በትግራይ ክልል 10 ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ
እሑድ፣ ኅዳር 16 2011ዛሬ በትግራይ ክልል በክልሉ በማዕከላዊ እና ደቡብ ዞኖች ባሉ ከተሞች የተደረጉት ሰልፎች በዋነኝነት ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚያወግዙ ነበሩ፡፡ የሰልፉ ተሳታፊዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕግ የበላይነት መሸርሸሩን በመጥቀስ መንግስት መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡ አክሱም፣ ዓድዋ፣ ሑመራ፣ ዓብይዓዲ፣ መኾኒ፣ አላማጣ፣ ኮረምና ሌሎች ከተማች ዛሬ ሰልፍ ካስተናገዱ መካከል ናቸው፡፡
ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ትላንት አላማጣ ከተማ ውጥረት ሰፍኖባት ውላለች፡፡ ትላንት ቅዳሜ ማታ ሶስት ሰዓት ገደማ በከተማዋ ባለ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በተመሳሳይ ጊዜ 3 ቦምቦች መፈንዳታቸውን ምንጮች ገልፀውልናል፡፡ በፍንዳታው በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀፍቶም ወሬታ ለDW ተናግረዋል፡፡
ከቦምብ ፍንዳታዎች አስቀድሞ በከተማዋ የተለያዩ ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መዋላቸውም ተነግሯል፡፡ "የቦምብ ጥቃት ሙከራው ህዝብ በሰልፉ ላይ እንዳይሳተፍ ጫና ለመፍጠር ነበር" ብለዋል ከንቲባው አቶ ሀፍቶም፡፡
ዛሬ በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ ሰልፎች "ፍትህ ለሁሉም" ፣ "ሕገ መንግስት ይከበር" ፣ "የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ አንቀበልም" ፣ "ተጠርጣሪዎች በሌላ አካል መዳኘት የለባቸውም" የሚሉ መፈክሮችን ሰልፈኞቹ አሰምተዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ተስፋለም ወልደየስ