1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች ስለሰላም ስምምነቱ ምን ይላሉ?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2015

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም በመንግሥት እና በህወሃት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በአዎንታዊነት እንደሚቀበሉት ትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለጹ።

https://p.dw.com/p/4JGA2
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ስለሰላም ስምምነቱ አስተያየት

 

በርካቶችን ለሞት፣ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ችግሮች የዳረገውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በብዙዎች ላይ ተስፋ አሳድሯል። አስተያየታቸው ለዶቼቬለ የሰጡት በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱት ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት እንደሚያደንቁ እና በአዎንታ እንደሚቀበሉ አስታወቀዋል። ስለሰላም ስምምነቱ በዉጭ የሚኖሩ የትግራይ ፖለቲከኞችና ተወላጆች አስተያየትያነጋገርናቸው የዓረና ትግራይ ከፍተኛ አመራር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ «ትግራይ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እና ቀጠናው በጦርነት ውስጥ መቀጠል የለበትም» የሚሉ ሲሆን፣ ለዚህም በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራዩ ህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት «ታላቅ የሰላም ዕድል የሚፈጥር ነው» ብለውታል። አቶ ዓምዶም የሰላም ስምምነቱ የፈረሙት ሁለቱ ኃይሎች ውሉን እንዲያፀኑም ጥሪ አቅርበዋል። የሁለቱን ኃይሎች የሰላም ስምምነት አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ በበኩሉ ስምምነቱን «ተስፋ ሰጪ» ብሎታል። ዓሲምባ በመግለጫው የሰላም ስምምነቱ «ከጅማሮ እስከ መጨረሻው ድረስ የህዝቦች ጥቅም ሳይሸራርፍ የሚያስጠብቅ፣ በምንም ሁኔታ ወደ ዳግም ጦርነት የማይመራ ሆኖ እንዲጠናቀቅ» ጥሪ አቅርቧል። ያነጋገርናቸው የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ ሊቀመንበር አቶ ሐጎስ ወልዱ የሰላም ሂደቱ ጅማሮ በአስቸኳይ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ገልፀዋል። የሰላም ስምምነቱ በበርካቶች ዘንድ ታላቅ ተስፋ የፈጠረ ቢሆንም ጊዜ በማይሰጥ ረሀብ፣ የመድኃኒት እጦት እና ሌሎች በርካታ ችግሮች ላይ ላለው የትግራይ ህዝብ ከስምምነቱ ስድስት ቀናት በኋላም ቢሆን እስከ ዛሬ ወደ ትግራይ የገባ ሰብአዊ እርዳታ ይሁን መድኃኒት፣ የተጀመረ የትኛውም የህዝብ አገልግሎት የለም።

Ätiopien  Tigray  Meeting Nairobi
በሰላም ስምምነቱ መሰረት ናይሮቢ ኬንያ ላይ የቀጠለው ውይይት ምስል African Union

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ