1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ የአየር በረራ መታገዱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 25 2013

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መሠረት መለዮውን፣ ሀገሩን እና ሕዝቡን እንዲከላከል" መወሰኑን ተናግረዋል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ "በትግራይ ውስጥ እና ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም የአገር መከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ የተከለከለ ነው" ብሏል።

https://p.dw.com/p/3kqV2
Äthiopien Fernsehansprache Abiy Ahmed, Ministerpräsident
ምስል Ethiopian Broadcasting corporation

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከገለጹ በኋላ በትግራይ ክልል የአየር በረራን ጨምሮ የመጓጓዣ አገልግሎት እንደማይኖር የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ "በትግራይ ውስጥ እና ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም የአገር መከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ የተከለከለ ነው" ብሏል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሊቱን በሰጡት መግለጫ መቀመጫውን በትግራይ ክልል ባደረገው የመከላከያ ሠራዊት ላይ "ከመቐለ ጀምሮ በበርካታ ሥፍራዎች በከሐዲ ኃይሎች እና ባደራጁት ኃይል ጥቃት ተፈጽሞበታል" ብለው ነበር።

ጠቅላይ ምኒስትሩ "እጅግ አስነዋሪ" ባሉት ጥቃት "ሰላም ለማስከበር በተለያየ አገር የተሰማራው የአገር መከላከያ ሠራዊት እንኳ በውጭ ኃይሎች ያልደረሰበትን ጥቃት በገዛ ወገኖቹ ከጀርባው እንዲመታ፤ ብዙዎች እንዲሰዉ፤ እንዲቆስሉ፤ ንብረቶች እንዲወድሙ ተደርገዋል።" ሲሉ ተደምጠዋል።

ትናንት ለሊት በቴሌቭዥን ከሰጡት መግለጫ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው "የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል።  ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል" ብለው ነበር።

ጠቅላይ ምኒስትሩ በቴሌቭዥን በሰበር ዜና በተላለፈ መልዕክታቸው "ይኸንን ከሐዲ፤ ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈር እና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

"የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መሠረት መለዮውን፣ ሀገሩን እና ሕዝቡን እንዲከላከል" መወሰኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በበኩሉ በክልሉ የአየር በረራ መከልከሉን አስታውቋል። ድምፂ ወያነ የተባለው የክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ በንባብ ባቀረበው መግለጫ የክልሉ መንግሥት ከክልሉም ይሁን ወደ ክልሉ የሚደረግ የመከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴን መከልከሉ ተገልጿል። 

"በትግራይ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አይኖርም" ያለው ይኸው መግለጫ "ወደ ትግራይ የሚደረግ ማንኛውም የአየር በረራ የተከለከለ ነው። ይኸንን ውሳኔ በመጣስ በአየር፤ በሕዝብ እና በንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ማንኛውም አይነት ሙከራ ተመጣጣኝ እርምጃ ይወሰድበታል" በማለት አስጠንቅቋል።

"ከየትኛውም አካባቢ የመጡ የሠራዊት አዛዦች እና አባላት የትግራይ ሕዝብ ልጆች ስለሆኑ የፖለቲካ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ ተገቢው እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው መታወቅ አለበት።" ያለው የክልሉ መግለጫ ጠቅላይ ምኒስትሩ ተፈጽሟል ስላሉት ጥቃት የሰጠው ማብራሪያ አልነበረም።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ በሰጡት መግለጫ "በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ፈጽመዋል" ብለው ነበር።  በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ በሚገኙት ሶሮቃ እና ቅራቅር የተባሉ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተናግረዋል።

"እስካሁን ባለን መረጃ በሶሮቃ እና በቅራቅር አካባቢ የውጊያ ሙከራ አድርጓል። ልዩ ኃይላችን [ጥቃቱን] መክቷል።" ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የክልሉ መንግሥት ለሚያስተዳድረው ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

"ሠራዊታችን በሚሊሺያ እና በልዩ ኃይል ከበባ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ የተወሰኑ አባላትን ከውስጥ ማዳን እና ማውጣት ችሏል። አንዳንድ ከባድ መሳሪያዎችንም ወደ እኛ ማውጣት ችለናል። እነዚህ ተመልሰን ለውጊያ እንዲዘጋጁ አድርገናል" ብለዋል።