1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተመድ ጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለአፍሪቃ

ሰኞ፣ መስከረም 16 2015

አፍሪቃ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የአህጉሪቱ መሪዎች ግፊታቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በኒውዮርክ 77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ በርካታ የአፍሪቃ ሀገራት፣አህጉሪቱ በጸጥታው ምክር ቤት ተገቢው ውክልና እንዲሰጣት ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4HN78
USA, New York | Sitzung des UN-Sicherheitsrats
ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

በተመድ ጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለአፍሪቃ

በኒውዮርክ ከተማ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት 77ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ በርካታ የአፍሪቃ መሪዎች ተመሣሣይ አጀንዳ አስተጋብተዋል። ይኸውም አህጉሪቱ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ይኑራት የሚል ነው። የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣በጉባዔው ፊት ባደረጉት ንግግር፣ የዓለሙ ተቋም ዘመኑን የዋጀ ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል። «ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለማንጸባረቅና ለጊዜያቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል።»

ለአፍሪቃ ችግር አፍሪቃዊ መፍትሔ ተግባራዊ መሆን የሚችለው፣ አህጉሪቱ በጸጥታው ምክር ቤት ተገቢው ውክልና ሲኖራት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደመቀ መኮንን፣ አፍሪቃ በጸጥታው ምክር ቤት ተገቢው ቦታ ሊሰጣትና ትክክለኛው የአፍሪቃ ድምጽ ሊሰማ እንጀሚገባው አሳስበዋል።

የ54 አገሮች አህጉር አፍሪቃ፣ ከኮቪድ 19 ለማገገም እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲሁም ግጭትን ለመቋቋም እየታገለች ባለበት ወቅት፣ ኢፍትሐዊ የሆነ ስርዓት ተጽእኖ እየደረሰባት ነው ሲሉ በርካታ መሪዎች ይስማማሉ። የሴኔጋል፣የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋቦን ፣ ጋና፣ናይጄሪያና ኬንያ መሪዎች ይጠቀሳሉ። አዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ለጉባዔው የመጀመሪያ በሆነው ንግግራቸው፣ የጸጥታው ምክር ቤት የአካታችነት ጉድለት እንዳለበት አመልክተዋል። «የዴሞክራሲ ስጋቶች ፣ኢዴሞክራሲያዊ እና ውክልና በሌለው የጸጥታው ምክር ቤት፣ ተአማኒነት ባለው መልኩ አይፈቱም። ይህ ወሳኝ ተቋም የሰው ልጅን ወክሎ የመጠበቅ፣ የመከላከልና የማስከበር አደራ የተጣለበትን እሴት ማንጸባረቁ በጣም አስፈላጊ ነው።»

Liz Truss visit to US for the United Nations General Assembly
ምስል Stefan Rousseau/REUTERS

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን፣ የአፍሪቃ መሪዎች በጸጥታው ምክር ቤት አባልነት ለመግባት ያቀረቡትን ጥያቄ ደግፈዋል። ባይደን ጥያቄውን፣ «ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚሄድ እርምጃ ነው» ብለዋል ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር። ዶይቸ ቨለ ስለጉዳዮ ያነጋገራቸው በሞርጋን ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የውክልና ጥያቄውን የሚያነሱት፣ከሌሎች የሚደርባቸውን ተጽእኖ ለመከላከልና ለመቋቋም ነው ይላሉ። ይሁንና ጥያቄያቸው ምላሽ ያገኝ ዘንድ፣ የደቡብ አሜሪካና የእስያ አገሮችን ድምጽ ማስተባበር እንዳለባቸው፣የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ሳይንስ ምሁሩ ጠቁመዋል። «አፍሪካውያኖች ከዚህ በፊትም ሦስተኛው ዓለም በሙሉ ብዙ የታገሉት ነገር አለ። ለምሳሌ 1970ዎቹ ውስጥ የዓለም ሁኔታ ግሎባል ሳንክቸሪ የሚባለው ብዙዎቻችን ነጻ ባልነበርንበት ጊዜ የተቋቋመ ስለሆነ ለእኛ ዕድገት በጣም እንቅፋት ስለሆነ መቀየር አለበት ብለው የተነሱበት ጊዜ አለ። የገለልተኛ መንግሥታት ተብሎ 120 ሃገራት እንደዚሁ ተቋቁመው በተለይም በዚያ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ጊዜ እኛ ውስጥ ጣልቃ አትግቡ እያሉ ብዙ እየለፉና እየታገሉ ነበረ። ያ ሁሉ እርባና ቢስ ሆነ። እና አሁንም ይህ ነገር አፍሪቃ ብቻ ተነስታ እንደዚሁ የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ መጠየቁ ብዙ ላያስኬድ ይችላል። ነገር ግን ሌላው ደቡብ አሜሪካ ለምሳሌ የአካባቢ ድርጅቶች አላቸው፤ እስያኖችም እንደዚሁ አንድ ላይ ተነስተው ማስጨነቅ አለባቸው። የተባበረ ክንድ በዓለም ደረጃ በተቀነባበረ መልኩ ጥያቄ ማቅረብን መግፋት አለባቸው» ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ