በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ኤሌክትሪክ ስርጭት ጀመረ
ረቡዕ፣ ኅዳር 28 2015ማስታወቂያ
መቐለን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ ከተሞች ከ18 ወራት በኃላ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የሐይል ቋት የኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት ማግኘት ጀመሩ። መቐለ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሐይል ሰሜን ሪጅን ሠራተኞች ለዶቼቬለ እንዳረጋገጡት፣ከትናንት ማምሻ ጀምሮ የትግራይ ዋና ከተማ መቐለን ጨምሮ መኮኒ፣ ውቅሮ፣ ዓዲግራት፣ ዓብይዓዲ እና ሌሎች በአካባቢው ያሉ ከተሞች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኃይል ቋት የኤሌክትሪክ ሐይል ማግኘት ጀምረዋል። ትግራይ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የሐይል ቋት ታገኘው የነበረ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሰኔ ወር 2013 ዓመተ ምህረት ወዲህ ተቋርጦ ነበር። በዚህ መካከል በትግራይ ከሚገኝ የሐይል ምንጭ፣ በክልሉ አስተዳደር አስተባባሪነት የተቆራረጠ የኤሌክትሪክ ሐይል ለህዝቡ ይቀርብ ነበር።ትላንት ማክሰኞ ከ11 ሰዓት ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሐይል ቋት ለመቐለና ለተለያዩ የትግራይ ከተሞች መቅረብ መጀመሩ የሐይል እጦትን ያቃልላል ተብሎ እንደሚገመት አዜብ ታደሰ በስልክ ያነጋገረችው የመቀሌው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ገልጾልናል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
አዜብ ታደሰ