምግብና ምግብ ነክ ባልሁኑ ተግባራት፣ በጤና፣ በመጠለያና በሌሎች መሰኮችም 723 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡

Äthiopien | Tilahun Mehari im DW Interview
ምስል Alemenew Mekonnen Bahir Dar/DW

በተባበሩት መንግስታት ስር ካሉ ተቋማት መካከል ተግባሩን በ190 ሀገራት እያከናወነ ያለው የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) 747 ሚሊዮን ብር በመመደብ እገዛ ማድረጉን ዶ/ር ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በኦነግ ሸኔ፣ በቅርቡ ደግሞ በህወሓት የተጎዱ የሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ስራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የ2.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፕሮጀክት አቅዶ እየሰራ ነውም ብለዋል፡፡

FHI የተባለ ድርጅትም በአማራ ክልል ለተለያዩ የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲውል የ6 ቢሊዮን ብር ስምምነት መፈረሙንም ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በክልሉ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች መልካም ቢሆኑም ከደረስው ጉዳት አኳያ በቂ ባለመሆኑ አሁንም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ኮሚቴ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እያጠኑት እንደሆነና ውጤቱም በቅርብ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ