በቤንሻንጉል የምርት መቀነስና የኑሮ ውድነት ስጋት
ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2011
ባለፈው አንድ ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርት መጠን መቀነሱንና በዓመቱ ውስጥ ሊሰበሰብ የታቀደው ከ30 ሚሊዩን በላይ ኩንታል ምርት በዕቅዱ መሠረት አለመከናወኑን የክልሉ የግብርና ቢሮ መረጃ ያሳለያል፡፡ ለዚህ ምርት መጠን መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በክልሉ የነበረው ግጭትና አመረጋጋት መሆኑም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሳ አህመድ ለ “DW” ገልጸዋል። የነበረው የጸጥታ ችግር በአብዛኛው አካባቢ በተቋሙ ለአርሶ አደሩ የሚደረገው ሙያዊ እገዛ አዳጋች እንዲሆን ከማድረግ አልፎ በምርት አሰባሰብ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደሩ በክልሉ የግብርና ምርት አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። በካማሽ ዞን ብቻ 6 በሚደርሱ ወረዳዎች ምርት አሰባሰብ ሂደት ተስተጓጉሎ እንደነበር ነው አቶ ሙሳ የተናገሩት። በዘንድሮውም ዓመት ሰብል በሚዘራበት ወቅት አንዳንድ አካባቢዎች አለመግባበቶች በመፈጠራቸው በታቀደው መሠረት እየተሠራ አልነበረም ብለዋል። ይህንን ለማካካስና በቀጣይ ዓመት የኑሮ ውድነት በክልሉ እንዳይፈጠር ለመከላል አርሶ አደሮሩ መስኖ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሠራ እና በነሐሴ እና መስከረም የሚዘሩ ሰብሎችን አርሶ አደሩ እንዲያመርት ታቅዶ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል። በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን ከ38 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ እንደሆነ የግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል። ዝርዝሩን የአሶሳው ዘጋቢያችን ነጋሳ ደሳለኝ ልኮልናል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ