1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ሁለት ተመራማሪዎች ተገደሉ

ዓርብ፣ ጥቅምት 16 2011

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ባለፈው ማክሰኞ ለምርምር በሄዱ ግለሰቦች ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለቱ ሲገደሉ አንደኛው በጠና መጎዳቱን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ። የአማራ ክልል ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ ነው ብሏል። 

https://p.dw.com/p/37GFT
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በአማራ ክልል ሁለት ተመራማሪዎች ተገደሉ

በጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ ለምርምር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት በአካባቢው ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት የተገደሉት አቶ ወሰን ታፈረ እና አቶ ማንደፍሮ አቤ የተባሉ ተመራማሪዎች መሆናቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ ለDW ተናግረዋል። ከሁለቱ ተመራማሪዎች ጋር አብረው የነበሩት እና በወረዳው ባለ ቤተሙከራ በምርመራ ባለሙያነት የሚገለግሉት አቶ ኃይለኢየሱስ ሙሉ ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል። ሶስቱ ግለሰቦች ባለፈው ማክሰኞ፤ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ ም፤ ጥቃት የደረሰባቸው በወረዳው በሚገኝ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰገራ ሽንት ናሙናዎችን በመሰብሰብ ላይ እያሉ መሆኑን አቶ አንተነህ አስረድተዋል። 

ተመራማሪዎቹ በድንጋይ እና በዱላ ተደብድበው የተገደሉት ለአካባቢው ህብረተሰብ በደረሰው የተሳሳተ መረጃ ነው ያሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው ድርጊቱ የተፈጸመው “በስሜት በመነሳሳት ነው” ብለዋል። ዕለቱ የገበያ ቀን ስለነበር በርካታ ህዝብ በተሰበሰበበት “ክትባት እየተከተበ ልጆቻችሁ ሞቱ። አራት ህጻናት ሞተዋል” በሚል በተሰራጨ ወሬ የአካባቢው ነዋሪ ተመራማሪዎቹ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን አብራርተዋል። ተመራማሪዎቹ ከናሙና መሰብሰብ ሌላ የትራኮማ በሽታ ያለባቸውን ተማሪዎች ለመለየት የዓይን ቆባቸውን ሲመርምሩ ነበር ተብሏል። 

ሟቾቹ ከጤና ጽህፈት ቤት ህጋዊ የትብብር ደብዳቤ አጽፈው ቢይዙም ለአካባቢው ህብረተሰብ ባለመነገሩ በህብረተሰቡ ዘንድየተሳሳተ ግንዛቤ መፈጠሩን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በወረዳው የወሊድ መከላከያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ማሪስቶፕስ የተሰኘ ድርጅት በህብረተሰቡ ተቃውሞ በአካባቢው የነበረውን ስራ እንዲያቋርጥ መደረጉን አብራርተዋል። ከክትባት ጋር በተያያዘ በቅርቡ በባህር ዳር ላይ ደርሶ የነበረን ተመሳሳይ ችግር የጠቀሱት አቶ አንተነህ በአካባቢያቸውም መሰል ችግር እንዳይከሰት ህብረተሰቡ “በንቃት እየጠበቀ ነበር” ብለዋል። 

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተመራማሪዎቹ ግድያ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለDW የገለጹት የኮሚሽኑ የመገናኛ ብዙሃን አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሰረት በጥቃቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል። የግድያው መንስኤ በመጣራት ላይ መሆኑን እና ምርመራው ሲጠናቀቅ እንደሚገለጽም አክለዋል። የጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከ30 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

(ከጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ)

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ