በአማራ ክልል ም/ቤቶች አዳዲስ ድምፆች
ረቡዕ፣ ሰኔ 16 20136ኛው አገራዊ ምርጫ በብዙ ሂደቶች አልፎ ፣ የተቆረጠለት የምርጫ ቀን ሁለት ጊዜ ተራዝሞና በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች አሁንም የምርጫ ጊዜው ሌላ ጊዜ ተቀጥሮለት ባለፈው ሰኞ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ተካሂዶ በአብዛኛው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቅቋል። ብዙዎቹ እንደሚያምኑት ምርጫው ከዚህ በፊት ከተደረጉ ምርጫዎች አንፃር ሲታይ በሁሉም መልኩ ሰላማዊና ነፃ ነበር፣ በዚህ ምክንትም ያልተገመቱ ውጤቶችም በጊዜያዊነት እየወጡ እንደሆነ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ የወጡ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶች በክልልና በፌደራል ተወካዮች ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙበት ሁኔታ እንደሚኖርም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ቻላቸው ታረቀኝም የሚመሰረቱ ምክር ቤቶች ብዝሐ ድምፅ ሊስተናግዱ የሚችሉበት አዝማሚያ እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ አዳዲስ ድምፆች ወደ ክልልም ሆነ ተወካዮች ምክር ቤቶች መግባት ከቻሉ በክርክርና በውይይት የዳበሩ ጠንካራና ገንቢ ፖሊሲዎችንና ህጎችን ለማውጣት ጠቃሚ ሆናልም ብለዋል፡፡ አቶ ቻላቸው እንደሚሉት በምክር ቤቶች የብዝሐ ድምፅ መኖር አዳዲስ ፖሊሲዎችን አጠንክሮ ከማውጣት ባለፈም ቀደም ሲል እንከን የነበረባቸውን ለመከለስም እድል ይፈጠራል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለባት ኢትዮጵያ፣ ከ37 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በመራጭነት ተመዝግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ