1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቻይና ውሃን ያሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ስጋት

ዓርብ፣ ጥር 29 2012

ቻይና ከመኖሪያ ቤቶቻቸው እንዳይወጡ ካገደቻቸው መካከል ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት የቻይናዋ ውሃን ከተማ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይገኙበታል።  በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በቻይና ውኃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወረርሽኙ ከገባ በኋላ የገጠማቸውን ፈተና ይገልፁልናል።

https://p.dw.com/p/3X36K
China leere Straßen in Wuhan wegen Coronavirus
ምስል Reuters/cnsphoto

የዓለም የጤና ድርጅት በቻይናዋ የውኻን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው  የኮሮና ቫይረስ አጣዳፊ የዓለም የጤና ሥጋት ነው ሲል አውጇል። ቫይረሱ ከቻይና ውጪ በ18 አገሮች የተገኘ ሲሆን ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩት የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ በተለይ ደካማ የጤና መሠረተ ልማት ባላቸው አገራት ሊፈጥር የሚችለው የጤና ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል። የ 20 ዓመቷ ቅድስት በቻይና ውኃን ከተማ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ናት። ስለ ኮሮና ቫይረስ የሰማችው በሽታው የአለም አቀፍ ስጋት ከመሆኑ በፊት ነው። «ስለ በሽታው ከሰማሁ አንድ ወር ሆኖኛል። ቫይረሱ ከመረጋገጡ በፊት እንደ ኢንፉሉዌንዛ አይነት ነገር ውሃን ውስጥ ገብቷል ይባል ነበር። ወደ ታህሳስ መጨረሻ ላይ ግን ጉዳዩ ክብደት አገኘ ። በትምህርት ቤታችን ውስጥም ተጠንቀቁ የሚል መልዕክት ተነገረን። እዛው ከተማ ስለነበርን ቀድመን ነው የሰማነው። ከዛ ወደ ጥር 21 አካባቢ ከቤት እንዳንወጣ ታገድን»
የዩንቨርስቲ ተማሪዎቹ  ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የቻይና ከተሞች ነዋሪዎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ከልክለዋል። 11 ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሏት ውሃን ከተማ የኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱ የተረጋገጠው ልክ የዛሬ ወር ነበር። እስካሁን ከ200 በላይ ሰዎች ሞተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል። ቻይና ውስጥ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ባይገደዱ ኖሮ በቫይረሱ ከዚህ የበለጠ ሰዎችም ይያዙ ነበር።  ቅድስት እስካሁን ከቤት የወጣነው አስቤዛ ለመግዛት ስንል ብቻ ነው ትላለች።  « ከዚህ በኋላ ራሱ መውጣት አይቻልም እየተባልን ነው። ስለዚህ በጣም ብዙ ምግብ ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀምጠን ሁሉም በእየክፍሉ እያበሰለ አሁን ላይ ይመገባል። በፊት ግን አምስትም ስድስትም እየሆንን አንድ ላይ እንመገብ ነበር።  ወደ ሌላ ክፍልም መሄድ አይቻልም።»
እንደ ቻይና የትምህርት ሚኒስቴር ከሆነ እኢአ በ2018 ዓም ቻይና ውስጥ 80 000 የአፍሪቃ ተማሪዎች ነበሩ። ከ 4000 በላይ ደግሞ በውሃን ከተማ የሚማሩ ናቸው። እስካሁን በቻይና ትምህርታቸውን ለመከታተል ከሄዱ አለም አቀፍ ተማሪዎች በበሽታው አንድ ተማሪ ተያዘብኝ ያለች ሀገር ህንድ ናት። ኢትዮጵያ ከቻይና ሲመለሱ በጥርጣሬ በህክምና ማዕከል ያቆየቻቸው አራት ተማሪዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን አስታውቃለች። ይህ በተለይ ለእነ ቅድስት ጥሩ ዜና ነው።
እስካሁን ስጋት ውስጥ የሚገኘው በአካል ዮሴፍ ሌላው ኢትዮጵያዊ የውሃን ከተማ ተማሪ ነው።« በጣም አስፈሪ ነገር ነው። በሽታው በትንፋሽ ይተላለፋል። እኔ በር ከፍቼ ስገባ የነካሁትን መክፈቻ ሌላ ሰው ቢነካ ሊተላለፍ ይችላል። በዛ ላይ እስካሁን መድሀኒት አልተገኘለት። በአካል በአሁኑ ሰዓት ከውሃን ከተማ 1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጓንዡ ከተማ ነው የሚገኘው። ጓደኞቹን ለመጠየቅ ወደዚች ከተማ የተጓዘው ወጣት  የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ውሃን ከተማ በመቋረጡ የተነሳ መቼ እንኳን ወደሚማርበት ከተማ እንደሚመለስ አያውቋም። በጓንዡ ከተማ ያለውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፀዋል።« እዚህም ያለው ሁኔራ ተመሳሳይ ነው። በአላቸው ስለሆነ ስቆችም ተዘግተዋል። ቤታችን ውስጥ መቀመጥ ነው። እቃ ለመግዛት ብቻ ነው የምንወጣው። ግን እንደ ውሃን ታክሲ እና ሜትሮ አልተዘጋም። ግን የሚንቀሳቀስ ሰው የለም።»

China leere Straßen in Wuhan wegen Coronavirus
ምስል picture-alliance/AP Photo/CHINATOPIX
China Wuhan Leere Supermarkt Regale nach Coronavirusausbruch
ምስል picture-alliance/AP Photo/Chinatopix
Schweiz Genf | Pressekonferenz  WHO - Tedros Adhanom Ghebreyesus Ruft Gesundheitsnotstand wegen Coronavirus aus
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

መላኩ እንዲሁ ውሃን ውስጥ በሚገኝ ሌላ ዩንቨርስቲ ውስጥ የዶክትሬት ተማሪ ነው። ስለ ቫይረሱ መጀመሪያ ላይ ሲሰማ እሱም ስጋት ገብቶት ነበር። « በተለይ ደግሞ ዜናው መብዛቱ። በየትኛውም በየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ስለሱ ነበር የሚወራው። በጣም የተጋነኑ ነገሮች ነበር የሚወራው። ማዳን እንደማይቻል። ወዘተ እና ለተወሰነ ጊዜ በጣም እየሰጋን ነበር። ከዛ ግን ቀንህ ከደረሰ አታመልጥም ማለት ጀመርኩ።» 
ይህ ቫይረስ ባይከሰት ኖሮ ተማሪዎቹ ከ15 ቀናት በኋላ ትምህርት ይጀምሩ እንደነበር የገለፀችልን ቅስድት እስከ ሰኔ ድረስ ትምህርት ላይከፈት ይችላል የሚል ስጋት አላት። 
ይሁንና እንደ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ያሉ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከውኃን ከተማ እያስወጡ ይገኛሉ ወይም መንገድ እያመቻቹ ነው።
በቻይና ውሃን ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረትም ዛሬ ባወጣው መግለጫ በርካታ ተማሪዎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ይሻሉ። የህብረቱ ሊቀ መንበር እና የሶስተኛ ዓመት የዶክትሬት ተማሪ የሆነችው ዘሀራ አብዱልሀዲ ከተማሪዎች የሚደርሰን ጥያቄ በመጠናከሩ የተነሳ ኤምባሲው ምላሽ እንዲሰጠን ከሁለት ቀን በፊት በይፋ ጠይቀናል ትላለች። በቻይና ቾንቺን ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ቆንስል ጀነራል አቶ አንተነህ ታሪኩ ለDW ሀሙስ ዕለት በሰጡት ምላሽ ዜጎቹን ከቻይና ማስወጣቱ ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም። ሆኖ ሲገኝ ግን መንግሥት ዝግጁ ነው። « እስካሁን ባለው ሁኔታ በቻይና መንግሥት በኩል ከቁጥጥራችን ውጪ ነው። ዜጎችን ማውጣት ትችላላችሁ የሚል የተገኘ ፍንጭ የለም። ሁለተኛ  ተማሪዎቻችን በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። ማንኛውም አይነት አቅርቦት እየተሟላላቸው ነው። እስካሁን በጤናቸው በኩል ምንም የደረሰ ችግር የለም። በቀጣይ ግን ሁኔታውን እየተከታተልን አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝ ጊዜ ዜጎቻችንን ለማስወጣት መንግሥት ዝግጁ ነው።» 

Symbolbild Corona-Virus
ምስል Reuters/D. Ruvic

መላኩ እስካሁን ትምህርት ቤቱ አስፈላጊ ቁሳቁስም ይሁን መረጃ በማቅረብ ከፍተኛ ትብብር እንደሚያደርግላቸው ገልፆልናል። በውኃን ከተማ እና አቅራቢያዋ በሚገኙ አካባቢዎች ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንገኛለን የሚለው መላኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከከተማዋ ማስወጣት ቢጀምር  እንኳን ውሃንን የግድ ለቆ መውጣት አይፈልግም።

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ